ጋብቻ በኢስላም

 ጋብቻ ኢስላም ልዩ ትኩረት ከቸራቸው ማህበራዊ ጉዳዮች አንዱ ነው .

ጋብቻ ኢስላም ልዩ ትኩረት ከቸራቸውና ካበረታታቸው ማህበራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ የነብያት ፈለግም ነው፡፡ (ገጽ፣ 196 ተመልከት)

ኢስላም ለጋብቻ ዝርዝር ድንጋጌና ስርዓትን በመዘርጋት ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ የባለ ትዳሮች መብት መከበር የጋብቻው ግንኙነት እንዲጎለብትና እንዲረጋ ያደርጋል፡፡ በመንፈስ የተረጋጋ፣ በእምነቱ የጸና፣ በሁሉም የማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ የመጠቀ፣ ሕፃናት በውስጡ የሚያድጉበት የሆነን ስኬታማ ቤተሰብ ለመመስረት ያስችላል፡፡

 

ከነኚህ ኢስላማዊ ድንጋጌዎች መካከል፡

ኢስላም ለአንድ ጋብቻ ትክክለኛነት በባልም ሆነ በሚስት በኩል የግድ ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶችን አስቀምጧል፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ኢስላም ለሚስትነት ያስቀመጣቸው መስፈርቶች፡

  1. ሙስሊም፣ ወይም የመጽሐፍት ባለቤት ማለትም አይሁድ ወይም ክርስቲያን መሆን አለባት፡፡ ይሁን እንጂ ኢስላም ከሙስሊሟም ቢሆን በሃይማኖቷ ጠንካራዋን እንድንመርጥ ይመክራል፡፡ ምክንያቱም ወደፊት ለልጆችህ እናትና ተንከባካቢ፣ ለአንተ ደግሞ በመልካም ነገር ላይ የምታግዝህና የምታጸናህ እሷ በመሆኗ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ባለ ሃይማኖቷን ምረጥ አለያ እጅህ አመድ አፋሽ ትሆናለች›› (አል ቡኻሪ 4802 / ሙስሊም 1466)
  2. ጥብቅና ጨዋ መሆን አለባት፡፡ በዝሙትና በእንዝላልነት የምትታወቅ ሴትን ማግባት ክልክል ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከምእመናት ጥብቆቹም ከነዚያ ከናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም (ተፈቀዱላችሁ)›› (አል ማኢዳ 5)
  3. ለዘላለሙ ሊያገባቸው እርም ከተደረጉ መሐሪሞቹ መካከል መሆን የለባትም፡፡ የዚህን ዝርዝር ማብራሪያ ከዚህ በፊት አሳልፈናል፡፡ በጋብቻው አንዲት ሴትን ከእህቷ ወይም ከአክስቶቿ ማለትም ከአባቷ እህት ወይም ከእናቷ እህት ጋር በአንድ ላይ ማግባት አይፈቀድለትም፡፡ (ገጽ፣ 200 ተመልከት)

ኢስላም ለባልነት ያስቀመጣቸው መስፈርቶች፡

ባል ሙስሊም መሆን አለበት፡፡ በኢስላም፣ ሙስሊም ሴትን ሃይማኖቱ የመጽሐፍ ተከታይ (አህለል ኪታብ) ወይም መጽሐፍ የለሽ ቢሆንም ለካሃዲ መዳር የተከለከለ ነው፡፡ ኢስላም አንድን ወንድ በባልነት ለመቀበል ወንዱ ሁለት ባህሪዎችን የተላበሰ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡

  • በሃይማኖቱ ጽኑ መሆኑና
  • መልካም ስነ ምግባር የተላበሰ በሆኑ ናቸው፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሃይማኖቱንና ስነምግባሩን የምትወዱለት ልጃችሁን ከጠያቃችሁ አጋቡት፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1084 / ኢብኑ ማጃህ 1967)

የባልና የሚስት መብቶች

አላህ (ሱ.ወ) በባልም በሚስትም ላይ ሊጠብቁት የሚገባ የሆነ መብት ሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም የጋብቻን ሕይወት የሚያሳምሩና የሚጠብቁ ነገሮችን በሙሉ እንዲፈፅሙ አነሳስቷል፡፡ እነኚህን ጉዳዮች የመጠበቅ ኃላፊነት በሁለቱም ወገን ላይ የተጣለ ነው፡፡ ባልም ሆነ ሚስት አንዳቸው ከሌላኛው የማይቻልን ነገር እንዲፈፅም መጠየቅ የለባቸውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ለነርሱም (ለሴቶች) የዚያ በነርሱ ላይ ያለባቸው (ግዳጅ) ብጤ በመልካም አኗኗር (በባሎቻቸው ላይ መብት) አላቸው፡፡›› (አል በቀራ 228) የሕይወት ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው አና የተከበረው ቤተሰብ እንዲጸና ነገርን ማግራራትና ጉድለትን ማለፍ እንዲሁም መለገስ ያስፈልጋል፡፡

የሚስት መብቶች

  1. ቀለብና መጠለያ
  • ሚስት ባለ ሃብት ብትሆንም እንኳ፣ ባል ለሚስቱ የምግቧን፣ የመጠጧን፣ የልብሷንና የአስፈላጊ ጉዳዮች ወጪዋን የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ እንዲሁም ለርሷ ተመጣጣኝ የሆነን መኖሪያ ወይም ማረፊያም ሊያዘጋጅላት ይገባል፡፡
  • የወጪ መጠን፡ ወጪ የሚለካው እንደ ባልየው የገቢ መጠንና እንደየ አገሩ የአኗኗር ዘይቤ ሲሆን፣ ማባከንም ሆነ መጨናነቅ የሌለበት ሊሆን ይገባል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የችሎታ ባለቤት ከችሎታው ይቀልብ፤ በርሱም ላይ ሲሳዩ የተጠበበት ሰው፣ አላህ ነፍስን የሰጣትን እንጅ አያስገድዳትም፡፡›› (አል ጠላቅ 7)
  • ይህን ወጪ ሲሸፍን መመጻደቅ፣ እንዲሁም በመጨናነቅ እሷንም ሆነ እራሱን ማዋረድ የለበትም፡፡ ገንዘብ ሲያወጣ፣ አላህ (ሱ.ወ) በገለጸው መልኩ በመልካም እሳቤ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ ሚስት በባሏ ላይ ያላት መብት እንጂ እርሱ በቸርነቱ የለገሳት አይደለም፤ እናም መብቷን በአግባቡ ሊጠብቅላትና ሊሰጣት ይገባል፡፡
  • በኢስላም፣ በሚስትና በቤተሰብ ላይ የሚወጣ ወጪ ከባድ ምንዳን ያጎናጽፋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ሙስሊም ከአላህ እመነዳበታለሁ በሚል እሳቤ በሚስቱ ላይ ወጪ ሲያወጣ ለርሱ ምጽዋት ይሆንለታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 5036 /ሙስሊም 1002) በሌላም ዘገባ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በርሷ ብትመነዳባት እንጂ አንተ የአላህን ፊት ከጃይ ሆነህ አንድም ወጪን አታወጣም፤ በሚስት አፍ ውስጥ የምታስቀምጣት ጉርሻ እንኳን ብትሆን፡፡›› (አል ቡኻሪ 56 /ሙስሊም 1628) ወጪ አልሰጥም ያለ ሰው፣ ወይም እየቻለ ማውጣት ካለበት የቀነሰ ሰው፣ በርግጥ ከባድ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ለአንድ ሰው ወንጀለኛነት፣ የሚያስተዳድረውን ሰው ማንገላታቱ ይበቃዋል፡፡›› (አቡ ዳውድ 1692)
  1. መልካም አኗኗር ወይም ግንኙነት

መልካም አኗኗር በሚለው የተፈለገው መልዕክት መልካም ስነ ምግባር የሚለው ነው፡፡ ልበ ለስላሳነት፤ ለብ ያለ ንግግርን መናገር፤ አንድም የሰው ልጅ ሊርቃቸው የማይችሉ ስህተቶችንና ድክመቶችን ችሎ ማለፍና የመሳሰሉትን ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በመልካምም ተኗኗሩዋቸው፤ ብትጠሉዋቸውም (ታገሱ)፤ አንዳችን ነገር ልትጠሉ፣ አላህም በርሱ ብዙ ደግ ነገርን ሊያደርግ ይቻላልና፡፡›› (አል ኒሳእ 19)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከሙእሚኖች መካከል የተሟላው ሙእሚን በስነ ምግባሩ በላጭ የሆነው ነው፤ በላጮቻችሁ ለሚስቶቻቸው በስነ ምግባራቸው ጥሩዎቹ ናቸው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1162)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህም ብለዋል፡- ‹‹ከሙእሚኖች መካከል የተሟላው ሙእሚን በስነ ምግባሩ ጥሩውና ለሚስቱ ገራገር የሆነው ነው፡፡››

(አል ቲርሙዚ 2612 / አህመድ 24677)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በላጫችሁ ለቤተቡ ጥሩዋችሁ ነው፤ እኔ ለቤተሰቤ ጥሩዋችሁ ነኝ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 3895) አንድ ሠሐቢይ፣ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ)፡- «አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ የአንዳችን ሚስት በሱ ላይ ያላት መብት ምንድን ነው?» በማለት ጠየቃቸው፤ እሳቸውም፡ ‹‹ስትበላ ልታበላት፤ ስትለብስም ልታለብሳት፤ ፊቷን ላትመታት፤ ላታዋርዳት፤ በቤትህ ውስጥ እንጂ ላታኮርፋት ነው፡፡›› አሉት፡፡ (አቡ ዳውድ 2142)

  1. መቻቻል

የሴቶች ተፈጥሯዊ ባህሪ ከወንዶች ጋር ይለያያል፤ በመሆኑም ይህን የሚለዩባቸውን ባህሪያት ወንዱ ሊላመደውና አቅልሎ ሊመለከተው ይገባል፡፡ የጋብቻን ሕይወት ከብዙ አቅጣጫ ለማየት ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ማንም ከስህተት ነፃ አይደለም፤ እናም ስህተት ሲከሰት ትዕግስት ማድረግና ከስህተቱ ባሻገር ያሉትን መልካም ጎኖች መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ ባልንም ሚስትንም፣ አንዱ የሌላኛውን መልካም ወይም ጠንካራ ጎን እንዲመለከቱ ያሳስባል፡፡ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በመካከላችሁም ችሮታን አትርሱ፡፡›› (አል በቀራ 237)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ለሴቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸውና ወንዶች በመልካም እንዲኗኗሯቸው አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም የሴቶች መንፈሳዊና ስጋዊ ባህሪያቸው ከወንዶች ጋር እንደሚለያይ ተናግረዋል፡፡ ይህ የባህሪ ልዩነት ለአንድ ቤተሰብ መደጋገፊያና ውበት መሆኑንም አስተምረዋል፡፡ እናም ይህ የባህሪ ልዩነት የመለያየትና የፍቺ መንስኤ ሊሆን አይገባም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሴት የተፈጠረችው ከጎን አጥንት ነው፤ በምንም ጉዳይ ላይ ላንተ አትስተካከልልህም፤ በሷ ልትጠቀም ከፈለግህ ከነጉብጠቷ ልትጠቀምባት ትችላለህ፤ ለማቃናት ከሞከርክ ግን ትሰብራታለህ፤ ስብራቷም መፈታቷ ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 3153 / ሙስሊም 1468)

  1. ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም

አንድ ሰው ከሚስቱ ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም፡፡ ቢያንስ በአራት ቀናት አንዴ ይህንን ሊፈፅም ይገባል፡፡ ከአንድ በላይ ያገባ ከሆነም የሳምንቱ ቀናቶችን በእኩልነት በሚስቶቹ መካከል ሊከፋፍል ይገባል፡፡

  1. ክብርህና ሞገስህ ስለሆነች ልትከላከላት ይገባል፡፡

አንድ ሰው ሲያገባ፣ ያገባት ሴት የእርሱ ክብሩ ነች፡፡ ስለሆነም ለሞት የሚዳርገው ቢሆንም እንኳን ይህን ክብሩን ሊከላከልና ሊሟገትለት ይገባል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ስለ ሚስቱ የተገደለ ሰው ሰማዕት ነው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1421/ አቡ ዳውድ 4772)

  1. የሚስትን ሚስጥር አለማባከን

አንድ ሙስሊም፣ የሚስቱን ልዩ ባህሪያትና፣ በርሱና በርሷ መካከል ስለ ተፈፀመ የአልጋ ላይ ሚስጥር ለሰዎች ሊያወራ አይፈቀድለትም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የትንሳኤ ቀን ከሰዎች ሁሉ ከደረጃ በኩል የከፋ ሰው ማለት፣ እርሱ ለሚስቱ ተገላልጦ፣ ሚስቱም ለርሱ ከተገላለጠች በኋላ የሷን ሚስጥር አውጥቶ የሚበትን ሰው ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 1437)

  1. በሴት ላይ ድንበር ማለፍ አይፈቀድም

ኢስላም ለሚፈጠሩ ችግሮች በርካታ መፍትሄዎችን አስቀምጧል፡፡ ከነዚህም መካከል፡

  • ስህተቶች በመወያየት፣ በመመካከርና በተግሳጽ ሊታረሙ ይገባል፡፡
  • ከሦስት ቀናት ላልበለጠ ጊዜ አለማናገር ወይም ማኩረፍ ከዚያም ከቤት ሳይወጣ በመኝታና በግብረ ስጋ ግንኙነት ማኩረፍ ይፈቀድለታል፡፡
  • እመት ዓኢሻ እንዲህ ብለዋል፡- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በአላህ መንገድ ላይ ሲዋጉ ካልሆነ በስተቀር አንዲትንም ሴት ሆነ ባሪያ መራቅ አያውቁም፡፡
  1. ማስተማርና መምከር

ሰውየው ሚስቱን በመልካም ሊያዛትና ከመጥፎ ሊከለክላት ይገባል፡፡ ወደ ጀነት ጸጋ የሚያዳርሳቸውን፣ ከእሳት ቅጣት የሚያርቃቸውን ነገሮች በማመቻቸትና በሱም ላይ በማበረታታት፣ እንዲሁም እርም ነገሮችን በመከልከልና እንዲጠሉ በማድረግ ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ሚስትም ባሏን በመምከር፣ ወደ መልካም ነገር በመገፋፋትና በመጠቆም፣ ልጆችን በጥሩ ስነ ምግባር ኮትኩቶ በማሳደግ ላይ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ከእሳት ጠብቁ፡፡›› (አል ተህሪም 6) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሰውየው በሚስቱ ላይ ጠባቂ ነው፣ ስለጠበቀው ነገር ይጠየቃል፡፡›› (አል ቡኻሪ 2416 /ሙስሊም 1829)

  1. ሚስቱ ያስገባችውን ቃል መጠበቅ

ጋብቻው በሚፈፀምበት ጊዜ፣ ሚስት ለምሳሌ፣ ይዘቱ ለየት ያለ ቤትን ሊገዛላት ወይም ሊሰራላት ዓይነት የተፈቀዱ ነገሮችን እንዲፈፅምላት ቃል ካስገባችው፣ ቃሉን የመጠበቅና የመሙላት ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም የጋብቻ ውል ከቃልኪዳኖች ሁሉ ትልቁና ከባዱ በመሆኑ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከመስፈርቶች ሁሉ እጅግ በርሱ ልትሞሉ የሚገባው ብልትን የተፈቀደ ያደረጋችሁበት ቃል ኪዳን ወይም መስፈርት ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 4856 /ሙስሊም 1418)

የባል መብቶች

  1. በመልካም ነገር ላይ እሱን የመታዘዝ ግዴታ አለባት

አላህ (ሱ.ወ) ወንድን በሴት ላይ የበላይ አስተዳዳሪ አድርጎታል፡፡ ይኸውም ልክ የአገር መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ለሕዝብ እንደሚያገለግሉት፣ ጉዳይዋን የሚያስፈፅምላት፣ መስመር የሚያስይዝላትና የሚከታተልላት እሱ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አላህ (ሱ.ወ) ለወንድ ልዩ መገላጫዎችን የሰጠው በመሆኑና በንብረት የማስተዳደር ኃላፊነት በሱ ላይ የተጣለ በመሆኑ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወንዶች በሴቶች ላይ ቋሚዎች (አሳዳሪዎች) ናቸው፤ አላህ ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ በማብለጡና (ወንዶች) ከገንዘባቸው (ለሴቶች) በመስጠታቸው ነው፡፡›› (አል ኒሳእ 34)

  1. ባሏ እንዲረካባት መዘገጃጀት ወይም መመቻቸት

ባል በሚስቱ ላይ ካለው መብቶች አንዱ፣ እርሱ ግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲፈፅም እራሷን ማመቻቸትና እንዲረካባት ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ሆን ብላ ለርሱ መቆነጃጀትና መዘገጃጀት ይወደድላታል፡፡ የወር አበባ ደም ላይ መሆን፣ ወይም የግዳጅ ጾም ላይ መሆን፣ ወይም በህመምና በመሳሰሉት ሸሪዓዊ ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር፣ ሚስት ባሏ ሊገናኛት እየፈለገ ወይም ሲጠራት ፈቃደኛ ካልሆነች እጅግ በጣም ትወገዛለች፤ ከባድ ወንጀልንም ትሸከማለች፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ሰው ሚሰቱን ወደ ፍራሹ ሲጠራት እንቢተኛ ከሆነችና ተቆጥቶባት ወይም ተከፍቶባት ካደረች እስኪነጋ ድረስ መላእክት ይረግሟታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 3065 /ሙስሊም 1436)

  1. ባል ወደቤቱ እንዲገቡ የማይፈልጋቸውን ሰዎች እንዲገቡ አለመፍቀድ

ባል በሚስቱ ላይ ካለው መብቶች መካከል ሚስት እርሱ ከሚጠላቸው ሰዎች አንዱንም አለማስገባት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዲት ሴት በርሱ ፍቃድ ካልሆነ በስተቀር ባሏ እያለ ልትጾም አይፈቀድላትም፤ በሱ ፍቃድ ካልሆነ በስተቀር በቤቱ ውስጥ ሰው እንዲገባ መፍቀድ የለባትም፡፡›› (አል ቡኻሪ 4899)

  1. በባል ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት

ባል በሚስት ላይ ካሉት መብቶች አንዱ ያለርሱ ፍቃድ ከቤት አለመውጣት ነው፡፡ ልዩ ቦታ ለመሄድ መውጣቷም ይሁን ለስራ ጉዳይ መውጣቷ ሁለቱም አንድ ነው፡፡ ያለ ባል ፈቃድ አይሆንም፡፡

  1. ሚስት ባሏን መንከባከብ

ሚስት ባሏን በሀገሬው ተለምዶ መሰረት ምግብ በማዘጋጀትና መሰል በሆኑ በቤት ውስጥ ጉዳዮች ልትንከባከበው ይገባል፡፡