ስድስቱ የእምነት መሠረቶች

በኃያሉ አላህ የማመን ትርጉም፡-

የኃያሉ አላህ መኖርን እውነት ብሎ አምኖ መቀበል ነው፡፡ ጌትነቱን፣ አምላክነቱን፣ ማረጋገጥ ነው፡፡ በስሞቹንና በባህሪያቱ ማመን ነው።

ስለ እነዚህ አራት ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው ዘርዘር ባለ መልኩ እንነጋገራለን፡-

  1. በአላህ መኖር ማመን፡-

የአላህ ፍጥረት፡-

በአላህ መኖር ማመን ሰው በተፈጥሮው የሚያረጋግጠውና ሌላ ተጨማሪ መረጃ የማያስፈልገው ነገር ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ምንም የተለያየ ሃይማኖትና መንገድ ቢከተሉም በጣም በርካታ ሰዎች አላህ ለመኖሩ ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡

የእርሱን መኖር የሚያረጋግጥ ጥልቅ የሆነ ስሜት በቀልባችን ይሰማናል፡፡ በተፈጥሮው አማኝ በሆነው ስሜታችን ገፋፊነት መጥፎና አስቸጋሪ ነገር ሲገጥመን ወደርሱ እንሸሻለን፡፡ አንዳንዶች ለመሸፋፈንና ለመዘናጋት ሙከራ ቢያደርጉም፥ አላህ በእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ውስጥ ወደ ሃይማኖተኛነት የመዘንበል ስሜትን ፈጥሯል፡፡

እኛም አላህ ለተጣሪዎች ምላሸን ሲሰጥ፣ ለጠያቂዎች የጠየቁትን ሲቸር፣ ለተለማማኞች ፍላጎታቸውን ሲያሟላ ስለምናይና ስለምንሰማ፥ ይህ ሁኔታ አላህ ለመኖሩ እርግጠኛ መረጃ ይሆነናል፡፡

አላህ መኖሩ እጅግ ግልፅ የሆነ ነገር ነው፡ መረጃዎችን መዘርዘርም አያስፈልግም፡፡ ግልፅ ከሚያደርጉት ነገሮች ውስጥም፡-

  • በሁሉም ሰው ዘንድ እንደሚታወቀው ማንኛውም ድርጊት አድራጊ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ በየጊዜው የምንመለከተው ይህ እጅግ በርካታ ፍጥረት አስገኚና ፈጣሪ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ እርሱም ኃያሉና ታላቁ አላህ ነው፡፡ አንድ ፍጡር ያለምንም ፈጣሪ ተገኘ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ራሱን በራሱ ፈጥሯል ማለትም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ነገር ራሱን በራሱ ሊፈጥር አይችልም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ወይስ ያለ አንዳች ፈጣሪ ተፈጠሩን ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?” (አልጡር፡35) በዚህ አንቀፅ መተላለፍ የተፈለገው መልእክት “እነርሱ ያለፈጣሪ አልተፈጠሩም፡፡ እነርሱም ራሳቸውን አልፈጠሩም፡፡ ስለዚህ ፈጣሪያቸው ሊሆን የሚችለው የተቀደሰውና ከፍ ያለው አላህ ነው” የሚል ነው፡፡
  • ሰማዩ፣ ምድሩ፣ ከዋክብቱ፣ ዛፎቹና ይህ ፍጥረተ-ዓለም በአጠቃላይ የተመሠረተበት ሥርዓት ግልፅ በሆነ ሁኔታ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፥ የዚህ ፍጥረተ-ዓለም ፈጣሪ አንድ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እርሱም ከፍ ያለውና ከጉድለት የጠራው አላህ ነው፡፡ “… የዚያን ነገሩን ሁሉ ያጠነከረውና የአላህን ጥበብ (ተመልከት)፡፡” (አል-ነምል፡88) ክዋክብቶችን በምሳሌነት እንውሰድ፥ ፅኑ በሆነ አኳኋንና ስርዓት ነው የሚጓዙት፡፡ ሁሉም ኮከብ ያለምንም መሰናክልና መወላገድ በራሱ በሆነ ምህዋር ብቻ ይጓዛል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም፤ ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም፤ ሁሉም በመዞሪያቸው ውሰጥ ይዋኛሉ፡፡” (ያሲን፡40)
  1. በኃያሉ አላህ ጌትነት ማመን

በኃያሉ አላህ ጌትነት የማመን ትርጉም፡-

ኃያሉ አላህ የሁሉም ነገር ባለቤት፣ ፈጣሪና ሲሳይን ሰጪ ነው ብሎ አምኖ መቀበልና እውነት ነው ብሎ በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በጌትነቱ ማመን ማለት ህይወት የሚሰጠውና የሚነሳው፣ የሚጠቅመውና የሚጎዳው እርሱ ብቻ ነው ብሎ ማመን ነው፡፡ የሁሉም ትዕዛዝ ባለቤት እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ መልካም ነገር ሁሉ በእጁ ነው፡፡ እርሱ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ነገሮችም ተጋሪ የለውም ብሎ ማመን ነው፡፡

ይህ እንግዲህ አላህ በተግባሩ ብቸኛ ነው ብሎ ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ እንደሚከተለው ማመን ያስፈልጋል፡-

በፍጥረተ-ዓለሙ ውስጥ ያሉትን ነገሮች የፈጠረው አላህ ብቻውን ነው ከርሱ ሌላ ፈጣሪ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው፡፡” (አል-ዙመር፡62) የሰው ተግባር ግን አንድን ነገር ወደ ሌላ ቅርፅ መቀየር ወይም እርስ በእርሱ ማቆራኘትና የመሳሰሉት እንጂ ከባድና ከምንም ተነስቶ የሚፈጥረው ነገር የለም፡፡ ሙት የሆነውን ነገር ወደ ህይወት ማምጣትም አይችልም፡፡

ለፍጥረታት ሁሉ ሲሳይን የሚሰጠው አላህ ነው፡፡ ከርሱ ውጪ ሲሳይን ሰጪ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “በምድር ላይ ምንም ተንቀሳቃሽ የለችም ምግቧ በአላህ ላይ ቢሆን እንጂ…” (ሁድ፡6)

አላህ የሁሉም ነገር ባለቤት ነው፡፡ ከርሱ ሌላ የነገሮች እውነተኛ ባለቤት የለም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “የሰማያትና የምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፤ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡» (አል-ማኢዳህ፡12ዐ)

የሁሉም ነገር አስተናባሪ እርሱ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ ነገሮችን የሚየሰተናብር የለም፡፡ እንዲህ ይላል…«ነገሩን ሁሉ ከሰማይ ወደ ምድር ያዘጋጃል፡፡» (አል-ሰጅዳህ፡5) ሰው ህይወቱንና ጉዳዮቹን የሚያስተናብረው በተገደበና በተወሰነ መልኩ ነው፡፡ ባለውና በሚችለው ነገር ብቻ ነው የሚያስተናብረው፡፡ ይህ ማስተናበር ደግሞ ውጤታማ ሊሆንም ላይሆን ይችላል፡፡ ከጉድለት የጠራውና የኃያሉ ፈጣሪ ማሰተናበር ግን አጠቃላይ ነው፡፡ ከርሱ ቁጥጥር የሚወጣ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ያለማንምና ያለምንም ተቃውሞ ያሻውን ፈፃሚ ነው፡፡ እንዲህ ይላል “ንቁ፤ መፍጠርና ማዘዝ የርሱ ብቻ ነው፤ የዓለማት ጌታ አላህ (ክብሩ) ላቀ፡፡» (አል-አዕራፍ፡54)

በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘመን የነበሩ አረብ አጋሪዎች በአላህ ጌትነት ያምኑ ነበር፡-

በአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ዘመን የነበሩ ከሃዲያን አላህ፥ ፈጣሪ፣ ንጉሥና አስተናባሪ መሆኑን ያምኑ ነበር፡፡ ይህ እምነታቸው ግን ወደ እስልምና እንዲገቡ አላደረጋቸውም… “ሰማያትንና ምድርንም የፈጠረ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይላሉ፡፡” (ሉቅማን፡25)

አላህ የአለማት ጌታ መሆኑን፣ ፈጣሪ፣ ባለቤትና አስተናባሪ መሆኑን ያረጋገጠ ሰው፣ አላህን በብቸኝነት ሊያመልክ ይገባዋል፡፡ የአምልኮ ተግባራትን ያለማንም ተጋሪ ለርሱ ብቻ ማዋል ይኖርበታል፡፡

አንድ ሰው የፍጥረተ-ዓለሙ ፈጣሪ፣ አስተናባሪ፣ ህይወት ሰጪና ነሺ አላህ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የአምልኮ ዓይነቶችን ከርሱ ውጪ ላሉ ነገሮች ማዋል በጣም የማያስገርም ነገር ነው፡፡ ይህ አስጠያፊ በደልና ታላቅ ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሉቅማን ልጃቸውን ሲመክሩ እንዲህ ያሉት “… ልጄ ሆይ! በአላህ (ጣዖትን) አታጋራ፤ ማጋራት ታላቅ በደል ነውና ያለውን (አስታውስ)፡፡” (ሉቅማን፡13)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) አላህ ዘንድ ታላቅ ወንጀል ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “አላህ ፈጥሮህ ሳለ ለርሱ ተጋሪን ማድረግህ ነው፡፡” በማለት መልሰዋል፡፡ (አል-ቡኻሪ፡4207 ሙስሊም፡86)

በአላህ ጌትነት ማመን ቀልብን ያረጋጋል፡-

አንድ የአላህ ባሪያ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ከሆነ፥ ከኃያሉ አላህ ውሳኔ ውጭ ሊሆን የሚችል ፍጡር እንደሌለ ይገነዘባል፡፡ ምክንያቱም የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት አላህ ሲሆን ከጥበቡ ጋር በሚስማማ መልኩ እንዳሻው የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡ የሁሉም ፈጣሪ እርሱ ነው፡፡ ከአላህ ውጭ ያለው ፍጥረት ሁሉ የተፈጠረና ፈጣሪው ወደ ሆነው አላህ ፈላጊ ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በአላሀ እጅ ናቸው፡፡ ከርሱ ውጭ ፈጣሪ የለም፡፡ ከርሱ ውጭ ሲሳይን ሰጭ የለም፡፡ ከርሱ ሌላ ፍጥረተ-ዓለሙን የሚያስተናብር የለም፡፡ ያለርሱ ፈቃድ የምትንቀሳቀስ ቅንጣት ነገር የለችም፡፡ ያለርሱ ትዕዛዝ የምትቆምም የለችም፡፡ ይህ እምነት ያለው ሰው ቀልቡ በአላህ ላይ ብቻ ይንጠለጠላል፡፡ እርሱን ብቻ ይጠይቃል፣ ከርሱ ብቻ ይፈልጋል፡፡ በሁሉም የህይወት ጉዳዩ የሚመካው በርሱ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ ሁሉንም የህይወት ገጠመኝ በፅናት፣ በቁርጠኝነትና በተረጋጋ መንፈስ ይጋፈጣል፡፡ ምክንያቱም ለህይወቱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት ሁሉንም ሰበብ ከመምከሩ ጎን ለጎን የአላህን እርዳታም ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነቱንም ይወጣል፡፡ ይሄኔ ነፍሱ ትረጋጋለች፡፡ ሰው ዘንድ ያለውን አይከጅልም፡፡ ሁሉም ነገር ያለው በአላህ እጅ ነው፡፡ የሚፈልገውን ይፈጥራል፡፡ ይመርጣልም፡፡

  1. በአላህ አምላክነት ማመን

በኃያሉ አላህ የማመን ትርጉም፡-

ግልፅም ሆነ ድብቅ የአምልኮ ዓይነቶች ሁሉ የሚገቡት ለኃያሉ አላህ ብቻ ነው ብሎ በቁርጠኝነት አምኖ መቀበል ማለት ነው፡ ሁሉንም የአምልኮ ዓይነቶች ለአላህ ብቻ እናውላለን፡፡ ዱዓእን፣ ፍራቻን፣ መመካትን፣ እርዳታ መፈለግን፣ ሶላትን፣ ዘካንና ፆምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአላደህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ የለም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ “አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እርሱ እጅግ በጣም ርኀሩኀ አዛኝ ነው፡፡” (አል-በቀራህ፡163)

አምላክ አንድ ብቻ መሆኑን አላህ ነግሮናል፡፡ ይህ ማለት የሚመለከው አንድ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ከአላህ ሌላ አምላክ ተደርጎ ሊይያዝ የሚገባው ነገር የለም፡፡ ከርሱ ውጭ ማንም አይመለክም፡፡

በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነት፡-

በአላህ አምላክነት የማመን አስፈላጊነትን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግልፅ እንዲሆን ማድረግ፡-

  1. ሰውም ሆነ ጋኔን የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ የተፈጠሩት አላህን በብቸኝነትና ያለምንም ተጋሪ ለመግገዛት ነው፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል…«ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡» (አል-ዛሪያት፡56)
  2. የአላህ መልእክተኞች የተላኩት መለኮታዊ መፅሐፍት የወረዱት ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡ ዓላማቸው በእውነት መመለክ የሚገባው አላህ መሆኑን ለማፅናት ሲሆን ከርሱ ውጭ በሚመለኩ ነገሮች ደግሞ ለመካድ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል… “በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልእክተኛን በእርግጥ ልከናል፤” (አል-ነሕል፡36)
  3. በሰው ልጅ ላይ የመጀመሪያው ግዴታ አላህን በብቸኝነት መገዛት ነው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሙዓዝ ቢን ጀበልን ወደ የመን ለሰበካ በላኩት ጊዜ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነገር ነግረውት ነበር፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት… “የመፅሐፍቱ ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ክርስቲያኖች /አይሁዶች/ ያጋጥሙሃል በመጀመሪያ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለከ አምላክ የለም ወደ ሚለው ቃል ጥራቸው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡1389 ሙስሊም፡19) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ለማለት የፈለጉት “በሁሉም የአምልኮ ዓይነቶች አላህን ብቻ አምልኩ በላቸው፡፡” ለማለት ነው፡፡
  4. “ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም፥ በአላሀ አምላክነት ማመን ነው፡፡ አምላክ ማለት የሚመለክ ማለት ነው፡፡ ከአላህ በቀር በዕውነት የሚመለክ የለም፡፡ ማንኛውም የአምልኮ ዓይነት ከርሱ ውጭ ለማንም አናውልም፡፡
  5. በአላህ አምላክነት ማመን፣ አዕምሮ የሚመራው አሳማኝ የሆነ፣ አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ፣ ባለቤትና አዘጋጅ ነው ብሎ የማመን ውጤት ነው፡፡

 አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው?

አምልኮ (ኢባዳ) ማለት፡- አላህ የሚወደውና የሚደሰትበት እንዲሁም ንግግሮችንና ተግባራትን ሁሉ የሚያጠቃልል ስም ሲሆን ሰዎች ይተገብሩት ዘንድ አላህ ያዘዘው ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር እንደ ሶላት፣ ዘካ፣ ሐጅ ግልፅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አላህንና መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) እንደ መውደድ፣ አላህን እንደ መፍራት፣ በርሱ እንደመመካትና ከርሱ እርዳታን እንደመፈለግ ስውር ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎችም አንደዚሁ፡፡

 

በሁሉም የሀይወት ዘርፍ አላህን ስለማምለክ፡-

ወደ አላህ መቃረብን ዓላማው ያደረገ የማንኛውም አማኝ ሙእሚን ተግባር በአምልኮ ዒባዳ ውሰጥ ይካተታል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት መሠረት አምልኮ በሶላት፣ በፆምና በመሳሰሉ የፀሎት ስነ-ሥርዓቶች የተገደበ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ዓይነት ጠቃሚ ተግባር መልካም የሆነን ዓላማ (ኒያ) እስካነገበ ድረስ፥ የአምልኮ ተግባር እንደሆነ የሚቆጠር ሲሆን ተግባሪውም አላህ ዘንድ ይመነዳበታል፡፡ የአላሀ ትዕዛዝ በአግባቡ ለመፈፀም ይቻል ዘንድ አካላዊ ጥንካሬ ለማግኘት በሚል ዓላማ አንድ ሙስሊም ቢመገብ፣ ቢጠጣና ቢተኛ አላህ ዘንድ ምንዳ ያገኝበታል፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ህይወቱን በሙሉ ለአላህ እያስገዛ ነው ማለት ነው፡፡ አላህን ለመታዘዝ ሰውነቱ ይጠነክር ዘንድ ይመገባል፡፡ በዚህ ዓላማ በመመገቡ አላህን እያመለከ ነው፡፡ ከአመንዝራነት ራሱን ለመጠበቅ በሚል ዓላማ ትዳር ይመሰርታል፡፡ ጋብቻው በራሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንለታል፡፡ ልክ እንደዚሁ ዓላማው ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ንግዱ፣ ሥራው፣ ቢዝነሱ ሁሉ አምልኮ ይሆንለታል፡፡ እውቀት መፈለጉ፣ መመራመሩ፣ መፈላሰፉ፣ መፍጠሩ ሁሉ እንደ አምልኮ ይቆጠርለታል፡፡ አንዲት እንስት ባልዋን፣ ልጆቿንና ቤቷን መንከባከቧ በርሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንላታል፡፡ በሁሉም የህይወት ዘርፍ የሚከናወኑ ጠቃሚ ተግባራት በሙሉ መልካም ዓላማና ዕቅድን መነሻ አድርገው እስከተፈፀሙ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ይቆጠራሉ፡፡

አምልኮ (ዒባዳ) ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡-

አላህ እንዲህ ይላል… “ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡ አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው፡፡” (አል- ዛሪያት፡56-58)

አላህ ሰውንም ሆነ ጋኔን የፈጠረበት ጥበብ እርሱን ይግገዙ ዘንድ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ፍጥረታት አላህን የሚግገዙት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ አላህ ከእነርሱ ጥቅም ፈላጊ ሆኖ አይደለም፡፡

ሰው የተፈጠረበትን መለኮታዊ ይህን ዓላማ ዘንግቶ በዓለማዊ ህይወት ውስጥ ሰጥሞ ከቀረ፥ በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ፍጥረታት የሚለየው ምንም ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንስሳቶች ከሰው በተቃራኒ በቀጣዩ ዓለም ስለሰሩት ሥራ አይጠየቁም እንጂ እነርሱም ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይፈነጥዛሉ፡፡ አላህ እንዲህብሏል… “… እነዚያም የካዱት (በቅርቢቱ ዓለም) ይጠቀማሉ፤ እንስሳዎችም እንደሚበሉ ይበላሉ እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት፡፡” (ሙሐመድ፡12) ተግባርና ዓላማቸው ከእንስሳ ጋር ተመሳስሏል፡፡ ነገርግን ከእንስሳ የሚለያቸው በመጨረሻው ቀን የስራቸውን ውጤት ማግኘታቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ምንም ከማያውቁት እንስሳት በተለየ አዕምሮ ያላቸው፣ የሚገነዘቡና የሚያውቁ በመሆናቸው ነው፡፡

የአምልኮ (ዒባዳ) መሠረቶት

አላህ እንተገብረው ዘንድ ያዘዘን አምልኮ በሁለት ዋና ዋና መሠረቶች ላይ የተገነባ ነው፡-

አንደኛ፡- ሙሉ የሆነ ፍራቻና መተናነስ፡-

ሁለተኛ፡- ሙሉ የሆነ ውዴታን ለአላህ ማዋል፡-

አላህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ያደረገው አምልኮ፥ ለአላህ ብቻ የሚውል ሙሉ የሆነ ፍራቻ፣ መተናነስና ዝቅ ማለትን በውስጡ ያካተተ ከመሆኑ ጎን ለጎን ሙሉ የሆነ ውዴታና ክጃሎትን ለአላህ ብቻ ማዋልን ይጠይቃል፡፡

ስለሆነም ልክ ምግብን ወይም ገንዘብን እንደምንወደው ሁሉ አላህንም ፍራቻና መተናነስን ባላካተተ አኳኋን የምንወደው ከሆነ አምልኮ አይባልም፡፡ ልክ እንደዚሁ አውሬና ጨቋኝ መንግስትን እንደምንፈራው ሁሉ አላህንም ውዴታን ባላጎዳኘ አኳኋን የምንፈራው ከሆነ ከአምልኮ አይቆጠርም፡፡ ሆኖም ግን በስራችን ውስጥ ውዴታንና ፍራቻን ካቆራኘን ትክክለኛ አምልኮን አስገኝተናል፡፡ አምልኮ ደግሞ ሊውል የሚገባው ለአላህ ብቻ ነው፡፡

የአምልኮ ቅድመ ሁኔታዎች፡-

አምልኮ የተስተካከለና አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡

የመጀመሪያው አምልኮን ያለ ምንም ተጋሪ ለአላሀ ብቻ ማዋል ሲሆን

ሌላው ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከአከናወኑት የአምልኮ ተግባር ጋር የሚጣጣምና የሚስማማ መሆን ይኖርበታል፡፡

አላህ እንዲህ ብሏል “አይደለም እርሱ በጎ ሰሪ ሆኖ ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው ለርሱ በጌታው ዘንድ ምንዳው አለው፤ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነሱም አያዝኑም፡፡” (አል-በቀራህ፡112) በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው” ማለት፥ የአላህን አንድነት በተግባር ያረጋገጠና አምልኮን ለርሱ ብቻ ያጠራ ማለት ነው፡፡ “በጎ ሰሪ ሆኖ” የሚለው ደግሞ፥ የአላህን ህግና የመልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) አርዓያነት የሚከተል ማለት ነው፡፡

ሥራን ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና (መንገድ) ጋር ማጣጣም ማለት እንደ ሶላት፣ ፆምና አላህን ማውሳት የመሳሰሉት ተግባራትን እርሳቸው ባከናወኑት መሠረት መፈፀም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ሌሎች የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለጥሩ ዓላማ (ኒያ) እስካከናወናቸው ድረስ ከአምልኮ ተግባራት ተርታ የሚመደቡ ቢሆንም፥ ከአላህ መልእክተኛ ሱንና ጋር የግድ እንዲጣጣሙ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ባይሆን መጠንቀቅ የሚኖርብን ሸሪዓውን የሚቃረን ሐራም ነገር ላይ ላለመውደቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የአላህን ትዕዛዝ ለመተግበር ጠንካራ ያደርገው ዘንድ ስፖርት ቢሰራ ወይም የቤተሰቡንና የልጆቹን ወጪ ለመሸፈን ስራ ቢሰራ ኒያውን እስካሳመረ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ቢቆጠርለትም ከሱንና ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡

 

 ሺርክ (የአምልኮ ተግባርን ከአላህ ዉጪ) ላለ አካል ማጋራት

  • ሺርክ በአላህ አምላክነት ላይ ያለንን እምነት የሚፃረር ነገር ነው፡፡ በአላህ አምላክነት ማመንና የአምልኮ ተግባራትን ለርሱ ብቻ ማዋል ከታላላቅና ወሳኝ ከሆኑ ግዴተዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ መሆኑ እርግጥ ከሆነ፥ ከዚህ በተመሳሳይ መልኩ ለአላህ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ተግባር ለሌላ አካል ማጋራት ደግሞ አላህ ዘንድ የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ንሰሃ ካልገቡ በቀር አላህ በፍፁም የማይምረው ብቸኛ ወንጀል ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “አላህ በርሱ ማጋራትን በፍፁም አይምርም፤ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ በአላህም የሚያጋራ ሰው ታላቅን ኃጢአት በእርግጥ ቀጠፈ፡፡” (አል-ኒሳእ፡48) ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) አላህ ዘንድ ከወንጀሎች ሁሉ ታላቁ ምን እንደሆነ ሲጠየቁ “አላህ ፈጥሮህ ሳለ ለርሱ ተጋሪ ማድረግህ ነው” በማለት መልሰዋል፡፡ (አል-ቡኻሪ፡ 4207 / ሙስሊም፡ 86)
  • በአላህ ማጋራት ስራን በሙሉ ከንቱና ውድቅ ያደርጋል፡፡ አላህም እንዲህ ብሏል፡፡ … “…ባጋሩም ኖሮ ይሠሩት የነበሩት ከነርሱ በታበሰ ነበር፡፡” (አል-አንዓም፡88) በአላህ አጋርቶ ንሰሃ ሳይገባ የሞተ ሰው ዕጣፈንታው ዘላለም በጀሃነም እሳት መቀጣት ይሆናል፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡፡ …”እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (አል-ማኢዳህ፡72)

ሺርክ ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ ታላቅና ታናሽ

  1. ታላቁ ሺርክ፡- ይህ ማለት አንድን የአምልኮ (ዒባዳ) ዓይነት ከአላህ ውጪ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ አንድ አላህ የሚወደውን ንግግርም ሆነ ተግባር ለአላህ ብቻ ካዋልነው አንድነቱን አፀደቅን ወይም አመንበት ማለት ነው፡፡ ይህን ተግባር ከርሱ ሌላ ለሆነ አካል ካዋልነው ደግሞ፥ ክደነዋል አጋርተንበታል፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ የሺርክ ተግባር ምሳሌን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ከአላህ ውጪ ያለን አካል ከህመም እንዲያሽረን፣ ሲሳይን እንዲያሰፋልን ከጠየቅነውና ከለመንነው በታላቁ የሺርክ ተግባር ላይ ወድቀናል ማለት ነው፡፡ ከአላህ ውጪ ለሆነ ነገር ብንሰግድ ወይም በርሱ ላይ ብንመካም እንደዚያው ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል … “ጌታችሁም አለ፡- ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና፤ እነዚያ እኔን ከመገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ሆነው ገሃነምን በእርግጥ ይገባሉ፡፡” (አል-ሙእሚን፡60) እንዲህም ይላል … “… ምእምናንም እንደ ሆናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ አሉ፡፡” (አል-ማኢዳህ፡23) ሌላ ሱራ ላይም እንዲህ ብሏል…”ለአላህም ስገዱ ተገዙትም፡፡” (አል ነጅም፡ 62) እነዚህን ተግባራት ከአላህ ሌላ ላለ አካል ያዋለ ሰው አጋሪ እንዲሁም ከሃዲ ይሆናል፡፡
  2. ትንሹ ሺርክ፡- ይህ ደግሞ ወደ ታላቁ ሺርክ ሊያደርስ የሚችል ንግግር ወይም ተግባር ነው፡፡ ትንሹ ሺርክ ታላቁ ሺርክ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ ለዚህኛው የሚሆን ምሳሌ መጥቀስም ይቻላል፡- ሰው አንዲያይለት በማሰብ ሶላትን ማስረዘም ወይም ሰዎች እንዲያደንቁት በማሰብ ቁርኣን ሲያነብ ወይም አላህን ሲዘክር ድምፁን ማድረግና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) “እኔ ለእናንተ በጣም ከምፈራላችሁ ነገር ውስጥ አንዱ ትንሹ ሺርክ ነው፡፡” በማለት ሲናገሩ ሰሃቦችም “አንቱ የአላህ መልእክተኛ ትንሹ ሺርክ ምንድ ነው?” በማለት ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም “የይዩልኝ ስራ ነው፡፡” በማለት መልስ ሰጡ (አህመድ፡2363) ሆኖም ግን ፍፁም ለሰው ተብሎ የሚደረግ የአምልኮ ተግባር ሶላትም ሆነ ፆም የመናፍቅ ሥራ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ከእስልምና ሃይማኖት ውጪ የሚያደርግ ታላቅ የሺርክ ተግባር ነው፡፡

 

ከሰው መፈለግና ሰውን አንዳንድ ነገር መጠየቅ የሺርክ ተግባር ነውን?

ከሰው መፈለግና ሰውን አንዳንድ ነገር መጠየቅ የሺርክ ተግባር ነውን?

የእስልምና ሃይማኖት የተደነገገው የሰውን አዕምሮ ከንቱ ከሆኑ እምነቶች ነፃ ለማውጣት ነው፡፡ የተደነገገው የሰው ልጅ ከአላህ ውጪ ላለ አካል ዝቅ እንዳይል ነው፡፡

ለሙታንም ሆነ ግዑዝ ለሆኑ አካላት ዝቅ ብሎ በመተናነስ ፍላጎትን መጠየቅ ህገ-ወጥ የሆነ ተግባር ነው፡፡ ይህ ከንቱ እምነትና ሺርክ ነው፡፡

ነገር ግን አጠገባችን ያለንና ህይወት ያለውን ሰው አቅሙ የሚችለውን ነገር እንዲያደርግልን ብንጠይቀው ወንጀል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ውሃ ውስጥ የሰጠመ ሰው ህይወቱን ያተርፈው ዘንድ ሰውን መጠየቁ፣ ወይም አንድ ሰው ዱዓእ እንዲያደርግልን ብንጠይቅ እስልምና የሚፈቅደው ህጋዊ ተግባር ነው፡፡

ሙታንን ወይም ግዑዝ አካላትን መከጀልና መማፀን የሺርክ ተግባር ነውን?
አዎን
ይህ ግልጽ አይደለም ኢማንን የሚቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም ሙታንና ግዑዛን ነገሮች፣ ጥያቄውን መስማትም ሆነ ምላሽ መስጠት አይችሉም፡፡ ልመና (ዱዓ) አምልኮ ነው። በመሆኑም ከአላህ ሌላ ለሆነ አካል አሳልፎ መስጠት ማጋራት ነው፡፡ ግልጽ አይደለም በታወጀበት ዘመን የነበሩ ዐረቦች ያጋሩ የነበሩት ግዑዛንንና ሙታንን በመለመን ነበር፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ሕያው ሆኖ ጥያቄህንና ልመናህን ሊሰማ የሚችልን አካል መለመንህና መጠየቅህ፡፡ እርሱ በሚችለው ነገር ላይ እንዲረዳህና እንዲያግዝህ በጠየቅከው ዓይነት? ልመናህን ለመመለስና ጥያቄህን ለመስማት ይችላልን?
አዎን
ይህ ተገቢ ልመና ነው፡፡ ምንም ችግር የለውም፡፡ በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነትና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ከሚከሰቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ከሕያው ሰው እርሱ የማይችለውን ነገር ከርሱ መፈለግ ወይም መከጀል ማለት አንድ መውለድ የማይችል መካን፣ ከሕያው ሰው ፃድቅ ልጅ እንዲሰጠው እንደመለመን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከኢስላም ጋር የሚቃረን ትልቁ የማጋራት ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ከአላህ ሌላ ያለን አካል መለመን ነውና፡፡