ገንዘብ ነክ ትስስር
አላህ (ሱ.ወ) በምድራዊ የሕይወት ቆይታ ሲሳይን ለመፈለግ መልፋትን ደንግጓል፡ አበረታቷል፡፡ ይህም እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
- አንድ ግለሰብ፣ ስራ የመስራትና በአቅሙ የመንቀሳቀስ ብቃት ካለው ሰዎችን መለመንን ኢስላም ከልክሎታል፡፡ መስራት እየቻለ፣ የመንቀሳቀስ ብቃት እያለው ሰዎችን የሚለምን ሰው፣ ልመናው አላህ ዘንድም ሆነ ሰዎች ዘንድ ያለውን ክብርና ደረጃ እንደሚያሳጣው አስተምሯል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በፍርዱ ዕለት በፊቱ ላይ ቁራጭ ስጋ የሌለ ሆኖ አላህን እስከሚገናኝ ድረስ አንዳችሁ ሰዎችን ከመለመን አይወገድም፡፡›› (አል ቡኻሪ 1405 ሙስሊም 1040)
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ችግር ገጥሞት፣ ችግሩን እንዲቀርፉለት ለሰዎች ያቀረበ፣ ችግሩ አትወገድም፤ ችግሩን ለአላህ ያቀረበ ግን አላህ ሊያከብረው ይከጀላል፡፡›› (አህመድ 3869 / አቡ ዳውድ 1645)
- ኢስላም በፈቀደው ክልል ውስጥ የሚከናወኑ እስከሆኑ ድረስ፣ ኢንዱስትሪያዊ፣ የልማትና የአገልግሎት መስጠት ስራዎች በሙሉ ነውር የለባቸውም፡፡ ነብያት፣ በሕዝቦቻቸው ውስጥ ይታወቁ የነበሩት፣ የተፈቀዱ ወይም ሐላል ስራዎችን የሚሰሩ በመሆናቸው ነበር፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ፍየል የጠበቀ ቢሆን እንጂ አንድም ነብይ አልተላከም፡፡›› (አል ቡኻሪ 2143) ‹‹ነብዩላህ ዘከሪያ አናጺ ነበሩ፡፡›› (ሙስሊም 2379) የተቀሩት ነብያትም እንዲሁ በመሰል ሙያዎች ላይ ተሰማርተው ይሰሩ ነበር፡፡
- በስራው ላይ ኒያውን አሳምሮ፣ ራሱን እንዲሁም ቤተሰቡን የሰው እጅ እንዳይከጅሉ ለማድረግ እና ችግረኞችን ለመርዳት ያቀደ ሰው፣ በሚሰራው ስራና በልፋቱ ምንዳን ያገኛል፡፡
በማበራዊ ግንኙነትና በመጠቃቀሚያ ነገሮች ዙሪያ ያለው መሰረታዊ መመሪያ
ሰዎችን አንዱን ከሌላው በሚያገናኙና ከባለጉዳይ ጋር በሚከናወኑ ማናቸውም ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ፡ መሸጥ፣ መግዛት፣ ማካራየትና፣ ሌሎችንም ስራዎች አስመልክቶ ኢስላም ያስቀመጠው መሰረታዊ መመሪያ የሚከተለው ነው፡፡
አንድ ነገር በራሱ እርም(ሐራም) መሆኑ፣ አለያም ከመጣበት ምንጭ አንጻር እርም(ሐራም) መሆኑ ተነጥሎ ከተነገረው ውጭ፣ ነገሮች ሁሉ የተፈቀዱ ናቸው፡፡ እና እነርሱን ማከናወንም ይቻላል፡፡
በቀጥታ በራሱ እርም የተደረገ፡
ይህ፣ አላህ (ሱ.ወ) አካሉን እርም ያደረገው ነገር ሲሆን፣ እርሱን መነገድ፣ መግዛትም ሆነ መሸጥ፣ ማከራየት፣ በማምረትና ለሰዎች ማከፋፈልና ማሰራጨት አይፈቀድም፡፡
የሚከተሉት ኢስላም በቀጥታ አካላቸውን እርም ያደረጋቸው ነገሮች ናቸው፡፡
- ውሻና አሳማ
- የሞቱ እንስሳት ወይም የአካላቸው ክፋይ
- አስካሪና አልኮል መጠጦች
- አደንዛዥ እጽና ማንኛውም በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነገር
- በሰዎች መካከል ዝሙትና መሰል እኩይ ተግባራትን የሚያስፋፉ መሳሪያዎች፣ ካሴቶች፣ የኢንተርኔት ድህረ ገጾች፣ የዝሙት ማስፋፊያ መፅሔቶች
- ጣኦታትና ማንኛውም ከአላህ ሌላ የሚገዙት ነገር
ከተገኙበት ምንጭ አንጻር እርም የተደረጉ ነገሮች
እነኚህ፣ መሰረታቸው የተፈቀደ ገንዘብና ንብረቶች ሆኖ እርምነታቸው ከተገኙበት ምንጭ አንጻር የሆነ ነገሮች ናቸው፡፡ ምንጫቸው ማህበረሰቡንና ግለሰቦችን የሚጎዱ በመሆነቸው ምክንያት እርም የተደረጉ ናቸው፡፡ በማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ነገሮችን እርም የሚያደርጉ ምክንያቶች፡
ወለድ፤ ማጭበርበር፤ አለመታወቅ፤ በደል፤ ቁማር
እነኚህን ጉዳዮች በሚከተለው መልኩ እናብራራቸዋልን