ሁለቱ ምስክርነቶች፤ ትርጉማቸውና ዓላማቸው

ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩንና መሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ

“ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የምንለው ለምንድ ነው?

  • በሙስሊም ላይ የመጀመሪያው ግዴታ ይህን ቃል ማረጋገጥ ነው፡፡ አንድ ሰው ወደ እስልምና መግባት ከፈለገ በቃሉ ውስጥ ባለው ፅንሰ-ሃሳብ ማመንና ቃሉን መግለፅ ይኖርበታል፡፡
  • ቃሉ ባካተተው ዕውነታ ከልቡ አምኖና የአላህን ውዴታ ፈልጎ ቃሉን በንግግር በመግለፅ የመሰከረ ሰው ከእሳት ቅጣት ነፃ ለመውጣት ሰበብ ይሆነዋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል… “(የአላህን ውዴታ በመፈለግ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ብሎ የመሰከረ ሰው አላህ በርሱ ላይ እሳትን እርም አድርጓታል፡፡” (አል-ቡከሪ፡415)
  • ይህ ቃል በውስጡ ባካተተው ፅንሰ-ሃሳብ አምኖ የሞተ ሰው የጀነት ነዋሪ ይሆናል፡፡ ነቡዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እነዲህ ብለዋል … “ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን አውቆ የሞተ ሰው ጀነት ገብቷል፡፡” (አህመድ፡464)
  • ይህ በመሆኑም ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን ማወቀ የግዴታዎች ሁሉ ተላቁ ግዴታ ነው፡፡

“ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የሚለው ቃል ትርጉም

ይህ ማለት ብቸኛ ከሆነው አላህ በስተቀር በዕውነት የሚመለከ አምላክ የለም ማለት ነው፡፡ ከተቀደሰውና ከፍ ካለው አላህ በስተቀር ከማንም ላይ መለኮታዊነትን መሻር ማለት ሲሆን መለኮታዊ ስልጣንን አንድና አጋር ለሌለው አላህ ብቻ ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡

«አል-ኢላህ» (አምላክ)! ማለት የሚመለክ ማለት ነው፡፡ አንድን ነገር ያመለከ ሰው ያንን ነገር ከአላህ ሌላ አምላክ አድርጎ ይዞታል፡፡ ከተቀደሰው፣ ከፍ ካለውና ፈጣሪ ከሆነው አንዱ ጌታ በስተቀር የሚመለኩ ነገሮች በሙሉ ባጢል (ሐሰት) ናቸው፡፡

አምልኮ የሚገባው ከጉድለት የጠራውና ከፍ ያለው አላህ ብቻ ነው፡፡ ቀልቦች በውዴታ፣ በማላቅ፣ በማክበር፣ በመተናነስ፣ በመፍራት፣ በርሱ ላይ በመመካት ያመልኩታል፡፡ ለልመናም እርሱን ይጠሩታል፡፡ ከአላህ ውጪ ለልመና የሚጠራ የለም፡፡ እርዳታ የሚጠየቀው እርሱ ብቻ ነው፡፡ በርሱ ካልሆነ በማንም መመካት አይቻልም፡፡ ለርሱ ካልሆነ ለማንም አይሰገድም፡፡ የአምልኮ እርድ ለርሱ ካልሆነ ለማንም አይታረድም፡፡ አምልኮ የተባለን በሙሉ ለርሱ ብቻ ማጥራት ግዴታ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ “አላህን ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች ቀጥተኞች ሆነው ሊገዙት፣ ሶላተንም አስተካክለው ሊሰግዱ ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልተዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)፡፡” (አል-በይናህ፡4)

ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም የሚለው ቃል በማረጋገጥ፥ አላህን ጥርት አድርጎ ያመለከ ሰው፥ ታላቅ የሆነ ደስታን ይጎናፀፋል፡፡ እርጋታና ስክነት ያለው መልካም ህይወት ይኖራል፡፡ አላህን በብቸኝነት ከማምለክ ሌላ፥ ለቀልብ ትክክለኛ የሆነ መረጋጋትን፣ እርካታንና ረፍት የሚሰጥ ሌላ ነገር የለም፡፡ አላህ እንዲህ ብሎዋል፡፡ “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን…” (አል-ነሕል፡97)

“ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የሚለው ቃል መሠረቶች

የዚህ ታላቅ የሆነ ቃል ትርጉምና ዓላማ ግልፅ እንዲሆንልን ከተፈለገ ሁለት መሠረቶችን ማወቁ ግድ ይለናል፡፡

የመጀመሪያው መሠረት፡- «ላ ኢላሃ» (አምላከ የለም) የሚለው ነው፡፡ ይህ ከአላህ ውጪ ባሉ ነገሮች ላይ አምልኮን መሻራችንን ማረጋገጫ ቃል ነው፡፡ ማጋራትን ውድቅ ማድረጊያ ቃል ነው፡፡ ከአላህ ሌላ በሚመለኩ ነገሮች ሁሉ መካድ ግዴታ ነው፡፡ ከአላህ ሌላ ሰውም ሆነ እንሰሳትም ሆነ መቃብርም ሆነ ከዋክብትም ሆነ ሌላ ማምለክ አይቻልም፡፡

ሁለተኛው መሠረት፡- ኢልለ ላህ (ከአላህ በስተቀር) የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ አምልኮን ለአላህ ብቻ የምናረጋግጥበት ቃል ነው፡፡ ሶላትን፣ ዱዓእና መመካትን የመሳሰሉ የአምልኮ ዓይነቶችን ሁሉ ለአላህ ብቻ የምናውልበት ማረጋገጫ ነው፡፡

የአምልኮ ዓይነቶችን በሙሉ ልንሰጥ የሚገባው አንድና አጋር ለሌለው አላህ ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱን እንኳ ከአላሀ ውጪ ላለ ነገር አሳልፎ የሰጠ ከሃዲ ይሆናል፡፡

አላህ እንዲሀ ይላል …“ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ ለርሱ በርሱ ማስረጃ የሌለውን የሚግገዛ ሰው ምርመራው ጌታው ዘንድ ብቻ ነው፤ እነሆ ከሀዲዎች አይድኑም፡፡” (አል-ሙእሚን፡117) ከአላሀ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም የሚለው ቃል ትርጓሜና መሠረቶች እንዲህ በሚለው የአላህ ቃል ውስጥ ተገልጿል… “በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡” (አል-በቀራህ፡256)

በዚህ የአላህ ቃል ውስጥ “በጣዖትም የሚክድ” የሚለው ቃል የመጀመሪያ መሠረት የሆነውን “አምላክ የለም” የሚለውን ቃል ሲሆን ያረጋገጠው “በአላህ የሚያምን” የሚለው የጌታችን ቃል ደግሞ ሁለተኛ መሠረት የሆነውን ከአላህ በስተቀር የሚለውን ቃል የረጋግጥልናል፡፡

ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን መመስከር

ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ.) ማወቅ

ልደታቸው፡-

የተወለዱት እ.ኤ.አ. በ570 መካ ውስጥ ነው፡፡ ሲወለዱ አባታቸው በህይወት አልነበሩም፡፡ እናታቸውንም ያጡት ገና ልጅ ሆነው ሳለ ነው፡፡ ተንከባክበው ያሳደጓቸው መጀመሪያ አያታቸው ዓብዱል ሙጠሊብ ሲሆኑ በመቀጠል ትንሽ አደግ እንዳሉ ደግሞ አጎታቸው አቢ-ጣሊብ ናቸው

ህይወታቸውና እድገታቸው፡-

ለነቢይነት ማዕረግ ከመብቃታቸው በፊት ለአርባ አመታት ያህል እ.ኤ.አ. (ከ570 -610) ከቁረይሽ ጎሳዎች ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የታላቅ ሥነ-ምግባርና የፅናት ተምሳሌት እንዲሁም መለያ ሆነው ቆይተዋል፡፡ «ታማኙ» «እውነተኛው» በሚሉ የቅፅል ሥሞች በገሃድ ይታወቁ ነበር፡፡ እረኛ ነበሩ፡፡ ከዚያም በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ነብይ ከመሆናቸው በፊትም በኢብራሒም መንገድ በመጓዝ አላህን በብቸኝነት ያመልኩ ነበር፡፡ የጣዖትና የባዕድ አምልኮዎችን ይርቁና ይጠየፉ ነበር፡፡

ተልዕኳቸው፡-

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) አርባ ዓመታትን በዚህ ሁኔታ ካሳለፉ በኋላ፥ በመካ አቅራቢያ ከሚገኙ ተራራዎች አንዱ በሆነው «ኑር» ተራራ ውስጥ በሚገኘው «ሒራእ» ዋሻ ውስጥ በመሆን በጥልቅ ተመስጦ አላህን ያመልኩ ነበር፡፡ ከዚያም ከአላህ ዘንድ የሆነ ወህይ (ራዕይ) ይገለፅላቸው ጀመር፡፡ የአላህ ቃል የሆነው ቁርኣን በእርሳቸው ላይ መውረድ ጀመረ፡፡ በመጀመሪያ በርሳቸው ላይ የወረደው የቁርኣን ቃል…”አንብብ ፥ በዚያ ሁሉን በፈጠረው ጌታህ ስም” የሚለው ነበር ይህ የእርሳቸው ተልዕኮ ዕውቀትን፣ ንባብን፣ ብርሃንና የቀጥተኛ ጎዳናን የማብሰሪያ አዲስ ዘመን ጅማሮ መሆኑን ለመግለፅ ይህ አንቀፅ ወረደ፡፡ ከዚያ በሃያ ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሌሎች የቁርኣን አናቅፅ እየተከታተሉ ወረዱ፡፡

የዳዕዋ (የሰበካ) መጀመር፡-

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ለሦስት ዓመታት ያህል ሰበካቸውን በድብቅ አካሄዱ፡፡ ከዚያም ለተከታዮቹ አስር ዓመታት ሰበካቸውን በግልፅና በገሃዱ አደረጉ፡፡ ነቢዩና (ሰ.ዐ.ወ.) የእምነት ባልደረቦቻቸው (ሶሃቦች) ይህን በማድረጋቸው፥ ጎሳዎቻቸው ከሆኑት ቁረይሾች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ፣ ሁከትና፣ ማዋከብ ገጠማቸው፡፡ ወደ ሐጅ ለሚመላለሱ ጎሳዎች የእስልምና ግብዣ ቀረበላቸው፡፡ የመዲና ነዋሪዎች ዘንድ ጥሪው ተቀባይነትን አገኘ፡፡ ከዚያ ቀስበቀስ ወደ መዲና ከተማ የስደት ጉዞ ተደረገ፡፡.

ስደት፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እ.ኤ.አ. በ622 ያኔ «የስሪብ» ትባል ወደ ነበረችው መዲና ከተማ ስደት አደረጉ፡፡ በወቅቱ የሃምሳ ሦስት ዓመት ጎልማሳ ነበሩ፡፡ ዳዕዋቸውን ያወገዙ የቁረይሽ ጎሳ ባላባቶች ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ.) ላይ ግድያ ለመፈፀመ አሲረው ነበር፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ኢስላም እየተጣሩ ለአስር አመታት ያህል በመዲና ከተማ ኖሩ፡፡ ሰላት፣ ዘካና ሌሎች የሸሪዓው ህግጋቶች እንዲተገበሩ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡

እስልምናን ማሰራጨት፡-

የአላህ መልእክተኛ ወደ መዲና ከተሰደዱ በኋላ ከ622-632 ባለው ጊዜ ውሰጥ የኢሰላማዊ ስልጣኔ መሠረት ተክለዋል፡፡ አዲስ ሙስሊም ማህበረሰብ ፈጥረዋል፡፡ ዘረኝነትና ጎሰኝነትን አስቀርተዋል፡፡ ዕውቀትን አሰራጭተዋል፡፡ የፍትህ፣ የፅናት፣ የወንድማማችነት፣ የመረዳዳት መርህን ገንብተዋል፡፡ አንዳንድ ጎሳዎች እስልምናን በአጭሩ በማስቀረት ተነሳስተው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ አላህ ሃይማኖቱንና መልእክተኛውን ረድቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በመካ ነዋሪ የሆኑ ብዙ ጎሳዎች ወደ እስልምና ገብተዋል፡፡ በዓረብ ፔንሱላ ከተማዎች የሚኖሩ በርካታ ጎሳዎችም በራሳቸው ምርጫ ፍላጎትና ውዴታ ወደ ዚህ ታላቅ ሃይማኖት እየተግተለተሉ ገብተዋል፡፡

ህልፈታችው፡-

የአላህ መልእክተኛ(ሰ.ዐ.ወ.) በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር ሰፈር 11፣ መልእክታቸውን አድርሰው ጨረሱ፣ አደራቸውንም ተወጡ፡፡ አላህም ሃይማኖቱን ሙሉ በማድረግ ለሰዎች ፀጋውን አጎናፀፈ፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የወባ ህመም አጋጠማቸው፡፡ ያደረባቸው ህመም እየፀና ሄደ በወርሃ ረቢዑል አወል በዕለተ ሰኞ በ11ኛው ዓመተ ሒጅራ ይህን ዓለም ተሰናብተው ወደ ቀጣዩ ዓለም ተሸጋገሩ፡፡ ይህ ማለት እ.ኤ.አ. ሜይ 8¸ 632 መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ዓለም ሲለዩ የስድሳ ሦስት ዓመት አዛውንት ነበሩ፡፡ ግብአተ-መሬታቸው የተፈፀመው ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) መስጂድ አጠገብ እሜቴ ዓኢሻ ቤት ውስጥ ነው፡፡

የነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ሙሉ ስም፡-
ሙሐመድ ቢን አብደላህ ቢን ዓብዱል ሙጠሊብ ቢን ሃሺም አል-ቁረይሺ የነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ጎሳ በዓረቦች ዘንድ እጅግ የተከበረ ጎሳ ነው፡፡
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ሰው ዘር ሁሉ የተላኩ መልእክተኛ ናቸው፡፡
 አላህ ነቢያችን ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ሁሉም የሰው ዘር በጠቅላላ ልኳቸዋል፡፡ እርሳቸውን መታዘዝ በሁሉም ሰው ላይ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “(ሙሐመድ ሆይ!) በላቸው እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደናንተ ወደ ሁላችሁም የአላህ መልእክተኛ ነኝ፡፡” (አል-ዕራፍ፡158)
በርሳቸው ላይ ቁርኣንን አወረደ፡-
አላህ፥ ከፊቱም ሆነ ከኋላው ሃሰት የሌለውን ታላቅ መፅሐፍ ቁርኣን በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ላይ አወረደ፡፡
የነቢያትና የመልእክተኞች መደምደሚያ፡-
አላህ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ.) የላከው የመጨረሻና መደምደሚያ ነቢይ አድርጎ ነው፡፡ ከርሳቸው በኋላ የሚነሳ አንድም ነቢይ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “…ግን የአላህ መልእክተኛና የነቢዮች መደምደሚያ ነው፡፡” (አል-አሕዛብ፡4ዐ)

«ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ ናቸው» የሚለው ቃል ትርጉም

እንዲህ ብሎ መመስከር፥ የተናገሩትን አምኖ መቀበል፣ ትዕዛዛቸውን መፈፀምና ክልከላቸውን መታቀብ ማለት ነው፡፡ አላህንም ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በደነገጉትና ባስተማሩን መሠረት ብቻ ማምለክና መግገዛት ማለት ነው፡፡

ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛ መሆናቸውን ማመኔ የሚያጠቃልለው ምንና ምንድ ነው?

  1. ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ.) ሁሉንም ነገር አስመልክቶ የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም፡-
  • ከህዋስ ስለራቁ ምስጢራዊ ነገሮች፣ ስለመጨረሻው ቀን፣ ስለጀነት ፀጋዎችና ስለ እሳት ቅጣት፣
  • በእለተ ቂያማ ስለሚከሰቱ ነገሮችና ምልክቶቻቸው እንዲሁም በመጨረሻው ዘመን ስለሚሆኑ ነገሮች፡-
  • ስላለፉና ስለቀደሙ ህዝቦች፣ በነቢያትና ጥሪ ባደረጉላቸው ህዝቦች መካከል ስለተፈጠሩት ነገሮች
  1. ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ያዘዟቸውን ነገሮች መተግበርና ከከለከሉት ተግባራት መታቀብም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም፡-
  • ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የሚያዝዙን ትዕዛዛት ከራሳቸው አፍልቀው ሳይሆን ከአላህ በሚገለፅላቸው ራዕይ አማካኝነት መሆኑን በእርግጥኝነት ማመን ይኖርብናል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “መልእክተኛውን የሚታዘዝ ሰው፥ በእርግጥ አላህን ታዘዘ፡፡” (አል-ኒሳእ፡80)
  • እርሳቸው ከከለከሏቸው ሐራም ነገሮች፣ መጥፎና ጎጂ የሆኑ ሥነ-ምግባራትና ግብረ ገቦች መታቀብም ይኖርብናል፡፡ እነዚህን ነገሮች እንዳናደርግ የከለከሉንም እውነታው ከእኛ ቢሰወርና ባናውቀውም ለአንዳች ጥበብ አላህ ፈልጎ ያደረገው መሆኑንና ለራሳችን ጥቅም መሆኑን ማመን ይኖርብናል፡፡
  • ያዘዙንን መተግበራችን፣ ከከለከሉን መታቀባችን ዞሮ ዞሮ ለእኛ መልካም እንደሆነና በዚህም ሆነ በቀጣዩ ዓለም ደስታን እንደሚያጎናፅፈን በእርግጠኝነት ማመን ይኖርብናል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል …”ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህንና መልእክተኛውን ታዘዙ፡፡” (አሊ-ዒምራን፡132)
  • ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ትዕዛዝ ሆን ብሎ መጣስ ለቅጣት የሚዳርግ ተግባር መሆኑ ተገቢ ነገር መሆኑንም ማመን ይኖርብናል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “…እነዚያም ትእዛዙን የሚጥሉ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ፡፡” (አል-ኑር፡63)
  1. አላህን ማምለክ የሚኖርብን ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በደነገጉት መልኩ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ዕውነታ ብዙ ነገሮችን የሚያካትት በመሆኑ ይህን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ይኽውም፡-
  • አርዓያነታቸውን መከተል፡- የአላህ መልእክተኛን (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና (የየእለት ተግባር) ፣ መመሪያና ህይወት በአጠቃላይ ንግግራቸውን፣ ተግባራቸውንና አፅድቆታቸውን ጨምሮ በሁሉም የህይወት እርከናችን በአርዓያነት ልንከተለው ይገባል፡፡ አንድ የአላህ ባሪያ የአላህ መልእክተኛን ሱንና ይበልጥ በአርዓያነት በተከተለ ቁጥር፥ ይበልጥ ወደ አላህ የተጠጋና ደረጃውም ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “በላቸው አላህን የምትወዱ እንደኾናችሁ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኋል፤ ኃጢአቶቻችሁንም ለናንተ ይምራልና፤ አላህ መሐሪ አዛኝ ነው፡፡” (አሊ-ዒምራን፡31)
  • የተሟላ ህግ፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ይዘው የመጡት ሃይማኖትና ህግጋት በሁሉም ረገድ ምሉዕና ጉድለት የሌለው ነው፡፡ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ.) ያልደነገጉትን የአምልኮ ተግባር በአዲስ መልክ መፍጠር ለማንም ሰው ቢሆን የተፈቀደ አይደለም፡፡
  • አላህ የደነገገው ህግ በሁሉም ጊዜና ቦታ ተስማሚ ነው፡- በአላህ መፅሐፍና በነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና ውስጥ የተደነገገው ህግና ሥርዓት በሙሉ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ተስማሚ ነው፡፡ ሰዎችን ከምንም ካስገኛቸውና ከፈጠራቸው ጌታ በላይ ሰዎችን የሚጠቅም ነገር የሚያውቅም ማንም የለም፡፡
  • ከሱንና ጋር ስምሙ መሆን፡- አንድ የአምልኮ ተግባር አላህ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ የአላህን ውዴታ ብቻ አስቦ (ነይቶ) መስራትና ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና ጋር የተጣጣመ መሆኑ ግድ ይላል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ስራን ይስራ በጌታውም መግገዛት አንድንም አያጋራ በላቸው፡፡” (አል-ከህፍ፡110) በዚህ አንቀፅ ውስጥ «መልካም ሥራ» በሚል የተወሳው ከአላህ መልእክተኛ ሱንና ጋር ተጣጥሞ የተገኘ ስራ ማለት ነው፡፡
  • በ ኢስላም ያላተደነገገን ሃይማኖታዊ ተግባርን መፍጠር ሃራም ነው፡- አላህን ለማምለክ በሚል፥ የአላህ መልእከተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ያልደነገጉትንና ሸሪዓዊ ባልሆነ መንገድ አዲስ የአምልኮ ተግባር የፈጠረ ሰው፥ የነቢዩን መንገድ ተፃሮ የተገኘ በመሆኑ ወንጀለኛ ይሆናል፡፡ ስራውም ተመላሽና ተቀባይነት የሌለው ይደረጋል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “… እነዚያም ትእዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ፡፡” (አል-ኑር፡63) ነቢዩም (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል “በዚህ ጉዳያችን ውስጥ ከርሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ፤ ሥራው ተመላሽ ነው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡2550 ሙስሊም 1718)