በህይወት የመኖራችን ዓላማ፡-
ለምን በህይወት ተገኘን? የመኖር ግቡ ምንድነው? የሚሉትን እጅግ ወሳኝ የሆኑ የዘላለም ጥያቄዎችን በመመለሱ ረገድ ብዙ አሳቢያንና ተመራማሪዎች ተመሳሳይ በሆነ አኳኋን ሲደናገሩ ኖረዋል፡፡
ለምን ተፈጠርን?
ብሕይወት የመኖራችን አላማስ ምንድን ነው?
የተከበረው ቁርዓን የሰውን በህይወት የመኖር ዓላማና ግብ በግልፅና ቁልጭ ባለ አኳኋን አስፍሮታል፡፡ ቁርዓን እንዲህ ይላል …«ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡» (አል-ዛሪያት 56)
በዚህ ምድር ላይ በህይወት የመኖራችን ግንባር ቀደሙ ዓላማ አላህን መግገዛት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ያሉት ነገር ይህንን የሚከተሉና የሚያሟሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን አላህን መግገዛት /ዒባዳ/ ማለት በኢስላም ግንዛቤ መሠረት ባህታዊ መሆንና ከዓለማዊ ህይወት ራስን መነጠል ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከሶላት፣ ከፆምና ከዘካ ጎን ለጎን የሚካሄዱ ሥራ፣ ንግግር፣ ፈጠራ፣ የርስ በርስ ግንኙነትና የመሳሰሉት ሌሎች ዓለማዊ ተግባራት ሁሉ ዓላማን /ኒያን/ አስካስተካከሉ ድረስ ዒባዳ /አምልኮ/ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እንዲያውም ከዚህም አልፎ ለዓለማዊ ነገሮች መጫወትና መደሰት ጥሩ በሆነ ዓላማና ለመልካም «ኒያ» እስከሆነ ድረስ ከዒባዳ ተግባራት ተርታ ይመደባል፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ሙሐመድ /ሰ.ዐ.ወ./ «በህጋዊ መንገድ የሚካሄድ ተራክቦ ምፅዋት ነው፡፡» ያሉት ነብዩ /ሰ.ዐ.ወ./ ለማለት የፈለጉት ከባለቤታችሁ ጋር የምታደርጉት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳይቀር ምንዳ የሚያስገኝ ዒባዳ ነው፡፡ ዒባዳ /አምልኮ/ በህይወት የመኖር ግብ ከመሆኑ ጋር፥ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ከተከናወነ ሙሉ ህይወት ይሆናል፡፡ ሙስሊም በየህይወት እርከኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት በሙሉ ዒባዳ ይሆናሉ፡፡ አላህ እንዲህ ይላል …«ስግደቴ መገዛቴም፥ ሕይወቴም፥ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው በል፡፡» /አል-አንዓም፡162/