ከወንድ አንጻር ሴቶች ያላቸው ስፍራ
ሴት ለወንድ ከምትሆንለት አንጻር በብዙ ክፍል ትመደባለች፡
- ሴቷ ለወንዱ ሚስት መሆኗ
አንድ ወንድ ሚስቱን በፈለገው መልኩ ማየትና በሷ መርካት ይፈቀድለታል፡፡ ሴትም ከባሏ ጋር እንዲሁው ይፈቀድላታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የመንፈስ ትስስራቸውን፣ የስሜት ውህደታቸውንና የአካል ቅርርባቸውን ሲገልጽ፣ ባልን የሚስት ልብስ ሚስትንም የባል ልብስ በማለት ይገልጻቸዋል፡፡ ‹‹እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡›› (አል በቀራ 187) (ገጽ፣ 204 ተመልከት)
- የቅርብ ዘመዱ (መሕረም) ከሆነች
ከሴቶች መሕረም የሚባሉት፣ አንድ ወንድ ፈፅሞ ሊያገባቸው የማይችሉ የሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡
1 | ወላጅ እናትና አያት፤ አያትነቱ ቢረዝምም ቢያጥርም አንድ ነው፡፡ |
2 | የራሱን ሴት ልጅ፣ የወንድ ልጁ ሴት ልጅ፣ የሴት ልጁ ሴት ልጅ፤ የልጅ ልጅነታቸው ምንም ያክል ቢወርድም እርምነቱ ያው ነው፡፡ |
3 | የእናት አባቱ ልጅ እህቱ፣ በአባት የሚገናኙ እህቱ፣ ወይም በእናት የሚገናኙ እህቱ፤ |
4 | የአባቱ እህት አክስቱ፤ ለአባቱ እህትነቷ በአባትም በእናትም ቢሆንም በአባት ብቻ ወይም በእናት ብቻም ቢሆንም ልዩነት የለውም፡፡ የአባት አክስትና የእናት አክስትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡ |
5 | የእናቱ እህት የሹሜው፤ ለእናቱ እህትነቷ በአባትም ሆነ በእናትም ቢሆን፣ በአባት ወይም በእናት ብቻም ቢሆን ልዩነት የለውም፡፡ የአባት አክስትና የእናት አክስትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡ |
6 | የወንድሙ ሴት ልጅ፤ ወንድምነቱ በእናትም በአባትም፣ ወይም በእናት ብቻ፣ ወይም በአባት ብቻ ቢሆንም ልዩነት የለውም፡፡ |
7 | የወንድም ወንድ ልጅ ሴት ልጅን ይመስል የልጅነት ሐረጓ ቢወርድም ፍርዱ ያው ነው፡፡ |
8 | የሚስቱ እናት፡ ሚስቱ አብራው ብትሆንም ወይም ቢፈታትም እናቷ እስከመጨረሻው መሕረምነቷ ይቆያል፡፡ ልክ እንዲሁ የሚስት እናት እናት ወይም የሚስት አያትም ከዚሁ ትመደባለች፡፡ |
9 | ከርሱ የማትወለድ የሚስቱ ሴት ልጅ |
10 | የልጅ ሚስት ወደ ታች የሚወለድ ቢሆንም ለምሳሌ እንደ ልጅ ልጅ ሚስት |
11 | ወደ ላይ ከፍ ቢልም የአባት ሚስት ወይም ልክ እንደ የልጅ ሚስት በአባት በኩል |
12 | የጡት እናቱ፡ የጡት እናት ማለት በሁለቱ የመጀመሪያ የአራስነት ዓመታት ወቅት ውስጥ አምስት ጊዜ ጠግቦ የጠባት ሴት ናት፡፡ እርሱን በማጥባቷ ምክንያት ኢስላም ለርሷ በርሱ ላይ መብት ደንግጎላታል፡፡ |
13 | የጡት እህቱ፡ ይህች ደግሞ እርሱን ያጠባችው ሴት ልጅ ናት፡፡ በዚሁ መልክ፣የጡት አክስት የጡት ወንድም ልጅ የጡት እህት ልጅና የመሳሰሉት ሁሉም የጡት ዘመዶች ልክ የደም ትስስር እንዳላቸው ዘመዶች እርም ይሆናሉ፡፡ |
- ሴቷ ለርሱ ባዕድ ከሆነች
ባዕድ ሴት የምትባለው ከተጠቀሱት መሓሪሞች ውጭ ያለች ሴት ሁሉ ነች፡፡ ከርሱ ጋር ዝምድና ያላቸው ቢሆኑም፣ እንደ አጎት ልጅ፣ የአክስት ልጅ፣ የወንድሙ ሚስት፣ ወይም ከርሱ ጋር ዝምድና የሌላቸው ቢሆንም ከርሱ ጋር የሚያስተሳስራቸው የዘር ሐረግ ወይም የአማችነት ትስስር ባይኖርም በኢስላም እይታ አጅነቢ ወይም ባዕድ ናቸው፡፡
በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከእምነት አስተምህሮ በራቁ ቤተሰቦችና ማህበረሰብ ውስጥ የአስገድዶ መድፈርና ፀያፍ የወንጀል ስራዎች በሰፊው ተስፋፍተዋል፡፡
በእርግጥ ኢስላም አንድ ሙስሊም ከባዕድ ሴት ጋር ሊኖረው የሚገባን ግንኙነት ሥርዓትና መመሪያ አድርጎለታል፡፡ ይህ ደግሞ ክብርን የሚጠብቅና የሰይጣን በሮችን የሚዘጋ ነው፡፡ የሰው ልጅን የፈጠረው አላህ(ሱ.ወ)፣ ለርሱ የሚበጀውን ከማንም በላይ ያውቃል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ሚስጥርን ሁሉ) አያውቅምን?›› (አል ሙልክ 14)
በወንድና በባዕድ ሴት መካከል የሚኖር ግንኙነት ስርዓት
- ዓይንን መስበር
አንድ ሙስሊም የሌላ ሰውን ሀፍረተ ገላ ማየት አይፈቀድለትም፡፡ የፍቶት ስሜቱን የሚቀሰቅሱ ነገሮችንም መመልከትም የተከለከለ ነው፡፡ ያለ ጉዳይ አንዲትን ሴት አተኩሮ ማየት የለበትም፡፡ አላህ ሱ.ወ) ሁለቱንም ጾታዎች ዓይናቸውን ሰበር እንዲያደርጉ አዟቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ የጥብቅነትና የጨዋነት ጎዳና በመሆኑ ነው፡፡ ዓይንን ያለ ገደብ እንደፈለጉ መልቀቅ የዝሙትና የወንጀል መንገድ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለምዕመናን ንገራቸው ዓይኖቻቸውን ያልተፈቀደን ከማየት ይከልክሉ፤ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ ይህ ለነሱ የተሻለ ነው፤ አላህ በሚሰሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡ ለምእመናትም ንገራቸው ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡›› (አል ኑር 30-31)
በድንገት የተከለከለን ነገር ለማየት የተጋለጠ ሰው ወዲያው ከዚያ እይታ ዓይኑን ሰበር ማድረግ አለበት፡፡ ዓይንን መስበር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በኢንተርኔት ከሚሰራጩ የተከለከሉ ነገሮችንም ያካትታል፤ የፍትወት ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን መመልከት ክልክል ነው፡፡
- በስርዓትና በመልካም ስነምግባር አብሮ መኖር
ስርዓትን በጠበቀና መልካም ስነ ምግባርን በተላበሰ መልክ፣ ከማንኛውም ስሜት ቀስቃሽ ነገሮች ርቀው አንዲት ባዕድ ሴትን ቢያናግር፣ እሷም ብታናግረው፣ ማሕበራዊ ሕይወታቸውን ቢመሩ አይከለከልም፡፡
- አላህ(ሰ.ወ) ሴቶች ባዕድ ወንዶችን ሲያናግሩ ድምፃቸውን እንዳያስለመልሙ ከልክሏል፡፡ ግልጽ የሆነ ንግግርን እንዲናገሩም አዟል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያ በልቡ በሽታ ያለበት እንዳይከጅል በንግግር አትለስልሱም መልካምንም ንግግር ተናገሩ፡፡›› (አል አሕዛብ 32)
- ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ አረማመዶች፣ እንቅስቃሴዎችና ከጌጦችም ከፊሎቹን ግልጽ ማድረግ የተከለከሉ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ሴቶችን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከጌጦቻቸው የሚሸፍኑት ይታወቅ ዘንድ በእግሮቻቸው አይምቱ፡፡›› (አል ኑር 31)
- የኸልዋ (ለብቻ መነጠል) እርምነት
ኸልዋ ማለት አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ማንም በማያያቸው ስፍራ ላይ ለብቻቸው መገኘት ሲሆን ይህንን ኢስላም እርም አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም፣ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ፣ ዝሙትና ፀያፍ ተግባራት እንዲፈፀሙ የሚያደርግበት የሸይጣን መግቢያ በር በመሆኑ ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አድምጡ! ከእይታ በራቀ ቦታ ላይ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር አይነጠልም ሦስተኛቸው ሰይጣን ቢሆን እንጂ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2165)
- አል ሒጃብ (የሴቶች ኢስላማዊ አለባበስ)
አላህ (ሱ.ወ) በሴቶች ላይ ሂጃብን ግዳጅ ያደረገው ማራኪ ውበትና አታላይ ተክለ ሰውነት ያላበሳቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯቸው ደግሞ ለወንዶች ፈታኝነቱ፣ ወንዶች ለሴቶች ካላቸው ተፈጥሯዊ ፈታኝ ገጽታ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
አላህ (ሱ.ወ) ሂጃብን የደነገገው ለብዙ ዓላማ ነው፡
- ሴት የተፈጠረችለትን ዓላማና የተጣለባትን ማህበረሰባዊ ኃላፊነት፣ በዕውቀትም በተግባርም በብቃትና በጥራት እንድትወጣ እንዲሁም ክብሯንና ጨዋነቷን ጠብቃ እንድትኖር ለማድረግ ነው፡፡
- የዋልጌነትና የጋጠወጥነት መንስኤዎችን በመቀነስና በማዳከም በአንድ በኩል የማህበረሰቡን ጽዱዕነት በሌላም በኩል የሴትን ክብር ለማስጠበቅ ነው፡፡
- ወደሴቶች ለሚመለከቱ ወንዶች በጥብቅነትና ስሜትን በመቆጣጠር ላይ ማገዝ፤ ይኸውም እንደማንኛውም የእድገትና የልማት አጋር ከሴቶች ጋር እንዲረዳዱና እንዲተጋገዙ ያደርጋል፡፡ የቅጽበታዊ ስሜት ማርኪያ የፍቶት ስሜት ቀስቃሽ ብቻ አድርገው እንዳይመለከቷት ለማድረግ ያስችላል፡፡
የሂጃብ ይዘት
አላህ (ሱ.ወ) ሴት ልጅ በባዕድ ወንዶች ፊት ከፊቷና ከመዳፎቿ በስተቀር ሰውነቷን በሙሉ እንድትሸፍን ግዴታ አድርጓል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጌጣቸውንም ከርሷ ግልጽ የኾነውን በስተቀር አይግለጡ፡፡›› (አል ኑር 31)
ግለጽ የኾነ የሚባለው ፊትና መዳፍን ነው፤ እሱም ቢሆን፣ ፊትና መዳፍን በመገለጥ የሚከሰት ፈተና ወይም ችግር ካለ መሸፈናቸው ግድ ይሆናል፡፡
የሒጃብ ስርዓተ ደንብ
አንዲት ሴት የሚከተሉትን ቅድመ መስፈርቶች በጠበቀ መልክ የፈለገችውን ዓይነት መልክና ይዘት ያለው ሒጃብ ወይም ልብስ መልበስ ይፈቀድላታል፡፡
- ሒጃቡ የግድ መሸፈን ያለበትን የሰውነት ክፍል በጠቅላላ የሚሸፍን መሆን አለበት
- ሰፊ መሆን አለበት፤ የሚያጣብቅ፣ ጠባብ፣ የሰውነትን ቅርጽ የሚያወጣና የሚያሳይ መሆን የለበትም፡፡
- ወፍራም መሆን አለበት፡፡ ስስነቱ በስሩ ያለን የሰውነት ክፍል የሚያጋልጥና የሚያሳይ መሆን የለበትም፡፡