በአላህ ስሞችና ባህሪያት ማመን፡-
ይህ ማለት፥ አላህ በመፅሐፉ ውስጥ ወይም መልእክተኛው በስሱናቸው ያፀደቁትንና አላህ እራሱን የሰየመበትን ስም እንዲሁም ማንነቱን የገለፀበትን ባህሪ ለአላህ በሚገባው መልኩ ማመን ማለት ነው፡፡
ከጉድለት የጠራ የሆነው አላህ ምርጥ የሆኑ ስሞችና ሙሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት፡፡ በስሙም ሆነ በባህሪያቱ ፍፁም አምሳያ የሌለው ጌታ ነው፡፡ እንዲህ ይለናል “የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱም ሰሚው ተመልካቱ ነው፡፡” (አል-ሹራ፥11)
አላህ በሁሉም ስሞቹና ባህሪያቱ ከየትኛውም ፍጡር ጋር ፍፁም የማይመሳሰልና የጠራ ነው፡፡
ከአላህ ስሞች ውስጥ የተወሰኑት፡-
አላህ እንዲህ ይላል “እጅግ በጣም ርኀሩኀ በጣም አዛኝ” (አል-ፋቲሐህ፡3)
አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡” (አል ሹራ፡11)(አል ሹራ 11)
አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡” (ሉቅማን፡9) አላህ እንዲህ ይላል “አላህ ከርሱ በቀር ሌላ አምላከ የለም፤ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፤” (አል-በቀራህ፡ 255)
አላህ እንዲህ ይላል “ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለሆነው፡፡” (አል-ፋቲሐህ፡2)
በአላህ ስሞችና ባህሪያት የማመን ፍሬዎች፡-
-
ኃያሉ አላህን ያሳውቀናል፡- በአላህ ስሞችና ባህሪያት ያመነ ሰው ስለ አላህ ያለው እውቀት ይጨምራል፡፡ በአላህ ላይ ያለው እርግጠኛ እምነትም ይጨምራል፡፡ ስለ አላህ አንድነት ያለው ዕምነት ይጠነክራል፡፡ የአላህን ስሞችና ባህሪያት ያወቀ ሰው፥ ቀልቡ በአላህ ታላቅነት፣ ውዴታና አክብሮት መሞላቱ የግድ ነው፡፡
-
አላህን በስሞቹ ማወደስ እንችላለን፡፡ ይህ ምርጥ ከሆኑ የዚክር (የውዳሴ) ዓይነቶች ውስጥ ይካተታል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብዙ ማውሳትን አውሱት፡፡” (አል-አሕዛብ፡ 41)
-
ስምና ባህሪውን ካወቅን፥ በስሞቹና በባህሪያቱ ልንማፀነው አንችላለን፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ለአላህም መልካም ስሞች አሉት ስትፀልዩም በርሷም ጥሩት” (አል-አዕራፍ፡ 180)በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፡- አንተ ሲሳይን ሰጪ ሆይ! ሲሳይን ስጠኝ፡፡ አንተ ይቅር ባይ ሆይ! ይቅር በለኝ፡፡ አንተ አዛኝ ሆይ! እዘንልኝ… ማለት እንችላለን፡፡
ከፍ ያሉ የእምነት ደረጃዎች፡-
እምነት የተለየዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ የአንድ ሙስሊም እምነት መዘንጋቱንና ሐጢአቱን መነሻ አድርጎ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ለአላህ ባለው ታዛዥነት፣ አምልኮና ፍራቻ ልክ እምነቱ ይጨምራል፡፡
የእምነት ከፍተኛው ደረጃ ሸሪዓው እንዳለው «ኢህሣን» በሚል ይተወቃል፡፡ ስለ «ኢህሣን» ምንነት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል… “አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና፥ አላህን ስትገዛው እያየኸው እንደምትገዛው ሆነህ ተገዛው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡50 ሙስሊም፡8)
ቆመህም ሆነ ተቀምጠህ፣ በደስታም ሆነ በሃዘን ወቅት በአጠቃላይ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆነህ አላህን ማስታወስ ይኖርብሃል፡፡ አላህ ምንግዜም በቅርበት ይመለከትሃል፡፡ እየተመለከተህ መሆኑን ካወቅህ ወንጀል አትፈፅምም፡፡ እርሱ ካንተ ጋር መሆኑን የምታውቅ ከሆነ ፍርሃትም ሆነ ተስፋ መቁረጥ አይቆጣጠሩህም፡፡ በእርግጥ አላህን በሶላትህና በዱዓህ አያናገርከው ብቸኝነት ሊሰማህ አይችልም፡፡
የሰወርከውንም ግልፅ ያደረግከውንም አላህ እንደሚየውቅ እየተገነዘብክ ነፍስህ ወደ ኃጢአት ልትገፋፋህ አትችልም፡፡ኃጢአት ላይ ተዳልጠህና ተሳስተህ ከወደቅህ ደግሞ ወደ አላህ በመመለስ ምህረቱን ትማፀነዋለህ እርሱም ይምርሃል፡፡
አላህን የማመን ፍሬዎች፡-
-
አላህ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ለምእመናን ይከላከልላቸዋል፡፡ ከጭንቅ ያድናቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላሀ እንዲህ ይላል “አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡” (አል-ሐጅ ፡ 38)
-
በአላህ ላይ የሚኖረን እምነት መልካም የሆነን ህይወት፣ ደስታንና ፍስሃን ያጎናፅፋል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል … “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤” (አል-ነሕል፡97)
-
እምነት ነፍስን ከከንቱ እምነቶች ፅዱ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው፥ ጉዳዩን ሁሉ ለአንድ አላህ ብቻ ይተዋል፡፡ እርሱ የዓለማት ጌታ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ እውነተኛ አምላክ የለም፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው ፍጡርን አይፈራም፡፡ ማንንም ሰው በቀልቡ አይከጅልም፡፡ ከዚህም በላይ ከንቱና አላስፈላጊ ከሆኑ እምነቶች ራሱን ነፃ ያደርጋል፡፡
-
የኢማን ከፍተኛ ተፅዕኖ፡- የአላህን ውዴታ ያስገኛል፡፡ ጀነት ያስገባል፡፡ ቋሚና ዘላለማዊ ለሆነ የፀጋ ስኬት ያበቃል፡፡ ሙሉ የአላህ እዝነትን ያስገኛል፡፡
በመላእክት ማመን
በመላእክት የማመን ትርጓሜ
.ይህ የመላእክትን መኖር፣ እነርሱ ከሰው ዘርም ከአጋንንትም ዓለም ያልሆኑ የስውር ዓለም ፍጡራን እንደሆኑ በቁርጠኝነት ማጽደቅ ነው፡፡ እነርሱ የተከበሩና አላህን ፈሪዎች ናቸው፡፡ አላህን ትክክለኛ የሆነ መገዛትን ይገዙታል፡፡ እርሱ ያዘዛቸውን በመፈፀም ያስተናብራሉ፡፡ በአላህ ላይ ፈፅሞ አያምጹም፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «(መላእክት) የተከበሩ ባሮች ናቸው፡፡ በንግግር አይቀድሙትም (ያላለውን አይሉም) እነሱም በትዕዛዙ ይሰራሉ፡፡» (አል አንቢያ 26-27)
በእነሱ ማመን ከኢማን ስድስት መሠረቶች አንዱ መረት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «መልክተኛው ከጌታው ወደርሱ በተወረደው አመነ፡ ምዕመናኖችም (እንደዚሁ) ሁሉም በአላህ በመላእክቱም በመጻሕፍትቱም በመልክተኞቹም…. አመኑ፡፡» (አል በቀራ 285) ኢማንን አስመልክተው ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍት፣ በመልዕክተኞች፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)
በመላእክት ማመን ምንን ያካትታል?
- በመኖራቸው ማመን፡ እነርሱ የአላህ ፍጥረታት እንደሆኑ እናምናለን፡፡ በተጨባጭ ያሉ ናቸው፡፡ አላህ የፈጠራቸው ከብርሃን ነው፡፡ እርሱን በመገዛትና በመታዘዝ ላይ አግርቷቸዋል፡፡
- ከነርሱ መካከል እንደ ጂብሪል (ዐ.ሰ) በስሙ ያወቅነውን እስከነስሙ እናምናለን፡፡ በስማቸው ያላወቅነውናቸውንም በጥቅሉ እናምንባቸዋለን፡፡
- ከባህሪያቸው በምናውቀው ማመን፡፡ ከባህሪያቸው መካከል፡
እነርሱ የስውር ዓለም ፍጥረታት መሆናቸው፡፡ ለአላህ የሚገዙ ፍጡራን ናቸው፡፡ ከቶም የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ባህሪ የላቸውም፡፡ እንደውም እነሱ አላህን ለመታዘዝ ሙሉ በሙሉ የተገሩ የአላህ ባሮች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ያዘዛቸውን በመጣስ አያምጡም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሰራሉ፡፡» (አል ተህሪም 6)
የተፈጠሩት ከብርሃን ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «መላእክት ከብርሃን ተፈጠሩ፡፡» ሙስሊም 2996
ክንፎች አሏቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለመላእክት ክንፍን እንዳደረገ ተናግሯል፡፡ የክንፎቻቸው ብዛት ይበላለጣል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሦስት ሦስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፤ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና፡፡» (ፋጢር 1)
- በአላህ ትዕዛዝ መሰረት እነርሱ ከሚያከናውኗቸው ስራዎቻቸው ባወቅነው ማመን፡፡ ከነርሱ መካከል፡-
መለኮታዊ ራዕይን ወደ መልክተኞች በማምጣት የተወከለ አለ፡፡ እሱም ጂብሪል (ዐ.ሰ) ነው፡፡
ነፍስን በማውጣት የተወከለም አለ፡፡ እርሱም የሞት መልአክና ተባባሪዎቹ ናቸው፡፡
መልካምም ሆነ እኩይ፣ የባሮችን ስራ መዝግቦ በማቆየት ወይም በመጠበቅ የተወከሉ አሉ፡፡ እነሱም የተከበሩ ፀሐፍት መላእክት ናቸው፡፡
በመላእክት የማመን ፍሬ ወይም ጥቅም፡፡
በመላእክት ማመን በሙእሚን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ከነኚህ ጥቅሞች መካከል የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፡፡
የአላህን ልቅና፣ ኃይል፣ ሙሉዕነትና ችሎታ ያሳውቃል፡፡ የፍጥረታት ትልቅነት የፈጣሪያቸውን ትልቅነት ያሳያል፡፡ በመሆኑም አንድ ሙዕሚን በመላእክት በማመኑ ለአላህ የሚሰጠው ደረጃና ለርሱ ያለው ከበሬታ ይጨምራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ብዙ ክንፎች ያሏቸው መላዕክትን ከብርሃን የፈጠረ ነው፡፡
-
አላህን በመታዘዝ ላይ ጽናትን ያጎናጽፋል፡፡ መላዕክት ስራዎቹን በሙሉ እንደሚፅፉ የሚያምን ሰው፣ ይህ እምነቱ የአላህ ፍራቻ እንዲያድርበት ያደርጋል፡፡ በይፋም ሆነ በድብቅ በአላህ ላይ አያምጽም፡፡
-
አንድ አማኝ በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ አላህን የሚታዘዙ መላእክት አብረውት በተሟላና ባማረ መልኩ እንዳሉ በእርግጠኝነት በሚረዳ ጊዜ አላህን የመታዘዝ ትዕግስትን ይላበሳል፡፡ መላመድንና መረጋጋትን ያገኛል፡፡
-
ከመላእክት መካከል የሚጠብቋቸውና የሚከላከሉላቸው በማድረግ አላህ ለአደም ልጆች በቸረው ትኩረቱና ክትትሉ ማመሰገን፡፡
በመጽሕፍት ማመን
በመጽሐፍት የማመን ትርጓሜ
አላህ (ሱ.ወ) በመልክተኞቹ ላይ ወደ ባሮቹ ያወረዳቸው መጽሐፍት እንዳለው፣ እነኚህ መጽሐፍት በሙሉ የአላህ ቃልና ንግግር እንደሆኑ ማመን ነው፡፡ ለክብርና ልቅናው ተገቢ በሆነ መልኩ በርግጥ ተናግሯል፡፡ እነኚህ መጽሐፍት በውስጣቸው ለሰው ልጅ፣ ለሁለቱም ዓለም የሚሆን መመሪያና ብርሃን የያዙ እውነቶች ናቸው ማለትን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ፡፡
በመጽሐፍት ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ማዕዘን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በአላህና በመልክተኛው፣ በዚያም በመልክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በዚያም ከበፊቱ ባወረደው መጽሐፍ እመኑ፡፡» (አል ኒሳእ 136)
አላህ (ሱ.ወ) በርሱ በመልዕክተኛው ላይ ባወረደው መጽሐፍ፣ በቁርኣን እንድናምን አዟል፡፡ ከቁርኣን በፊት በተወረዱ መጽሐፍት ማመንን አዟል፡፡
ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኢማንን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡- «በአላህ፣ በመላእክቱ፣ በመጽሐፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)
በመጽሕፍት ማመን ምንን ያካትታል?
- ከአላህ በትክክል የተወረዱ በመሆናቸው ማመን
- የአላህ ቃል (ንግግር) መሆናቸውን ማመን
- በነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ላይ እንደተወረደው ቁርኣን፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንተወረደው ተውራት፣ በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ እንደተወረደው ኢንጂል ዓይነት አላህ በስም የጠራቸውን በስማቸው ማመን፡፡
- ከዜናዎቻቸው፣ በትክክለኛ ዘገባ የደረሱንን በእውነተኝነታቸው ማመን፡፡
የቁርኣን ልዩ መገለጫዎች
የተከበረው ቁርኣን በነብያችንና በአርአያችን በሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ የተወረደ የአላህ ቃል ነው፡፡ በመሆኑም ሙእሚን ይህን” መጽሐፍ በእጅጉ ያልቀዋል፡፡ ድንጋጌዎቹን ለመተግበርና አንቀፆቹን እያስተነተነ ለማንበብ ይጥራል፡፡
ይህ ቁርኣን በቅርቢቱ ዓለም መመሪያችን፣ በመጨረሻው ዓለም የስኬታችን ሰበብ መሆኑ ብቻ ልዩ ለመሆን ይበቃዋል፡፡
የተከበረው ቁርኣን በርካታ መለያዎች አሉት፡፡ ከቀደሙት መለኮታዊ መጽሐፍት የሚነጥሉት የርሱ ብቻ የሆኑ የተለያዩ መገለጫዎችም አሉት፡፡ ከነኚህም መካከል፡-
- የተከበረው ቁርኣን የአምላክን ድንጋጌ ማጠቃለያ የያዘ መሆኑ፡፡ በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ያለውን፣ አላህን በብቸኝነት የመገዛት ትዕዛዝን የሚያጠናክር ኾኖ ነው የመጣው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በውነት አወረድን» (አል ማኢዳ 48) «ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭ» ማለት በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ከተነገሩ ዜናዎች፣ ከተላለፉ የእምነት አመለካከቶችና ጉዳዮች ጋር የሚስማማና የማይቃረን ማለት ነው፡፡ «በርሱ ላይ ተጠባባቂ» የሚለው ደግሞ ከርሱ በፊት የነበሩ መጽሐት ላይ የሚመሰክርና በአደራ የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡
- እነሆ የሰው ልጆች በሙሉ በቋንቋና በጎሳ መለያየታቸው እንዳለ ሆኖ፣ ዘመናቸው ምንም እንኳ ከቁርኣን መወረድ በኋላ የመጣ ቢሆንም እርሱን የመከተል፣ እርሱ ያቀፈውን የመተግበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ቀደምት መጽሐፍት ግን የተወረዱት ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለተወሰኑ ሕዝቦችና በተወሰነ ዘመን ላይ ነበር፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ (በል)፡፡» (አል አንዓም 19)
- አላህ (ሱ.ወ) የተከበረውን ቁርኣን የመጠበቁን ኃላፊነት ለራሱ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም የመቀየር፣ የመደለዝ፣ የመከለስና የመበረዝ እጅ አልተሰነዘረበትም፡፡ ወደፊትም ለመቼውም አይዘረጋበትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፤ እኛም ለርሱ ጠባቂዎቹ ነን፡፡» (አል ሒጅር 9) ሰለሆነም በውስጡ ያሉ ዜናዎች በሙሉ ትክክለኛ ናቸው፡፡ ልንቀበለውም የግድ ይላል፡፡
በቀደምት መጽሐፍት ውስጥ ስላለ ነገር ሊኖረን የሚገባ አቋም ምንድን ነው?
አንድ ሙስሊም፣ በነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት፣ በነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል፣ በትክክል ከአላህ ዘንድ የተወረዱ እንደነበሩ ያምናል፡፡ ሁለቱም በውስጣቸው ለሰው ልጆች ለዚች ዓለምና ለወዲያኛው ዓለም ሕይወታቸው መመሪያና ብርሃን የያዙ፣ ተግሳጻትን እንዲሁም ድንጋጌዎችንና ዜናዎችን አቅፈው የነበሩ መሆናቸውን ያምናል፡፡
ነገር ግን አላህ (ሱ.ወ) በቁርኣን ውስጥ የመጽሐፍት ባለቤት የሆኑት አይሁዶችና ክርስቲያኖች፣ መጽሐፍታቸውን እንደበረዙና እንዳበላሹ፣ ከመጽሐፍ ያልሆነን ነገር በውስጡ እንደጨመሩ፣ ከነበረውም እንደቀነሱ ነግሮናል፡፡ በመሆኑም በወረዱበት ይዘት ላይ አልቆዩም፡፡
አሁን ያለው ተውራት፣ በሙሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ተውራት አይደለም፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች አጣመውታል፤ ለውጠውታል፡፡ በርካታ ድንጋጌዎቹን ተጫውተውበታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከነዚያ አይሁዳውያን ከሆኑት ሰዎች ንግግሮችን ከስፍራዎቹ የሚያጣምሙ አሉ፡፡» (አል ኒሳእ 46)
አሁን ያለው ኢንጂልም ቢሆን በዒሳ(ዐ.ሰ) ላይ የተወረደው ኢንጂል አይደለም፡፡ ክርስቲያኖችም ኢንጂልን አጣመውታል፡፡ በርካታ በውስጡ የነበሩ ድንጋጌዎችን ለውጠዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ክርስቲያኖችን በማስመለከት እንዲህ ብሏል፡- «ከነሱም እርሱ ከመጽሐፉ ያላደለ ሲኾን ከመጽሐፉ መኾኑን እንድታስቡ በመጽሐፉ ምላሶቻቸውን የሚያጣምሙ ክፍሎች አሉ፡፡ እርሱ ከአላህ ዘንድ ያልኾነ ሲኾን እርሱ ከአላህ ዘንድ ነውም ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁ ሲኾኑም በአላህ ላይ ውሸትን ይናገራሉ፡፡» (አለ ዒምራን 78)
«ከነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተዉ፤ ስለዚህ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው አላህም ይሰሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡» (አል ማኢዳ 14)
ዛሬ በመጽሐፍት ባለቤቶች እጅ የሚገኘው፣ ተውራትንና ኢንጂልን አካቷል ብለው የሚያምኑበት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውስጡ በርካታ ብለሹ የእምነት አመለካከቶችንና ትክክለኛ ያልሆኑ ዜናዎችን፣ እንዲሁም የውሸት ትረካዎችን ይዟል፡፡ ስለሆነም ከዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቁርኣን ወይም ትክክለኛ የሐዲስ ዘገባ እውነትነቱን ያጸደቀውን በስተቀር እውነት ብለን አናምንበትም፡፡ ቁርኣንና ሀዲስ ያስተባበሉትን ደግሞ እናስተባብላለን፡፡ ከዚህ ውጭ የሆነውን በዝምታ እናልፋለን፡፡ እውነት ብለን አናጸድቅም ውሸት ነው ብለንም አናስተባብልም፡፡
እንዲህ ከመሆኑም ጋራ፣ አንድ ሙስሊም እነኚህን መጽሐፍት አያንኳስስም፤ አያራክስም፣ ምክንያቱም ምናልባት በውስጣቸው ያልተበረዘና ያልተለወጠ የአላህ ንግግር ቅሪት ሊኖር ይችላል፡፡
በመጽሐፍት የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ
በመጽሐፍት ማመን በርካታ ጥቅሞች ወይም ፍሬዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጥቅሞች መካከል፡
አላህ (ሱ.ወ) ከምእመናን ላይ አደጋን በጠቅላላ ይመክታል፡፡ ከመከራና ስቃይ ውስጥ ያወጣቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡» (አል-ሐጅ፡ 38)
አላህ በድንጋጌዎቹ ውስጥ ያለውን ጥበብ ወይም ምክንያታዊነት ማወቅ፡፡ ይኸውም ለያንዳንዱ ሕዝብ ተጨባጭ ሁኔታውን የሚመጥንና ከባህሪው የሚስማማ የሆነ የራሱ ልዩ ድንጋጌ የደነገገለት መሆኑ ነው፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፡» (አል ማኢዳ 48)
-
እነኚህን መጽሐፍት በማውረድ ለተከሰተው የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ፡፡ እነኚህ መጽሐፍት በዱንያም በኣኺራም ብርሃንና መመሪያ ናቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳችን ለዚህ ታላቅ የአላህ ጸጋ ምስጋና ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡