በእስልምና ሃይማኖት በጌታና በባሪያው መሃል አማላጅ የለም፡-

ብዙ ሃይማኖቶች ለአንዳንድ ግለሰቦች ከሌላው ሰው በተለየ መልኩ ሃይማኖታዊ መለያዎችን ችረዋል፡፡ የሰዎች የአምልኮ ጥንካሬም ሆነ የእምነት ደረጃ የሚለካው በእነዚህ ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እንዲሆን አድርገዋል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች በእነዚህ ሃይማኖቶች መሠረት በሰውና በአምላክ መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አገናኝ ድልድዮች መሆናቸው ነው፡፡ ምህረት የሚለግሱትም እነርሱ ናቸው፡፡ የሩቅ ምስጢር (ገይብ) አዋቂ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ይህ እነርሱን ግልፅ ኪሳራ ላይ የጣላቸው የሃቅ ተቃራኒ የሆነና የሐሰት ጥሪያቸው ነው፡፡

ነገርግን ኢስላም ብርሃኑን ፈነጠቀና ለሰው ልጅ ክብርን አጎናፀፈው፣ ከፍ ያለ ደረጃም ሰጠው፡፡ የሰው ደስታ፣ ንሰሐም ሆነ አምልኮ መወሰን ያለበት የፈለገውን ያህል ክብርና ደረጃ ይኑራቸው በጥቂት ግለሰቦች ፈቃደኝነት ላይ ነው የሚለውን ከንቱ አስተሳሰብ ውድቅ አደረገው፡፡

የአንድ ሙስሊም የአምልኮ ተግባር የሚወሰነው በርሱና በአላህ መካከል ብቻ ነው፡፡ ሌላ በመሃከል ሆና የሚያገናኝ አማላጅ ግለሰብ አያስፈልግም፡፡ አላህ ለባሪያው ቅርብ የሆነ ጌታ ነው፡፡ የባሪያውን ጥሪ ሰምቶ ምላሽ መስጠት ይችላል፡፡ አምልኮውን፣ ሶላቱን በመመልከትም ምንዳ ይሰጠዋል፡፡

ማንኛውም የሰው ዘር ምህረት የመቸርም ሆነ ንሰሀ የመቀበል መብትም ሆነ ሥልጣን የለውም፡፡ አንድ የአላህ ባሪያ የሆነ ግለሰብ ለአላህ ፍፁም ቅን ሆኖ ንሰሃ እስከገባ ድረስ፥ አላህ ንሰሀውን ይቀበለዋል ምህረትም ይለግሰዋል፡፡ ማንም ግለሰብ በዚህ ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ ተፅዕኖ የማሳደር መለኮታዊ ኃይል የለውም፡፡ ነገራት ሁሉ የሚከናወኑት በአላህ እጅ ነው፡፡