የዚህ ዓለም ታላቅ ፀጋ
ኃያሉ አላህ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፀጋዎችን ለሰው ዘር አጎናፅፏል፡፡ ሁላችንም እነዚህን የአላህ ፀጋና ትሩፋቶች ከማጣጣም ለአፍታም ተቆጥበን አናውቅም፡፡
ከጎደሎ ባህሪያት የጠራው ጌታ ብዙዎች ያጡትን የማየትና የመስማት ታላቅ ፀጋን ችሮናል፡፡ አዕምሮን፣ ጤናን፣ ገንዘብን፣ ቤተሰብን ያለክፍያ ሰጥቶናል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ እኛን ያገለግል ዘንድ ገርቶናል፡፡ ፀሐዩ፣ ሰማዩ፣ መሬቱ፣ ፍጥረታቱ ሁሉ የእኛ አገልጋይ ተደርገዋል፡፡ «የአላህንም ፀጋ ብትቆጥሩ አትዘልቋትም፤ አላህ በእርግጥ መሐሪ አዛኝ ነውና፡፡» /አል-ነሕ፡18/
ይህም ሆኖ አጭሩ የዕድሜ ገደባችን ሲጠናቀቅ እነዚህ ፀጋዎችም አብረው ያከትማሉ፡፡
በዚህ ዓለም /ዱንያ/ ላይ ደስታና ዕርካታን አጎናፅፎ እስከቀጣዩ ዓለም /አኼራ/ ድረስ የሚሸጋገር አንድና ብቸኛ ፀጋ ግን አለ፡፡ እርሱም ወደ ኢስላም ጎዳና የመመራት ፀጋ ነው፡፡ ይህ አላህ ለባሮቹ ያጎናፀፈው ታላቅ ፀጋ ነው፡፡
ይህ በመሆኑም ነው፥ አላህ ከሌሎች ፀጋዎች አስበልጦ ይህንን ፀጋ ወደ ራሱ ያስጠጋው፡፡ እንዲህ ይለናል «… ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፤»/አል-ማኢዳህ፡3/
አንድን ሰው ከጨለማዎች ወደ ብርሃን በማውጣትና እርሱ ወደ ወደደው ሃይማኖት ከመምራት የበለጠ ታላቅ ፀጋ አላህ ለሰው ልጅ አጎናፅፎዋልን?! አላህ ለሰው ይህን ፀጋ የቸረው፥ በህይወት የተገኘበት ዋንኛ ዓላማ የሆነውን አላህን የመገዛት ተልዕኮ በአግባቡ ያሳካ ዘንድ ነው፡፡ ሰው ይህን በማድረጉ በዚህ ዓለም ላይ ደስታን ሲያገኝ በቀጣዩ ዓለም ደግሞ የማይቋረጥ ምንዳ ይጠብቀዋል፡፡
አላህ ከሰዎች ሁሉ የበለጥን ምርጥ ህዝቦች እንድንሆን አድርጎ በመምረጥ፥ ሰላም በነርሱ ላይ ይሁንና የነቢያትና የመልእክተኞች ሁሉ ጥሪ የሆነውን «ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም» የሚለውን ኃይለ-ቃል እንድናነግብ ማድረጉ ለእኛ ታላቅ ፀጋ ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ፀጋና በረከትስ ይኖራል?
አንዳንድ አላዋቂ ሰዎች ሙስሊም የሆኑት በፍፁም ፈቃዳቸው ብቻ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር በነቢዩ ሙሐመድ /ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን/ ላይ አጉል ለመመፃደቅ ሲዳዳቸው፥ አላህ ተችቷቸዋል፡፡ ወደዚህ ሃይማኖት ጎዳና መመራት የሚቻለው በርሱ ፀጋ ብቻ መሆኑን ገልፆላቸዋል፡፡ እንዲህ ይላል አላህ …«በመስለማቸው፤ በእስልምናችሁ በኔ ላይ አትመጣደቁ፤ ይልቁንም አላህ ወደ እምነት ስለመራችሁ ይመጣደቅባችኋል፤ እውነተኞች ብትኾኑ (መመጣደቅ ለአላህ ነው) በላቸው፡፡» (አል-ሐሹራት፡17)
በእርግጥ የኃያሉ አላህ ፀጋዎች ብዙ ናቸው፡፡ እንደዚህም ሆኖ በስም ጠቅሶ ያወሳውና ለእኛ እንዳጎናፀፈን የነገረን አንድና ብቸኛ ፀጋ ወደ ኢስላም ጎዳና መመራት፣ እርሱን መገዛትና አንድነቱን በተግባር ማረጋገጥ ነው፡፡
ይህ ፀጋ ከእኛው ጋር ቋሚና ዘውታሪ ሆኖ እንዲቆይ፥ ምስጋና ያስፈልገዋል፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል… «ጌታችሁም ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ፥ በትክዱም /እቀጣችኋለሁ/፤ ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና በማለት ባስታወቀ ጊዜ /አስታውሱ/፡፡»(ኢብራሂም፡7)
ይህን ፀጋ ማመስገን የሚቻለው እንዴት ነው?
ማመስገን የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው፡-
በሃይማኖት ላይ በመፅናትና በርሱ ምክንያት ችግር ሲገጥም በመታገስ (ገጽ፣ 229 ተመልከት)
ጥበብና ትዕግስት በተሞላው አኳኋን እስልምናን በማስተዋወቅና ወደርሱ በመጣራት ነው፡፡ (ገጽ፣ 230 ተመልከት)