እስልምና ሚዛናዊ ሃይማኖት ነው፡-

እስልምና ከመጠን በላይ አለማክረርና አለማካበድን እንዲሁም ከደረጃ በታች አለመውረድና አለመለስለስን መለያው አድርጎ የተደነገገ ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ መለያው በሁሉም ሃይማኖታዊና አምልኮአዊ መርሆቹ ውስጥ ጎልቶ ይንፀባረቃል፡፡

አላህ (ሱ.ወ.) ለመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ለሰሀቦችም ሆነ ለምእመናን ሚዛናዊ ይሆኑ ዘንድ በማስገንዘብ አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ይህም በሁለት መንገዶች ሊገለፅ ይችላል፡-

በሃይማኖት ጎዳና ላይ በመፅናትና በልብ ውስጥ ለአላህ ሕግጋቶች ከፍተኛ ቦታ በመስጠትና፡፡

ከአክራሪነት፣ ከድንበር አላፊነትና ከጠርዘኝነት በመከልከል ናቸው፡፡

ኃያሉ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ «እንደታዘዝከውም ቀጥ በል፤ ከአንተ ጋር ያመኑትም (ቀጥ ይበሉ)፤ ወሰንንም አትለፉ፤ እርሱ የምትሰሩትን ሁሉ ተመልካች ነውና፡፡»(ሁድ፡112)

ጌታችን በዚህ አንቀፅ ለማለት የፈለገው በእውነት ላይ በመፅናት ብዙም ሳታካብዱና አላስፈላጊ ነገሮችን በመጨማመር ድንበር አላፊ ሳትሆን ለዚሁ እየታገልክ ኑር ነው፡፡

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) በአንድ ወቅት የእምነት ባልደረባቸውን (ሰሀባቸውን) ስለ ሐጅ ተግባራት ሲያስተምሩት፥ ያለፉት ህዝቦች ለጥፋት ሊዳረጉ የቻሉት ድንበር በማለፍ መሆኑን በማውሳት፥ ሰሀቢው ከማካበድ ተግባር እንዲቆጠብ አስገንዝበውታል፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት…«አደራችሁን! በሃይማኖት ውስጥ ማካበድን ተጠንቀቁ፥ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ህዝቦች ለጥፋት የዳረጋቸው ማካበድ ነው፡፡» (ኢብን ማጃህ፡3029)

ለዚህ ነው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) «አደራችሁን አቅማችሁ በሚፈቅደው ተግባር ላይ ብቻ ተሰማሩ» ያሉት (አል-ቡኻሪ፡1100)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) የተልዕኮዋቸውን ትክክለኛ ገፅታ ቁልጭ ባለ ቃል ገልፀዋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የተላኩት ለሰዎች ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ለማሸከም ሳይሆን፥ ገራገርና በጥበብ የተሞላ ዕውቀት ለማስጨበጥ ነው፡፡ መልእክተኛው እንዲህ ብለዋል አላህ «አጨናናቂ ወይም አጣባቢ አድርጎ አልላከኝም ነገር ግን አግራሪና አስተማሪ አድርጎ ልኮኛል፡፡» (ሙስሊም፡1478)