በመጨረሻው ቀን ማመን

በመጨረሻው ቀን የማመን ትርጓሜ

አላህ (ሱ.ወ) ሰዎችን ከቀብር ይቀሰቅሳል ከዚያም በስራዎቻቸው ይተሳሰባቸዋል በዚያም ይመነዳቸዋል፤ በዚህም የጀነት ነዋሪዎች በማረፊያቸው ይረጋሉ፤ የእሳት ነዋሪዎችም በማረፊያቸው ይረጋሉ፤

ብሎ በቁርጠኝነት ማመን ነው፡፡ በመጨረሻው ቀን ማመን ከኢማን ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው፡፡ በርሱ ሳያምኑ ኢማን ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ግን መልካም ስራ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ሰው ነው»» (አል በቀራ 177)

ቁርኣን በመጨረሻው ቀን በማመን ላይ ትኩረት ያደረገው ለምንድን ነው?

ቁርኣን በመጨረሻው ቀን በማመን ላይ ለየት ያለ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በየአጋጣሚው ሁሉ ስለሱ አሳስቧል፡፡ በተለያየ የዐረበኛ አገላለጾች የርሱን ተከሳችነት አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመጨረሻው ቀን ማመንን በአላህ ከማመን ጋር አስተሳስሮታል፡፡

ምክንያቱም በአላህና በፍትሃዊነቱ ማመን በመጨረሻው ቀን ማመንን ያስገድዳል፡፡ የዚህ ማብራሪያም እንደሚከተለው ይሆናል፡-

አላህ (ሱ.ወ) በደልን አይቀበልም፡፡ በዳይን ሳይቀጣ፣ ተበዳይንም ሳይክስ አይተውም፡፡ መልካም ሰሪን ሳይመነዳና ሳይከፍለው አይቀርም፡፡ ሁሉንም ባለ መብት የሚገባውን መብት ይሰጠዋል፡፡ በዚች ዓለም ላይ በዳይ ሆኖ የሚኖር፣ በዳይ ሆኖ የሚሞት፣ ነገር ግን ምንም የማይቀጣ ሰው እንመለከታለን፡፡ በተቃራኒው ተበዳይ ሆኖ የሚኖር ተበዳይ ሆኖ የሚሞት ግን አንድም መብቱ የማይመለስለት ሰው እናያለን፡፡ ታዲያ አላህ በደልን አይቀበልም የሚለው ትርጓሜ ምንድነው? ትርጓሜው ከዚህ ሕይወት ሌላ እኛ ዳግም የምንኖርበት ሌላ ሕይወት አለ ማለት ነው፡፡ የግድ ሌላ የምላሽ ሕይወት ይኖራል፡፡ መልካም ሰሪ የሚመነዳበት፣ መጥፎ የሰራም የሚቀጣበት፣ ሁሉም ባለ መብት የሚገባውን መብት የሚያገኝበት ዓለም ይኖራል፡፡

ኢስላም ግማሽ የቴምር ፍሬን በመለገስ እንኳን ቢሆን ለሌሎች መልካም በመዋል ከእሳት እንድንርቅ ያዘናል፡፡

በመጨረሻው ቀን ማመን ምንን ያካትታል?

አንድ ሙስሊም በመጨረሻው ቀን ማመኑ በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ ያካትታል፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል፡-

  1. በመቀስቀስና በመሰብሰብ ማመን፡- ሙታን ከመቃብራቸው ወጥተው ሕያው እንዲሆኑ ይደረጋሉ ፡፡ ሩሐቸውም ወደየገላዎቻቸው ይመለሳሉ፡፡ ሰዎች የዓለማት ጌታ ፊት ይቆማሉ፡፡ ከዚያም ጫማ ሳይጫሙ እርቃናቸውን ልክ መጀመሪያ ሲፈጠሩ እንደነበሩት ሆነው በአንድ ስፍራ ይሰበሰባሉ፡፡

በመቀስቀስ ማመን በቁርኣንና በሐዲስ የተነገረ ጉዳይ ነው፡፡ ጤናማ አዕምሮና የተፈጥሮ ባህሪም ያጸደቁት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጠኝነት አላህ (ሱ.ወ) በቀብሮች ውስጥ ያለን እንደሚቀሰቅስ፣ ነፍሶች ወደየገላዎቻቸው እንደሚመለሱ፣ ሰዎች በጠቅላላ የዓለማት ጌታ ፊት እንደሚቆሙ እናምናለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከዚያም እናንተ ከዚህ በኋላ በእርግጥ ሟቾች ናችሁ፡፡ ከዚያም እናንተ በትንሳኤ ቀን ትቀሰቀሳላችሁ፡፡» (አልሙዕሚኑን 15-16)

መለኮታዊ መጽሐፍት በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ የአላህ (ሱ.ወ) ጥበበኝነት በውስጡ ያዘለውም ይህንኑ ነው፡፡ ይኸውም አላህ (ሱ.ወ) በተጣለባቸው በእያንዳንዱ ሃላፊነት ፍጡራን የሚመነዱበት የሆነ መመለሻ ዓለም እንዳዘጋጀ በመልክተኞቹ ልሳን መናገሩ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የፈጠርናችሁ ለከንቱ መኾኑን፣ እናንተም ወደኛ የማትመለሱ መኾናችሁን አሰባችሁን? (ለከንቱ የፈጠርናችሁ መሰላችሁን?)» (አል ሙዕሚኑን 115)

መቀስቀስን የሚያረጋግጡ የቁርኣን ማስረጃዎች

  • የሰው ልጅን ያለ አንዳች ቀዳሚ ምሳሌ የፈጠረው አላህ ነው፡፡ ያለ አንዳች ቀዳሚ ምሳሌ የፈጠረ ደግሞ መልሶ ማስገኘት፣ ወደነበረበት መመለስ አይሳነውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱም ያ መፍጠርን የሚጀምር ከዚያም የሚመልሰው ነው፡፡» (አል ሩም 27) አላህ (ሱ.ወ) አጥንቶች ከበሰበሱ በኋላ እንደነበሩ መመለሳቸውን ለሚያስተባብል ሰው ምላሽ እንዲሰጥበት ሲያዝ እንዲህ ብሏል፡- « ያ በመጀመሪያ ጊዜ ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል፤ እርሱም በፍጡሩ ሁሉ(ኹኔታ) ዐዋቂ ነው በለው፡፡» (ያሲን 79)
  • ምድር ምንም ዓይነት ዛፍም ሆነ አረንጓዴ ተክል የማይታይባት ኾና ከደረቀችና ከሞተች በኋላ፣ አላህ (ሱ.ወ) ዝናብ ያወርድባታል፡፡ እንደ አዲስ በአረንጓዴ ትሸፈናለች፡፡ ከእያይነቱ ቡቃያን ታበቅላላች፡፡ እናም ምድርን በዚህ መልኩ ሕያው ማድረግ የቻለ ጌታ ሙታንንም ሕያው ማድረግ ይችላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን፤ በርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን፡፡ ዘምባባንም ረዣዥም ለርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትሆን (አበቀልን) ለባሮቹ ሲሳይ ትኾን ዘንድ (አዘጋጀናት) በርሱም የሞተችን አገር ሕያው አደረግንበት (ከመቃብር) መውጣትም እንደዚሁ ነው፡፡» (ቃፍ 9-11)
  • ማንኛውም ማገናዘብ የሚችል ሰው የሚረዳው ነገር ቢኖር አንድ ትልቅና ከባድን ነገር መከወን የቻለ ከሱ በታች የሆነን ነገር በሚገባ መከወን እንደሚችል ጥርጥር የሌለው መሆኑን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እጅግ በጣም ግዙፍ፣ ሰፋፊ፣ ውስብስብና ድንቅ ፍጥረቶች ከመሆናቸው ጋር ሰማያትን፣ ምድርንና ከዋክብትን ያለ አንዳች ቀዳሚ ናሙና ፈጥሯቸዋል፡፡ በመሆኑም የበሰበሱ አጥንቶችን ሕያው በማድረግ ቻይ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ እርሱም በብዙ ፈጣሪና ዐዋቂው ነው፡፡» (ያሲን 81)
  1. በምርመራና በሚዛን ማመን፡ አላህ (ሱ.ወ) ፍጡራኑን በዱንያ ሕይወት ሲሰሩት በነበረው ስራቸው ይመረምራቸዋል፤ ይተሳሰባቸዋል፡፡ የአሃዳዊነት፣ የተውሂድ አራማጆች የሆኑ፣ አላህንና መልክተኛውን የሚታዘዙ፣ ምርመራቸው እጅግ በጣም ገር ነው፡፡ ከአጋሪያን የሆነ አመጸኛ ደግሞ ምርመራው እጅግ በጣም ብርቱ ነው፡፡

ስራዎች ትልቅና ከባድ በሆነ ሚዛን ይመዘናሉ፡፡ መልካም ስራዎች በአንድ ጎን፣ ክፉ ስራዎች ደግሞ በሌላኛው ጎን ይደረጋሉ፡፡ የመልካም ስራው ክብደት ከመጥፎው ስራው የበለጠና ሚዛን የደፋለት ከጀነት ሰዎች ይሆናል፡፡ የመጥፎ ስራው ክብደት ከመልካም ስራው የበለጠና ሚዛን የደፋበት ደግሞ ከእሳት ሰዎች ይሆናል፡፡ ጌታህ ማንንም አይበድልም፡፡

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በትንሳኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም፡፡ (ስራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ፡፡» (አል አንቢያእ 47)

  1. ጀነትና እሳት፡ ጀነት የዘልዓለማዊ ጸጋዎች ዓለም ናት፡፡ ጀነት አላህ (ሱ.ወ) እርሱን ለሚፈሩ፣ እሱና መልክተኛውን ለሚታዘዙ ምዕመናን ያዘጋጃት ናት፡፡ በውስጧ ነፍሶች የሚፈልጉት ዘውታሪ የሆኑ የጸጋ ዓይነቶች በሙሉ አሉ፡፡ በሷ ውስጥ የሚወደዱ ነገሮች ሁሉ የዓይን መርጊያዎች ሲሆኑ ይገኛሉ፡፡

አላህ (ሱ.ወ) የጎን ስፋቷ ብቻ የሰማያትና የምድርን ያክል የሆነችውን ጀነት ለመግባት በታዛዥነት ላይ ባሮቹ እንዲሸቀዳደሙ ሲያነሳሳና ሲያበረታታ እንዲህ ብሏል፡- «ከጌታችሁ ወደ ኾነችም ምሕረትና ስፋትዋ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ኾነች ገነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትኾን ተቻኮሉ፡፡» (አለ ዒምራን 133)

እሳት ደግሞ ዘልዓለማዊ መቀጫ ዓለም ናት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለካሃዲያን፤ ለነዚያ በአላህ ለካዱና መልክተኞች ላይ ላመጹት መቀጫ ትሆን ዘንድ ያዘጋጃት ናት፡፡ በውስጧ በአዕምሮ ውልብ ብሎ የማያውቅ፣ እጅግ በጣም አሳማሚ ቅጣት፣ ስቃይ፣ ሰቆቃና መከራ አለ፡፡

አላህ (ሱ.ወ) ባሮቹን ከዚች ለከሃዲያን መቀጫ ካዘጋጃት እሳት በማስጠንቀቅ መልክ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ደንጊያዎች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፡ ለከሃዲዎች ተደግሳለች፡፡ » (አል በቀራ 24)

አምላካችን ሆይ ጀነትንና ከንግግርም ከስራም ወደርሷ የሚያቃርበውን እንድትለግሰን እንጠይቅሃለን፡፡ ከእሳትና ወደርሷ ከሚያቃርብ ንግግርና ስራም ባንተ እንጠበቃለን፡፡

  1. የቀብር ስቃይና ድሎቱ፡ ሞት እውነት መሆኑን እናምናለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በናንተ የተወከለው መልአከ ሞት ይገድላችኋል ከዚያም ወደ ጌታችሁ ትመለሳላችሁ፡፡» (አል ሰጅዳ 11) ይህ በተጨባጭ የሚመለከቱት፣ ጥርጥር የሌለው እውነታ ነው፡፡ የሞተ ወይም የተገደለ ብቻ በማንኛውም ሁኔታ ሕይወቱ ያለፈ ሰው፣ ይህ ቀነ ገደቡ እንደሆነና የሞተበት ሁኔታ ከዕድሜው ላይ ምንም እንደማያጎድል እናምናለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለሕዝብም ሁሉ የተሰነ ጊዜ አላቸው፡፡ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት አንዲትን ሰዓት አይቆዩም (ከጊዚያቱም) አይቀድሙም፡፡» (አል አዕራፍ 34)

 

  • አንድ የሞተ ሰው ቂያማው ቆማበታለች፡፡ ወደ ወዲያኛው ዓለምም ተሸጋግሯል፡፡
  • ለከሃዲያንና ለአማጽያን በቀብር ውስጥ ቅጣት እንደተዘጋጀ፣ ለምእመናንና ለጻድቅ ባሮች ደግሞ የድሎት ጸጋዎች እንደተደገሱ የሚያረጋግጡ በርካታ ሐዲሶች ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተዘግበዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ እናምናለን፡፡ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አንፈላፈልም፡፡ ምክንያቱም ይህ የስውሩ ዓለም ክስተትና አዕምሮ ተጨባጭ ሁኔቴውንና በምን ዓይነት እንደሚከሰት ሊደርስበት ስለማይችል ነው፡፡ ልክ እንደ ጀነትና እሳት የስዉሩ ዓለም ክስተት እንጂ የይፋዊ ዓለም ክስተት አይደለም፡፡ አዕምሮ ሊቀይስ፣ ሊመረምርና ሊወስን የሚችለው በነባራዊው ዓለም ተመሳሳይ ያለውንና የርሱን ስርዓት የሚከተልን ነገር ብቻ ነው፡፡
  • የቀብር ሕይወት በስሜት ሕዋሳት የሚደረስበት አይደለም፡፡ ስውር ወይም ገይብ ሕይወት ነው፡፡ በሕዋስ የሚደረስበት ቢሆን ኖሮ በስውር ወይም ከሕዋስ በራቀ ነገር ማመንን ጥቅም አልባ ያደርገው ነበር፡፡ ኃላፊነት የተጣለበትንም ሚስጥር ፉርሽ ያደርጋል፡፡ ሰዎችም ባልተቀበሩ ነበር፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «አትቀባበሩም ማለትን ባልሰጋ ኖሮ አላህን እኔ የምሰማወን የቀብር ቅጣት እንዲያሰማችሁ እለምነው ነበር፡፡» (ሙሰሊም 2868 /አል ነሳኢ 2958) ከላይ የጠቀስነው ምክንያቶች በእንሳሳት ላይ ሰለሌሉ እነሱ ይህን እንዲሰሙ ተደርገዋል፡፡

በመጨረሻው ቀን የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ

  1. በመጨረሻው ቀን ማመን ሰዎችን በመልካም ስራ ላይ ስርዓት ይዘው እንዲዘወትሩ አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ እንዲሁም አላህን እንዲፈሩና ከሁሉ ለኔ ባህሪና ከይዩልኝ እንዲርቁ በማድረግ የጎላ ሚና አለው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መልካም ስራ በመጨረሻው ቀን ከማመን ጋር ተያይዞ የሚቀርበውም ለዚህ ነው ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የአላህን መስጂዶች የሚሰራው በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ነው፡፡» (አል ተውባ 18) «እነዚያም በመጨረሻይቱ ዓለም የሚያምኑት እነርሱ በሶላታቸው ላይ የሚጠባበቁ ሲኾኑ በርሱ ያምናሉ፡፡ » (አል አንዓም 92)

  2. በሕይወት ውጣውረድ እራሳቸውን በመወጠር አላህን በመታዘዝ ላይ ከመሽቀዳደም ለተዘናጉ፣ ወደ አላህ በመቃረብ ጊዜን ከመሻማት፣ እርሱን ከመታዘዝ፣ የዚችን ዓለም እውነተኛ ገጽታና አጭርነት ከማስተንተን፣ የወዲያኛውን ዓለም መርጊያነት ዘልዓለማዊነት ከማሰብ ለተዘናጉና ለረሱ ማሳሳቢያና ማስጠንቀቂያ አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ)በቁርኣን ውስጥ መልዕክተኞችን ስራቸውን በመጥቀስ ሲያወሳ፣ እነዚያን ስራዎችና የላቁ ገድሎች እንዲፈጽሙ ሰበብ የሆናቸውን ጉዳይ በማሞገስ ነበር ያወሳው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ ጥሩ በኾነች ጠባይ መረጥናቸው (እርሷም) የመጨረሻይቱን አገር ማስታወስ ናት፡፡» ማለትም የነኚያ የተከበሩ ስራዎቻቸው መንስኤ እነርሱ የመጨረሻይቱን አገር በማስታወስ ለየት ያሉ መሆናቸው ሲሆን ይህም ማስታወሳቸው እነዚያን ስራዎችና አቋሞች እንዲኖራቸው ገፋፍቷቸዋል፡፡ እነርሱን ለማሳሰብና ለማስጠንቀቅ እንዲህ አለ፡- «የቅርቢቱን ሕይወት ከመጨረሻይቱ ይበልጥ ወደዳችሁን? የቅርቢቱ ሕይወት በመጨረሻይቱ (አንጻር) ጥቂት እንጂ አይደለም፡፡» (አል ተውባ 38) የሰው ልጅ በመጨረሻው ቀን በትክክል በሚያምን ጊዜ ማንኛውም የዚች ዓለም ጸጋ ከመጨረሻው ዓለም ጸጋ ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል እርግጠኛ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በወዲያኛው ዓለም ለአንዲት ቅጽበት የሚያገኘውን ቅጣት ምንም ሊያክለው አይችልም፡፡ በዚህም በዱንያ ላይ ያለ የቅጣት ዓይነትም ከመጨረሻው ዓለም ቅጣት ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል ይገነዘባል፡፡ በሌላ በኩል እዚህ ያለ ተድላና ደስታ በወዲያኛው ዓለም ከሚያጋጥም የቅጽበት ጸጋ ወይም ድሎትና ደስታ ጋር አይስተካከልም፡፡

  3. የሰው ልጅ በመጨረሻው ቀን ካመነ የስራውን ምንዳ ማግኘቱ አይቀሬ እንደሆነ እርግጠኛ ስለሚሆን ይረጋጋል፡፡ ስለሆነም የሆነ የዚህች ዓለም ጥቅም ቢያመልጠው ወይም ቢያጣው ተስፋ በመቁረጥና በመበሳጨት ነፍሱን በሐዘን አይገድልም፡፡ እንዳውም ታታሪ ሊሆንና አላህ (ሱ.ወ) የመልካም ሰሪን ምንዳ በከንቱ እንደማያስቀር እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ የጎመን ዘር ቅንጣትን የሚያህል ነገር ከርሱ በግፍ ወይም ያለ አግባብ ቢወሰድበት ወይም ቢጭበረበር የትንሳኤ ቀን እሷ እጅግ በምታስፈልገው ወቅት ላይ ያገኛታል፡፡ ፈንታው ያለምንም ጥርጥር በጣም በሚያስፈልገው ወቅት ላይ እንደሚሰጠው ያወቀ ሰው እንዴትስ ያዝናል? በእርሱና በሞጋቹ መሐከል የሚዳኝውና የሚፈርደው የፍትሃውያን ሁሉ ፍትሃዊ የሆነው ጥበበኛው ዳኛ አላህ(ሰ.ወ) እንደሆነ ያወቀ እንዴትስ ይተክዛል?