በመልዕክተኞች ማመን

የሰው ልጅ መለኮታዊ መልዕክት ያስፈልገዋል፡፡

ለሰው ልጆች ሕግጋትን የሚያብራራላቸውና ወደ ትክክለኛው ጎዳና የሚመራቸው ከጌታ የሆነ መልዕክተኛ ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ መለኮታዊ መልዕክት የዓለም እስትንፋስና የሕይወት ብርሃን ነው፡፡ መንፈስ፣ ሕይወትና ብርሃን የሌለው ዓለም እንዴት ዓይነት ሕልውና ሊኖረው ይችላል?

አላህ (ሱ.ወ) መልክቱን ሩሕ ሲል የሰየመው ለዚህ ነው ፡፡ ሩሕ ከሌለ ሕይወት የለም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እንደዚሁም ወደ አንተ ከትዕዛዛችን ሲኾን መንፈስን (ቁርኣንን) አወረድን፡፡ መጽሐፉም እምነቱም ምን እንደሆነ የምታውቅ አልነበርክም፡፡ ግን (መንፈሱን) ከባሮቻችን የምንሻውን ሰው በርሱ የምንመራበት ብርሃን አደረግነው፡፡ አንተም ወደ ቀጥተኛው መንገድ በርግጥ ትመራለህ፡፡» (አል ሹራ 52)

ይኸውም የሰው ልጅ አዕምሮ በጥቅሉ ጠቃሚና ጎጂ ነገሮችን መለየት የሚችል ቢሆንም፣ በመልዕክተኞች አማካይነት ካልሆነ በስተቀር በረቀቀ መልኩ መጥፎውንና መልካሙን የሚለይበት መንገድ አይኖረውም፡፡

በሁለቱም ዓለም ደስታም ሆነ ስኬት ሊገኝ የሚችልበት መንገድ በመልዕክተኞች እጅ የሚገኘው ብቻ ነው፡፡ ክፉና ደጉንም በረቀቀ መልኩ የሚለየው መንገድ የነርሱ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ፣ መልዕክተኞች ካስተላለፉት መልዕክት ጀርባውን የሰጠ ሰው ለመልዕክቱ ተቃራኒ በሆነበትና ጀርባውን በሰጠበት ልክ አለመረጋጋት፣ ጭንቀትና መረበሽ ያገኘዋል፡፡

በመልዕክተኞች ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡

በመልዕክተኞች ማመን ከስድስቱ የኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «መልዕክተኛው ከጌታው ወደ እርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእመናንም (እንደዚሁ)፤ ሁሉም ‌በአላህ፤ በመላዕክቱም፤ በመጽሐõፍቱም፣ ከመልዕክተኞቹ በአንድም መካከል አንለያይም (የሚሉ ሲሆኑ ) አመኑ፡፡» (አልበቀራ 285)

አንቀጹ፣ በመልዕክተኞች መካከል ምንም ሳይለያዩ በሁሉም ማመን ግዴታ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ አይሁዶችና ክርስቲያኖች እንዳደረጉት በከፊሎቹ አምነን በከፊሎቹ አንክድም፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የኢማን ማዕዘናትን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፡- «በአላህ በመልአኮች፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀንና በክፉም በደጉም በአላህ ውሳኔ ልታምን ነው፡፡» (ሙስሊም 8)

በመልዕክተኞች የማመን ትርጓሜ

አላህ (ሱ.ወ) በእያንዳንዱ ሕዝብ ውስጥ ከነርሱው የሆኑ፣ አላህን በብቸኝነት ወደ መገዛት የሚጣሩና ለርሱ ተጋሪ እንደሌለው የሚያስተምሩ መልዕክተኞችን የላከ መሆኑን በቁርጠኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ መልዕክተኞች ሁሉም እውነተኞችና እውነተኝነታቸው በአምላክ የተረጋገጠ ነው፡፡ አላህን በእጅጉ የሚፈሩና ታማኞች ናቸው፡፡ ወደ ትክክለኛው ጎዳና የተመሩና የሚመሩ ናቸው፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እነርሱን የላከበትን ነገር በሙሉ አድርሰዋል፡፡ ከርሱ ምንም የደበቁትም ሆነ የቀየሩት ነገር የለም፡፡ ከራሳቸው ዘንድ አንዲትም ፊደል በውስጡ አልጨመሩም አልቀነሱምም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በመልዕክተኞቹም ላይ ግልጽ ማድረስ ብቻ እንጂ ሌላ የለባቸውም፡፡» (አል ነሕል 35)

በመልዕክተኞች ማመን ምንን ያካትታል?

  1. መልዕክታቸው በትክክልና በቀጥታ ከአላህ ዘንድ ነው የተላለፈው ብሎ ማመን፡፡ የመልዕክተኞች ሁሉ ጥሪ፣ አላህን ያለአጋር በብቸኝነት ወደ ማምለክ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በየ ሕዝቡም ሁሉ ውስጥ አላህን ተገዙ ጣዖትንም ራቁ በማለት መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል::» (አል ነህል 36)

በርግጥ የየነብያቱ ደንብና ስርዓት ንዑስ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊለያይ ይችላል፡፡ ከነኚያ ከተላኩባቸው ሕዝቦች አንጻር የተፈቀዱና የተከለከሉ ነገሮች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከናንተ ለሁሉም ህሕግና መንገድን አደረግን፡፡» (አል ማኢዳ 48)

  1. በነብያትና በመልክተኞች በሙሉ ማመን፡፡ አላህ በስማቸው የነገረንን ከነስማቸው እናምንባቸዋለን፡፡ ለምሳሌ ሙሐመድ፣ ኢብራሒም፣ ሙሳ፣ ዒሳ፣ ኑሕ (ዐለይሂሙ ሰላም) …. ከነሱ መካከል ስማቸውን የማናውቃቸውን ደግሞ በጥቁሉ እናምንባቸዋለን፡፡ ከነሱ መካከል አንዱን የካደ ሁሉንም ክዷል፡፡
  1. በቁርኣንና በሐዲስ የተጠቀሱ የመልዕክተኞችን ገድልና ተዓምራት እውነት ነው ብሎ መቀበል፡፡ ለምሳሌ ለነብዩላህ ሙሳ (ዐ.ሰ) ባሕሩ የተሰነጠቀላቸው መሆኑን ማመን፡፡
  1. ወደ እኛ የተላኩትን መልዕክተኛ ህግና ስርዓት መተግበር፡፡ እሳቸውም ከሁሉም በላጩና መቋጫ የሆኑት ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡

የመልዕክተኞች መገለጫ

  1. መልዕክተኞች የሰው ዘር ናቸው፡፡ በነሱና በሌላው ሰው መሐከል ያለው ልዩነት፣ አላህ (ሱ.ወ) በመለኮታዊ ራዕይና መልዕክት የመረጣቸው መሆኑ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከአንተም በፊት ወደ እነሱ የምናወርድላቸው የኾኑ ሰዎችን እንጂ ሌላን አልላክንም፡፡» (አል አንቢያእ 7) የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ደረጃ የላቸውም፡፡ ነገር ግን በውጫዊ ተክለ ሰውነታቸው ምንም እንከን የሌላቸው፣ የሙሉዕነትን ደረጃ የደረሱ ሲሆን በስ-ነምግባራቸውም በሙሉዕነት የመጨረሻውን ጣራ የነኩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በጎሳቸውም የተከበረ ጎሳ አባል ናቸው፡፡ እንዲሁም ብሩህ አዕምሮና ማራኪ ልሳን የተቸሩ ናቸው፡፡ ይህም የመልዕክቱን ውጣ ውረድ በአግባቡ እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል፡፡ የነብይነትን ፈተናም በብቃት እንዲወጡ አግዟቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) መልዕክተኞችን ከሰው ዘር ያደረገበት ምክንያቱ የሰዎች ተምሳሌቶች ከራሳቸው እንዲሆን ነው፡፡ በመሆኑም መልዕክተኞችን መከተልና እነርሱን በተምሳሌትነት መያዝ በሰዎች ሊከናወን የሚችልና በችሎታቸው ስር ያለ ጉዳይ ነው፡፡
  2. አላህ (ሱ.ወ) መልዕክቱን በማስተላለፉ ለይቷቸዋል፡፡ ከሌላው ሰው ነጥሎ እነርሱን መለኮታዊ ራዕዩን እንዲረከቡ መርጧቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት ወደ እኔ የሚወረድልኝ ቢጢያችሁ ሰው ብቻ ነኝ፡፡» (አል ካሕፍ 110) የነብይነት ማዕረግም ሆነ መለኮታዊ መልዕክት፣ በመንፈሳዊ ምጥቀት ወይም በጮሌነት ወይም በአዕምሮ ብስለት የሚያገኝ ነገር አይደለም፡፡ እሱ የአላህ መምረጥና ማጨት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከሰዎች መካከል መልዕክተኞችን መርጦ አጭቷቸዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ መልክቱን የሚያደርግበትን ስፍራ ዐዋቂ ነው፡፡» (አል አንዓም 124)
  1. እነርሱ ከአላህ በሚያስተላልፉት መልዕክት ከስህተትና ከመርሳት የተጠበቁ ናቸው፡፡ ከአላህ በሚያስተላልፉት መልዕክት አይሳሳቱም፡፡ አላህ ወደ እርነሱ የላከውንም በማስፈፀም አይሳሳቱም፡፡
  2. እውነተኝነት፡ መልዕክተኞች በንግግራቸውም በተግባራቸውም እውነተኞች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ይህ አዛኙ ጌታ የቀጠረን፣ መልዕክተኛቹም እውነትን የነገሩን ነው፡፡» (ያሲን 52)
  3. ትዕግስት፡ መል°ክተኞች ወደ አላህ ሃይማኖት አብሳሪና አስጠንቃቂ በመሆን በርግጥ ተጣርተዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ ስቃዮችና መከራዎች ደርሰውባቸዋል፡፡ ሁሉንም የሚደርስባቸውን መከራና ስቃይ የአላህን ቃል የበላይ በማድረግ ጉዞ ላይ በትዕግስት ተሸክመው አልፈዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከመልዕክተኞችም የቆራጥነት ባለቤት የነበሩት እንደታገሱ ሁሉ ታገስ፡፡» (አል አሕቃፍ 35)

የመልዕክተኞች ምልክቶችና ታዓምራታቸው

አላህ (ሱ.ወ) መልዕክተኞቹን በማስረጃና ተያያዥነት ባላቸው የተለያዩ ነገሮች እውነተኝነታቸውንና ነብይነታቸውን በማረጋገጥ ረድቷቸዋል፡፡ ከዚህም መካከል በሰው ልጅ ችሎታ የማይከሰቱ በሆኑ ታዓምራትና ግልጽ በሆኑ ምልክቶች ያደረገላቸው እገዛ ወይም ድጋፍ አንዱ ነው፡፡ ይህም የሆነው እውነተኝነታቸውን ለማጽደቅና ነብይነታቸውን ለማጽናት ነው፡፡

ታዓምራት የሚባለው ተለምዶን ጥሰው የሚከሰቱ ነገሮችን ነው፡፡ ይኸውም አላህ (ሱ.ወ) በነብያቱና በመል°ክተኞቹ አማካይነት ይፋ የሚያደርገው ሲሆን ሰዎች መሰሉን ሊያመጡ ወይም ሊያስከስቱ የማይችሉት እንደሆነ በመፎካከር መልክ የሚከሰት ነው፡፡

ከነብያት ተዓምራት መካከል፡

  • የነብዩላህ ሙሳ(ዐ.ሰ) በትር ወደ እባብነት መቀየር፡
  • ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ሕዝቦቻቸው በቤቶቻቸው ውስጥ ስለሚመገቡትና ስለሚያከማቹት ምግብ መናገራቸው፡
  • ለነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጨረቃ መሰንጠቅ:

በዒሳ(ዐ.ሰ) ዙሪያ ያለው የሙስሊም እምነት

  1. እርሱ ዒሳ(ዐ.ሰ) ከታላላቅ መልዕክተኞች አንዱና ስብዕናው እጅግ የላቀ ነው፡፡ እነኚህ ከመልዕክተኞች መካከል ስብዕናቸው እጅግ የላቀ ነቢያት የቆራጥነት ባለተቤት በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነርሱም ሙሐመድ’ ኢብራሒም’ ኑሕ’ ሙሳና ዒሳ ናቸው (አለይሂሙ ሰላም)፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በሚከተለው ቃሉ ዘክሯቸዋል፡- «ከነብዮችም የጠበቀ ቃልኪዳናቸውን በያዝን ጊዜ (አስታውስ)፤ ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሂምም፣ ከሙሳም፣ ከመርየም ልጅ ዒሳም(በያዝን ጊዜ አስታውስ)» (አል አሕዛብ 7) ይላል፡፡
  2. ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) የኣደም ዝርያ ሰው ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ወደ ነገደ ኢስራኢል የላከው ሲሆን የተለያዩ ተዓምራት በርሱ እጅ እንዲፈፀሙ አድርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ደረጃ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለኢስራኢልም ልጆች ታምር ያደረግነው የሆነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ » (አል ዙኽሩፍ 59) ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ሕዝቦቹን፣ እሱንም ሆነ እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው እንዲይዟቸው ፈፅሞ አላዘዘም፡፡ ለነርሱ ያላቸው አላህ ያዘዘውን ብቻ ነበር፡፡ «ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ» (አል ማኢዳ 117)
  3. እሱ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡ እናቱ መርየም፣ ፃድቅ፣ እውነተኛ፣ ለጌታዋ ፍፁም ታዛዥና ተገዢ፣ ጥብቅ፣ ጨዋና ድንግል ሴት ነች፡፡ ዒሳን(ዐ.ሰ) የፀነሰችው ያለአባት በአላህ (ሱ.ወ) ችሎታ ነው፡፡ የእርሱ አፈጣጠር ዘልዓለማዊ ተዓምር ነው፡፡ ልክ ኣደምን ያለአባት እና ያለእናት እንደፈጠረው ሁሉ እርሱንም ያለ አባት ፈጠረው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ ኣደም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ሁን አለው ሆነም፡፡» (አል ዒምራን 59)
  4. በርሱ በዒሳ(ዐ.ሰ) እና በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መሐከል የተላከ መልዕክተኛ የለም፡፡ ስለ ነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትንቢት ተናግሮ አብስሯል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የመርየም ልጅ ዒሳም፡ የኢስራኢል ልጆች ሆይ! እኔ ከበፊቴ ያለውን ተውራትን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደ እናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ (አስታውስ) በግልጽ ታዕምራት በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልጽ ድግምት ነው አሉ፡፡» (አሥ ሠፍ 6)
  5. አላህ (ሱ.ወ) በእርሱ እጅ እንዲፈፀሙ ባደረጋቸው ታዓምራት እናምናለን፡፡ ለምፃምን ማዳኑን፣ አይነ ስዉራን ማብራቱን፣ ሙታንን ማስነሳቱን፣ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ስለሚበሉትና ስለሚያከማቹት መናገሩን እናምናለን፡፡ ሁሉም በአላህ ፍቃድ የተፈፀሙ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ለነብይነቱና ለመልዕክተኝነቱ ትክክል ለመሆኑ ግልጽ የሆነ ማስረጃ አድርጎታል፡፡
  6. ዒሳ(ዐ.ሰ) የአላህ ባሪያና መልክተኛ ነው ብሎ እስከሚያምን ድረስ የአንድም ሰው ኢማን የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ አይሁዶች እርሱን ከገለጹበት የቅጥፈትና ፀያፍ ነገሮች ሁሉ የጸዳና የጠራ እንደሆነም እናምናለን፡፡ በዒሳ እውነተኛ ማንነት ዙሪያ የተሳሳቱትን የክርስቲያኖች አመለካከትም እናወግዛለን፡፡ ይኸውም እሱና እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት ማድረጋቸው ነው፡፡ ከፊላቸው እርሱ የአላህ ልጅ ነው ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ ከስላሴዎች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ አላህ እነርሱ ከሚሉት ሁሉ የላቀ ነው፡፡
  7. አላህ (ሱ.ወ) አይሁዶች ዒሳን(ዐ.ሰ) ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ ወደ ሰማይ ከፍ አደረገውና አሳረገው እንጂ እሱ አልተገደለም አልተሰቀለምም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የእርሱ ምስል በሌላ ሰው ላይ እንዲሆን አደረገ እናም ያንን ሰው ዒሳ መስሏቸው ገደሉት ሰቀሉትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸውም (ረገምናቸው) አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡ ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም በትንሳኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡ » (አል ኒሳእ 157-159) አላህ (ሱ.ወ) እርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ እንዲያርግ በማድረግ ጥበቃ አድርጎለታል፡፡ በመጨረሻው ዘመን ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ሕግና ስርዓት ይዳኛል፡፡ ከዚያም በዚ‹ ምድር ይሞታል፤ በሷም ውስጥ ይቀበራል፡፡ ሌሎች ሰዎች እንደሚቀሰቀሱት የትንሳኤ ቀን ይቀሰቀሳል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከርሷ (ከምድር) ፈጠርናችሁ በርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን ከርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን፡፡» (ጧሃ 55)

 

በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነትና መልዕክተኝነት ማመን

  • ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን እናምናለን፡፡ እርሳቸው የመጀመሪያዎችም የኋለኞችም አለቃና የነብያት መቋጫ ናቸው፡፡ ከርሳቸው ብኋላ የሚነሳ ነብይ የለም፡፡ መልዕክታቸውን አድርሰዋል፡፡ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሕዝባቸውን መክረዋል፡፡ በአላህ መንገድ መታገል የሚገባቸውን ያክል ታግለዋል፡፡
  • እርሳቸው የተናገሩትን በሙሉ እንቀበላለን፡፡ ያዘዙትን እንተገብራለን፡፡ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር እንርቃለን፡፡ እርሳቸው በዘረጉልን መስመር መሰረት አላህን እንገዛለን፡፡ ከርሳቸው ባሻገር ማንንም በአርዓያነት አንከተልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አላችሁ፡፡» (አል አሕዛብ 21)
  • ለወላጅ፣ ለልጅ፣ በአጠቃላይ ለሰዎች ካለን ውዴታ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ውዴታ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «አንዳችሁም እኔ እርሱ ዘንድ ከወላጆቹ፣ ከልጆቹና ከሰዎች በሙሉ የበለጠ ተወዳጅ እስካልሆንኩ ድረስ አያምንም፡፡» (አል ቡኻሪ 15/ ሙስሊም 44) እርሳቸውን በትክክል መውደድ ማለት ፈለጋቸውን መከተል፣ መመሪያቸውን መንገድ ማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛ ደስታም ሆነ ሙሉዕ መመራት ሊረጋገጥ የሚችለው እርሳቸውን በመታዘዝ ብቻ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ብትታዘዙትም ትመራላችሁ፤ በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም፡፡» (አል ኑር 54)
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተላለፉትን በሙሉ መቀበል አለብን፡፡ ለፈለጋቸውም ታዛዦች መሆን ይኖርብናል፡፡ የእርሳቸውን መመሪያ ትልቅ ስፍራና ክብር ልንቸረው ያስፈልጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍፁም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፡፡» (አል ኒሳእ 65)
  • የእርሳቸውን ትዕዛዝ ከመጻረርና ከመቃረን ልንጠቀቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የርሳቸውን ትዕዛዝ መቃረን ለፈተና፣ ለጥመትና ለአሳማሚ ቅጣት ይዳርጋል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ» (አል ኑር 63)

የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ልዩ ይዘት

የነብዩ ሙሐመድ መልክት ከቀደምት መልዕክቶች ለየት የሚያደርጉት በርካታ ይዘቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት የቀደምት መልዕክቶችን መልዕክት የሚቋጭ መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፡፡ ግን የአላህ መልዕክተኛና የነብዮች መደምደሚያ ነው፡፡» (አል አሕዛብ 40)
  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ቀደምት መልዕክቶችን የተካ መሆኑ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከተላኩ ብኋላ አላህ (ሱ.ወ) እርሳቸውን ከመከተል ውጭ ምንም ዓይነት ሃይማኖትን አይቀበልም፡፡ በርሳቸው ጎዳና እንጂ አንድም ሰው ወደ ጀነት ጸጋ መድረስ አይችልም፡፡ እርሳቸው ከመልዕክተኞች ሁሉ የተከበሩ ናቸው፡፡ ሕዝባቸውም ከሕዝቦች ሁሉ ምርጥና በላጭ ሕዝብ ነው፡፡ ሕግጋታቸውም ከሕግጋት ሁሉ የተሻለና የተሟላ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡» (አል ዒምራን 85)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፡ ከዚህ ሕዝብ ውስጥ የሁድም ሆነ ክርስቲያን አንድም ሰው ስለኔ ሰምቶ በተላኩበት የማያምን አይኖርም ከእሳት ጓዶች ቢሆን እንጂ» (ሙስሊም 153 / አህመድ 8609)

  • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልክት ሁለቱንም ፍጡሮች ማለትም አጋንንትንም ሰውንም የሚመለከት መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጅኖች ያሉትን ሲያወሳ እንዲህ ብሏል፡- «ወገኖቻችን ሆይ የአላህን ጠሪ ተቀበሉ፡፡»

((አል አሕቃፍ 31) « አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢኾን እንጂ አልላክንህም ፡፡» (ሰበእ 28) ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በስድስት ነገሮች ከነብያት ተልቄያለሁ፡ ጥቅላዊ የንግገር ስልትን ተሰጥቻለሁ፤ ጠላትን በማስፈራት ታግዣለሁ፣ ምርኮ ተፈቅዶልኛል፣ ምድር ንፁሕና የጸሎት ስፍራ ተደርጋልኛለች፣ ወደ ፍጡራን በመሉ ተልኬያለሁ፣ ነብያት በእኔ ተደምድመዋል፡፡» (አል ቡኻሪ 2815 / ሙስሊም 523)

በመልዕክተኞች የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ

በመልዕክተኞች ማመን ከባድ ጥቅም አለው ከነዚህም መካከል

  1. አላህ(ሱ.ወ0 ለባሮቹ ያለውን ርህራሄና እንክብካቤ ማወቅ፡ ይኸውም መልዕክተኞቹን ወደ ነርሱ በመላክ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና እንዲመሯቸውና በምን መልኩ አላህን ማምለክ እንዳለባቸው እንዲያብራሩላቸው በማድረጉ ነው፡፡ የሰው ልጅ አዕምሮ ይህን የማወቅ ችሎታ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ስለ ነብያችን ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- «(ሙሐመድ ሆይ) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡» (አል አንቢያእ 117)

  2. በዚህ ታላቅ ጸጋው ላይ አላህን ማመስገን

  3. መልዕክተኞችን መውደድ፣ ማላቅና ለነሱ በሚገባ መልኩ እነሱን ማድነቅና ማሞገስ፡፡ ምክንያቱም እነሱ አላህን በመገዛት፣ መልዕክቱን በማድረስና ለባሮቹ መልካምን በማስተማር ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋልና ነው፡፡

  4. መልዕክተኞች ከአላህ ዘንድ የተላኩበትንና ይዘው የመጡትን መልዕክት መከተል፡ እሱም አላህን በብቸኝነት ማምለክና ለርሱ ተጋሪ አለማድረግ ነው፡፡ እርሱንም በተግባር መተርጎም ነው፡፡ በዚህም ምእመናን በሁለቱም ዓለም መመራትን ስኬትንና መልካሙን ሁሉ ያገኛሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገረምም፡፡ ከግሳጼዬም የዞረ ሰው ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፡፡» (ጧሃ 123-124)