ልብስ በኢስላም
አንድ ሙእሚን ከሰዎች ጋር ለመደባለቅና ሠላትን ለመስገድ የሚለብሰው ልብስ፣ የሚያምርና ንጹህ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ (ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡›› (አል አዕራፍ 31)
አላህ (ሱ.ወ)፣ የሰው ልጅ በአለባበሱና በይፋዊ መገለጫው እንዲቆነጃጅ የሚያዘው ሕግን ደንግጓል፡፡ ይህ በራሱ የአላህን ጸጋ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአላህን ጌጥ ያችን ለባሮቹ የፈጠራትን ከሲሳይም ጥሩዎቹን እርም ያደረገ ማን ነው? በላቸው እርሷ በትንሳኤ ቀን ለነዚያ ላመኑት ብቻ ስትኾን በቅርቢቱ ሕይወት ተገቢያቸው ናት፡፡ በላቸው እንደዚሁ ለሚያውቁ ሕዝቦቹ አንቀጾችን እናብራራለን፡፡›› (አል አዕራፍ 32)
ልብስ ብዙ ጉዳዮች ይፈጸሙበታል፡
- የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ከእይታ ይሸፍናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን፡፡›› (አል አዕራፍ 26)
- ገላን ከሙቀትና ከውርጭ፣ እንዲሁም ከጎጂ ነገሮች ይጠብቃል፡፡ ብርድና ሙቀት ተለዋዋጭ የአየር ንብረቶች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ የልብስን ገጽታ በማስመልከት እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሐሩርንም (ብርድንም) የሚጠብቋችሁን ልብሶች፣ የጦራችሁንም አደጋ የሚጠብቋችሁን ጥሩሮች ለናንተ አደረገላችሁ፡፡እንደዚሁ ትሰልሙ ዘንድ ጸጋውን በናንተ ላይ ይሞላል፡፡›› (አል ነሕል 81)
ኢስላም ተፈጥሯዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎችን አኗኗር አስመልክቶ የተደነገጉት ሕጎች በሙሉ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማሙና ከጤናማ አዕምሮ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡
ኢስላም ተፈጥሯዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎችን አኗኗር አስመልክቶ የተደነገጉት ሕጎች በሙሉ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማሙና ከጤናማ አዕምሮ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡
የሙስሊም አለባበስና የተፈቀዱ መቆነጃጃዎች ኢስላም የሰው ልጅን አለባበሰ የተገደበ አላደረገውም፡፡ ድንበር ማለፍ የሌለባቸው ከሆነና ለተፈለጉበት ዓላማ መዋል የሚችሉ እስከሆኑ ድረስ፣ ሁሉም የልብስ ዓይነቶች ሕጋዊ መሆናቸውን ያጸድቃል፡፡
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ በዘመኑ የነበሩ አልባሳትን ለብሰዋል፡፡ ሰዎች የተወሰኑ ልብሶች ብቻ እንዲለበሱ አላዘዙም፡፡ እንዳይለበሱ የከለከሉት ውስን ልብስም የለም፡፡ የከለከሉት በአለባበስ ዙሪያ ያሉ የተወሰኑ ገጽታዎችን ነው፡፡
በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የሁሉም ነገር መሰረቱ የተፈቀደ ነው፡፡ በማስረጃ ካልሆነ በስተቀር እርም ነው ማለት አይቻልም፡፡ ልብስ ደግሞ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ አምልኮ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት አምልኮ መሰረቱ የተከለከለ ነው፡፡ በማስረጃ ካልሆነ በስተቀር የተፈቀደ ወይም ሕጋዊ አይሆንም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ያለማባከንና ያለኩራት ብሉ፣ መጽውቱ፣ ልበሱ፡፡›› (አል ነሳኢ 2559)
የተከለከሉ አልባሳት
- አንድ ሙስሊም ሀፍረተ ገላውን በልብስ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሀፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን፡፡›› (አል አዕራፍ 26) ኢስላም ለወንዶችም ለሴቶችም የሀፍረተ ገላን ገደብ አስቀምጧል፡፡ የወንድ ልጅ ሀፍረተ ገላ ከእንብርቱ እስከ ጉልበቱ ሲሆን፣ ትልቁ ሀፍረተ ገላው ሁለት ብልቶቹ ናቸው፡፡ እነኚህ ሁለት ብልቶች፣ ለሚስት ወይም እንደ ሕክምና እና መሰል ጉዳዮች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ካልሆነ በስተቀር ለማንም ማሳየት አይፈቀድም፡፡ አንድ ሠሓቢይ፣ ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ሀፍረተ ገላ በጠየቃቸው ጊዜ እንዲህ ብለውታል፡- ‹‹ሀፍረተ ገላህን፣ ለባለቤትህ ወይም በቁጥጥርህ ስር ላሉ ባሮች ካልሆነ በስተቀር ከማጋለጥ ጠብቅ፡፡›› ሠሓቢዩም፡ «አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ፣ ሰዎች ከፊሉ ከከፊሉ ጋር ተደበላልቀውና ተቀላቅለው የሚኖሩ ከሆነስ?» አላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉት፡- ‹‹አንድም ሰው እንዳያይብህ ማድረግ እስከቻልክ አይይብህ፡፡›› አሉት ሠሓቢዩም በማስከተል፡- «እሺ አንዳችን ብቻውን ከሆነስ?(እርቃኑን ቢሆንስ)» በማለት ጠየቀ፡፡ ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አላህ ከሰዎች የበለጠ ሊታፈር ይገባል፡፡›› አሉት (አቡ ዳውድ 4017) ሴት ልጅ፣ ለወንዶች እይታ በምትጋለጥበት ወይም ወንዶች ፊት ለፊት ስትሆን፣ ከመዳፎቿና ከፊቷ በስተቀር ሰውነቷ በጠቅላላ ሀፍረተ ገላዋ ነው፡፡ ይህ ሴቶችን ከማናቸውም ክብራቸውን ከሚያጎድፍና በነርሱ ላይ አደጋን ከሚጋርጥ ነገር የሚጠብቅ ነው፡፡ ኢስላም፣ በፈቀደበት አጋጣሚ ላይ ካልሆነ በስተቀር ለባዕድ (አጅነቢ) ወንዶች ምንም ዓይነት የገላዋን ክፍል መግለጥና ለእይታ ማጋለጥ አይፈቀድላትም፡፡ ነገር ግን የቅርብ ተጠሪዎቿ (መሓሪሞቿ) ፊት ለፊት በተለምዶ መገለጥ ወይም መታየት ያለበት የሆነን ገላዋን ተገልጣ መታየት ትችላለች፡፡ ባሏ ግን ለርሱም ሆነ ለርሷ የፈለጉትን መመልከትና በሱም መርካትና መደሰት ይችላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡›› (አል በቀራ 187) የገላን ቅርጽ የሚያወጣ የተወጣጠረ ልብስም ሆነ ከስሩ ያለን ገላ ገልጦ በሚያሳይ ስስ ልብስ መሸፈን አይቻልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ ሀፍረተ ገላውን የሚያሳይ ስስ ልብስ በሚለብስ ሰው ላይ የዛተው ለዚህ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹ሁለት ዓይነት ሰዎች የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡›› ካሉ በኋላ ‹‹ለብሰው የተራቆቱ ሴቶች፡፡›› በማለት አንደኛውን ጠቅሰዋል፡፡
-
በሁለቱ ጾታዎች መሐል መመሳሰልን የሚፈጥር ይህ ሴቶች ብቻ የሚለብሷቸውን አልባሳት በመልበስ ወንዶች ከሴቶች ጋር መመሳሰላቸውንና እንዲሁም ሴቶች በወንዶች መመሳሰላቸውን የሚገልፅ ነው፡፡ ይህ ከከባባድ ወንጀሎች ውስጥ የሚፈረጅ እርም ወይም ክልክል ነው፡፡ በአካሄድ፣ በንግግርና በመሳሰሉት መመሳሰልም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የሴቶችን ልብስ የሚለብስን ወንድ እንዲሁም የወንዶችን ልብስ የምትለብስ ሴትን ተራግመዋል፡፡ (አቡ ዳውድ 4098) በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከወንዶች መካከል በሴቶች የሚመመሳሰሉትን፣ ከሴቶች መካከልም በወንዶች የሚመሳሰሉትን ተራግመዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 5546) እርግማን ማለት ከአላህ እዝነት መባረርና መራቅ ነው፡፡ ኢስላም የወንድ ባህሪና ውጫዊ መገለጫዎቹ፣ የርሱ ብቻና ከሴቶች የሚለዩት እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ ሴቶችም እንዲሁ፡፡ ካልተበረዘ ተፈጥሯዊ ስርዓትና ጤናማ አዕምሯዊ እይታ ጋር የሚስማማውም ይሄው ነው፡፡
- ከካሃዲያን ልዩ መገለጫ ጋር የሚመሳሰለል ልብስ እንደ ባሕታውያንና ካህናት ልብሶች ዓይነት የተወሰነ ሃይማኖት መገለጫ ወይም አርማ የተደረጉ አልባሳትና የመሳሰሉት የተከለከሉ ናቸው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከሕዝቦች ጋር የተመሳሰለ እርሱ ከነርሱ ነው፡፡›› (አቡ ዳውድ 4031) የሃይማኖት ማንጸባረቂያ አርማ ያለባቸው አልባሳትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ መመሳሰል፡ የአቋም ድክመት፣ በራስ አለመተማመንና እርሱ በእምነት እርግጠኛ አለመሆንን የሚያስረዳ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም፣ ከከሃዲያን መካከል አብዛኞቹ የሚለብሱትና የሚያዘወትሩት ቢሆንም፣ በሀገሩ ላይ በሰፊው ሕዝብ የሚለበስን ልብስ መልበሱ መመሳሰል አይባልም፡፡ ምክንያቱም፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በኢስላማዊው ድንጋጌ ከተከለከለው ውጭ የቁረይሽ አጋሪያን ይለብሱት የነበረውን የልብስ ዓይነት ይለብሱ ነበር፡፡
-
ኩራትና መኮፈስን የሚያንጸባርቅ አለባበስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በቀልቡ ውስጥ የቅንጣትን ክብደት ያክል ኩራት ያለበት ሰው ጀነት አይገባም፡፡›› (ሙስሊም 91) ኢስላም ኩራትና መኮፈስን የሚፈጥር ከሆነ ወንዶች ልብሳቸውን ከቁርጭምጭሚታቸው በታች በመልቀቅ እንዳይጎትቱ ከልክሏል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በትዕቢት ተሞልቶ ልብሱን የጎተተ ሰው የትንሳኤ ቀን አላህ አይመለከተውም፡፡›› (አል ቡኻሪ 3465 ሙስሊም 2085) ለታዋቂነት የሚጋብዝ ልብስም ተከልክሏል፡፡ አንድ ሰው በመልበሱ ሰዎች የሚገረሙበትና የሚደነቁበት፣ ስለሱ የሚያወሩለት ፣በይዘቱ ወይም በመልኩ ወይም እሱን የለበሰ ሰው በሚያሳየው የኩራትና የትዕቢት ስሜት ምክንያት የሚሸማቀቁበት የአለባበስ ዓይነት ወይም ልብስ የተከለከለ ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በዱንያ ላይ የታዋቂነት ልብስን የለበሰ ሰው፣ አላህ (ሱ.ወ) በትንሳኤ ቀን የውርደት ልብስን ያለብሰዋል፡፡›› (አህመድ 5664 ኢብኑ ማጃህ 3607)
- ሐርነት ወይም ወርቅነት ያለው ከሆነ ለወንዶች የተከለከለ ነው፡፡ ኢስላም ሁለቱንም በወንዶች ላይ እርም አድርጓል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እነኚህ ሁለቱ በወንድ ሕዝቦቼ ላይ እርሞች ናቸው፤ ለሴቶቻቸው ደግሞ የተፈቀዱ ናቸው፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 3595 / አቡ ዳውድ 4057) በወንዶች ላይ እርም የተደረገው፣ በሐር ትል የሚመረተው የተፈጥሮ ሐር ነው፡፡
- ማባከንና ማዝረክረክ ያለበት፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ማባከንና ኩራት በሌለበት ሁኔታ ብሉ መጽውቱ ልበሱ፡፡›› (አል ነሳኢ 2559) ይህ እንደሁኔታው ይለያያል፡፡ ባለሃብት፣ ድሃ ሊገዛው የማይገባውንና የማይችለውን የልብስ ዓይነት የመግዛት መብት አለው፡፡ ይህም ካለው ሃብትና ገቢ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ደረጃ አንጻር የሚታይ ይሆናል፡፡ አንድ ልብስ ለድሃ ሰው ማባከን ተብሎ ለሃብታም ግን ማባከን ላይባል ይችላል፡፡