የእስልምና ሃይማኖት ሁሉንም የህይወት ዘርፍ ያካትታል፡-

እስልምና በመስጂድ ውስጥ ተወስኖ በዱዓ እና በሶላት ብቻ የሚገለፅ ሙሰሊሞች የሚያከናውኑት በመንፈሳዊነት የተገደበ ሃይማኖት አይደለም፡፡

ወይም ደግሞ ተከታዮቹ ግለሰቦች አምነው የሚቀበሉት በልብ ውስጥ ብቻ የሚያድር እምነት አይደለም፡፡

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያተኩር ሥርዓትም አይደለም፡፡

አሊያም ደግሞ አንድን ማህበረሰብ ለመገንባት ያለመ ንድፈ-ሐሳብ ብቻም አይደለም፡፡

ወይም ደግሞ ከሌሎች ወገኖች ጋር በመኗኗሩ ረገድ ሊኖር ስለሚገባው መልካም ሥነ-ምግባርና ግብረ-ገብ የሚያስተምር የእነፃ ትምህርት ብቻም አይደለም፡፡

ይልቁንም ሁሉንም የህይወት ዘርፍ ያካተተ የተሟላ አስተምህሮ ነው፡፡ እያንዳንዱን የኑሮ እርከን ያጠቃለለ ነው፡፡

አላህ ይህን የመሰለ ፀጋ ሙስሊሞች እንዲጎናፀፉ አድርጓል፡፡ ይህን ሙሉ ሃይማኖት እንከተለው ዘንድም ወዶልናል፡፡ እንዲህ ይላል …«ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ፀጋዬንም በናንተ ላይ ፈፀምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡» (አል-ማኢዳህ፡3)

አንዱ የመካ ሙሽሪክ ለማሾፍ በመፈለግ ሰልማን አል-ፋርሲ ለተባሉት ሰሀቢ እንዲህ አላቸው «ጓደኛችሁ (ረሱልን ለማለት ነው) የመፀዳጃ ቤት ስርዓትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል፡፡» ታላቁ ሰሀቢም «አዎን ያስተምሩናል!» ብለው መለሱና በዚሁ ዙሪያ ያለውን ኢስላማዊ ሕግና ሥርዓት አብራሩለት፡፡