ወለድ

በወለድ ውስጥ በደልና በሌላው ላይ ጉዳት ማድረስ የሚገኝበት በመሆኑ በኢስላማዊው ሕግ እርም የተደረገ ጭማሪ ገንዘብ ነው፡፡

የወለድ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ታዋቂዎቹና እርምነታቸው በጣም የጠበቀው፡ የብድርና የእዳ ወለድ ነው፡፡ ይህ በአንድ ገንዘብ ላይ ያለ ሸያጭ ወይም በሁለቱ ጠረፎች መካከል የእቃ ልውውጥ ሳይኖር የሚገኝ ጭማሪ ሲሆን ሁለት መልክ አለው፡፡

  • የእዳ ወለድ

የብድሩ መክፈያ ወቅት ደርሶ ተበዳሪው በቃሉ መሰረት መክፈል ሳይችል ሲቀር በብድሩ መጠን ላይ የሚደረግ ጭማሪ ነው፡፡

ለምሳሌ፡ አቶ ሰዒድ ከአቶ ኻሊድ ከአንድ ወር በኋላ ለመክፈል 1000 ዶላር ተበደሩ እንበል፡፡ ወሩ ሲያልቅና የመክፈያው ወቅት ሲደርስ፣ አቶ ሰዒድ መክፈል ባይችሉና በቃላቸው መገኘት ቢያቅታቸው፣ አቶ ኻሊድ በተስማሙበት ወቅት ላይ ማለትም ወሩ እንዳለቀ የሚከፍሉት ከሆነ ያለምንም ጭማሪ ገንዘቡን ሊከፍሉት፣ ከተጨማሪ አንድ ወር በኋላ የሚከፍሉት ከሆነ ደግሞ 1100 ዶላር እንዲከፍሉት፣ ደግሞም መክፈል ካልቻሉ ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ 1200 ዶላር አድርገው ይከፍሉት ዘንድ እንደ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጡ፣ እነኚህ ጭማሪዎች የእዳ ወለድ ይባላሉ፡፡

  • የብድር ወለድ

ይህ ደግሞ ከአንድ ግለሰብ ወይም ባንክ የሆነ ያክል ገንዘብ ሲበደር በስምምነታቸው መሰረት ብድሩን እስኪከፍል ድረስ በየዓመቱ ወይም ከዚያ በታች ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ወቅት በስምምነቱ መሰረት (ለምሳሌ 5 ፐርሰንት) እየተጨመረ ታስቦበት የሚከፍለው ጭማሬ ገንዘብ ነው፡፡

ለምሳሌ፡ አንድ ሰው የሆነን የመኖሪያ ቤት በመቶ ሺህ መግዛት ይፈልግና በቂ ገንዘብ አይኖረውም፡፡ ከዚያም ወደ ባንክ ያመራና ለቤቱ መግዢያ ከባንኩ አንድ መቶ ሺህ ይበደራል፡፡ ይኸውም ለአምስት ዓመታት በየወሩ እየተቆራረጠ የሚከፈል ሲሆን መጠኑም አንድ መቶ ሃምሳ ሺ ብር በሚል ስምምነት ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ወለድ የብድር ወለድ ይባላል፡፡

ወለድ ከከባድ ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አባዳሪ በማበደሩ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ከሆነም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡ ብድሩ የንግዱን ዘርፍ ለማጠናከር፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት፣ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት፣ ቤት ለመግዛት፣ ወይም የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችን ለመግዢያ የሚውል ቢሆንም ወለድ ካለው የተከለከለ ነው፡፡

ዕቃዎችን ዋጋቸውን ከተመናቸው በላይ በየጊዜው በካሽ በመክፈል መግዛት ግን ወለድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ መገልገያ መሣሪያን ወዲያው በሚከፈል አንድ ሺህ ዶላር መግዛት ወይም ይህንኑ መሣሪያ ለዕቃው ባለቤት፣ ለሻጩ በየወሩ መቶ ዶላር በመክፈል በአንድ ሺህ ሁለት መቶ ዶላር መግዛት ዓይነት ነው፡፡

የወለድ ፍርድ

ወለድ በጥብቅ የተከለከለ እርም(ሐራም) ነው፡፡ እርምነቱም በግልጽ የቁርኣን አንቀጾችና ሐዲሶች ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ወለድ ከትላልቅ ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከወንጀለኞች መካከል ጦርነትን እንዳወጀበት የዛተው ወለድን በሚበላና በርሱ በሚገለግል ሰው ላይ ብቻ ነው፡፡ የወለድ እርምነት በኢስላም ብቻ ሳይሆን በቀደምት መለኮታዊ መመሪያዎችም ጭምር የተደነገገ ነው፡፡ ነገር ግን ከቁርኣን ውጭ ባሉ መመሪያዎች ውስጥ ያሉት ሕግጋት ድለዛና ክለሳ እንደተደረገባቸው ሁሉ የወለድ ሕግም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የመጽሐፍቱ ባለቤት የሆኑትን ሕዝቦች የቀጣበትንና በነርሱ ላይ የተቆጣበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከርሱ በርግጥ የተከለከሉ ሲሆኑ አራጣንም በመያዛቸውና የሰዎችን ገንዘቦች ያለ አግባብ በመብላታቸው ምክንያት (ረገምናቸው)፡፡›› (አል ኒሳእ 161)

የወለድ ቅጣት

  1. በወለድ የሚገለገል ሰው ከአላህና ከመልክተኛው ጋር ጦርነት በማወጅ እራሱን አጋፍጧል፡፡ በዚህም የአላህ እና የመልክተኛው ተዋጊ ጠላት ይሆናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) አራጣን የሚበሉ ሰዎችን እንዲህ ይላል፡- ‹‹(የታዘዛችሁትን) ባትሰሩም ከአላህና ከመልክተኛው በኾነች ጦር (መወጋታችሁን) ዕወቁ፡፡ ብትጸጸቱም ለናንተ የገንዘቦቻችሁ ዋናዎች አሏችሁ አትበደሉም አትበድሉምም፡፡›› (አል በቀራ 279) ይህ ጦርነት መንፈሳዊና አካላዊ ጫናዎች አሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሰዎችን ያጋጠማቸው አለመረጋጋት፣ ጭንቀት፣ የሃሳብና የትካዜ ፈተና፣ በዚህ ጦርነት ምክንያት የመጣ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ የአላህን ትዕዛዝ በጣሰ ወይም ወለድ በበላ ወይም በወለድ ላይ በተባበረ ሰው ምክንያት የመጣ ጣጣ ነው፡፡ ይህ የዱንያ ወጤቱ ሲሆን ታዲያ የአኼራው የጦርነት ውጤትስ ምን ይሆን?
  2. በወለድ የሚገለገልና ወለድን የሚበላ፣ እንዲሁም በዚህ ላይ እገዛ የሚያደርግ ሰው ከአላህ እዝነት የተባረረና የተረገመ ነው፡፡ ጃቢር(ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡- «የአላህ መልክተኛ ወለድ የሚበላን፣ ወኪሉን፣ ጸሐፊውን፣ ምስክሩንም ጭምር ረግመዋል፡፡» ‹‹ሁላቸውም እነሱ (በወንጀሉ) እኩል ናቸው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ (ሙስሊም 1598)
  3. ወለድ የሚበላ ሰው የትንሳኤ ቀን የሚቀሰቀሰው እጅግ ዘግናኝና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ የአውድቅ በሽታ እንዳለበት፣ በጅን እንደተለከፈ ሰው እየተወላከፈና እየወደቀ ይነሳል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነዚያ አራጣን የሚበሉ ያ ሰይጣን ከመንካቱ የተነሳ የሚጥለው ሰው (ከአውድቁ) እንደሚነሳ ቢጤ እንጂ (ከመቃብራቸው) አይነሱም፡፡›› (አል በቀራ 275)
  4. የወለድ ገንዘብ ምን ቢበዛ ከበረከት የተሟጠጠ ነው፡፡ በወለድ እረፍትን፣ ስኬትንም፣ እርካታና እርጋታንም ማግኘት አይቻልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡›› (አል በቀራ 276)

ወለድ በማህበረሰብና በግለሰቦች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት

ኢስላም በማህበረሰብና በግለሰብ ደረጃ በሚያስከትለው ጉዳትና ክስረት የተነሳ በወለድ ዙሪያ ጠበቅ ያለ አቋም ይዟል፡፡

  1. በሀብት መከፋፈል ተግባር ላይ በሀብታሞችና በድሆች መካካል ልዩነትን ይፈጥራል

ወለድ፣ ገንዘብ ከማህበረሰቡ ውስጥ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ብቻ እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን በርካቶችን የገንዘብ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ በገንዘብ ክፍፍል ላይ ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ ድንበር ባለፈ መልኩ ሃብትን ያከበቱ የጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መፈንጪያ ይሆናል፡፡ የተቀሩት ስራ አጦች፣ ድሆችና ችግረኞች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ቂምን፣ ምቀኝነትንና ወንጀልን ከሚያስፋፉ ምክንያቶች ዋነኛው ነው፡፡

  1. ገንዘብን አለመቆጠብና የአባካኝነት ልማድ

ለአበዳሪ በሚገኝ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የብድር ስርዓት እንዲስፋፋ ነገሮችን ማግራራት፣ ብዙዎች ገንዘብን እንዳይቆጥቡና የአባካኝነት ልማድን እንዲያዳብሩ ያበረታታል፡፡ ምክንያቱም ተበዳሪ ባስፈለገው ጊዜ ገንዘብን በቀላሉ ያገኛል፡፡ በመሆኑም ስላለበትና ስለወደፊቱ አያስብም፡፡ የተበደረውን ገንዘብ በመዝናናትና በትርፍ ነገሮች ላይ ወሰን ባለፈ ሁኔታ ያባክናል፡፡ ብሎም፣ ከፍተኛ የሆነ የብድር ዕዳ ይከማችበትና ሕይወቱ ይጨናነቃል፡፡ ዕድሜ ልኩን በወሰደው ብድርና በተሸከመው እዳ እንደተሸማቀቀ ይኖራል፡፡

  1. ወለድ፣ ባለ ሃብቶች ሀገርን በሚጠቅም ነገር ላይ እንዳይሳተፉ የሚከለክል እንቅፋት ነው፡፡

በወለድ ስርዓት ውስጥ አንድ ባለ ሃብት በገንዘቡ ላይ ተጨማሪ የወለድ ገንዘብ የሚያገኝበት አጋጣሚ ይመቻችለታል፡፡ ይህ ደግሞ ለማህበረሰቡ ምን ያክል ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም፣ ገንዘቡን በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በንግዱ ዘርፎች እንዳያውል ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም፣ እነኚህ ስራዎች ልፋትና ድካምን የሚፈልጉና እንዲሁም የተወሰነ ያክል አደጋ ወይም ክስረት ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በመስራት ፋንታ ገንዘቡን አበድሮ አራጣን መሰብሰብን ይመርጣል፡፡

  1. ወለድ የገንዘብ በረከት እንዲወገድ፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

ማንኛውም በድርጅቶች ወይም በግለሰቦች ላይ የሚከሰት የኢኮኖሚ ውድቀትም ሆነ ከፍተኛ ኪሳራ መንስኤው በተከለከለው ወለድ ላይ መዘውተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አላህ (ሱ.ወ) የተናገረው የበረከት መወገድ አንዱ ውጤት ነው፡፡ ምጽዋትና ለሰዎች መልካም መዋል ግን ገንዘብ እንዲባረክና እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡›› (አል በቀራ 276)

አንድ ሰው ቀደም ሲል በወለድ የሚገለገል የነበረ ቢሆንና ኢስላምን ቢቀበል፣ የሚሰጠው ብይን ወይም ፍርድ ምንድን ነው?

አንድ በወለድ ውል በመገልገል ላይ የነበረ ሰው ኢስላምን ከተቀበለ፣ ፍርዱ ሁለት መልክ የኖረዋል፡፡

  1. 1- እርሱ ጭማሪውንና የሚገኘውን ጥቅም የሚወስድ አበዳሪ የነበረ ከሆነ፣ ኢስላምን ሲቀበል፣ ዋናውን ብቻ ነጥሎ በመውሰድ ጭማሪውን ይተዋል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ብትጸጸቱም ለናንተ የገንዘቦቻችሁ ዋናዎች አሏችሁ፡፡ አትበድሉም አትበደሉምም፡፡›› (አል በቀራ 279)
  2. ጭማሪውን የሚከፍል (ተበዳሪ) ከነበረ ደግሞ፡-
  • ከባድ የሆነ ጉዳት የማያደርስበት ከሆነ ውሉን በማፍረስ ከዚህ ፅልመት መውጣት አለበት፡፡
  • ውሉን ማፍረሱ ትልቅ ኪሳራን የሚያደርስበት ከሆነ ግን፣ ደግሞ ላይመለስበት ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ውሉን እስከተዋዋለበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከጌታውም ግሳጼ የመጣለትና የተከለከለ ሰው ለርሱ (ከመከልከሉ በፊት) ያለፈው አለው፡፡ ነገሩም ወደ አላህ ነው (አራጣ ወደ መብላት) የተመለሰው ሰው እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡›› (አል በቀራ 275)
አንተ ጭማሪ የምትቀበል አበዳሪ ነህን (ወለድ በዪ) ?
አዎን
እንግዲውስ ያለምንም ጭማሪ ገንዘብህን ዋናውን ብቻ መውሰድ ይኖርብሃል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ተበዳሪ ነህ፤ ግን ያለ አንዳች ከባድ ኪሳራ ውሉን ማፍረስ ትችላለህን?
አዎን
ምንም ኪሳራ የማያስከትልብህ ከሆነና የምትችል ከሆነ ውሉን ማፍረስ አለብህ፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ውሉን ማፍረስ የማትችል ከሆነ፣ ወይም በማፍረስህ ምክንያት ትልቅ ጉዳት የሚደርስብህ ከሆነ፣ ደግመህ ላትመለስበት ቁርጠኛ ውሳኔ አድርገህ ውሉን ትጨርሳለህ፡፡