ቤተሰብ በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ
የሚከተሉት ጉዳዮች ኢስላም ለቤተሰብ ልዩ እንክብካቤና እገዛ ማድረጉን በግልጽ ያሳያሉ፡-
- ኢስላም በጋብቻ ጅማሬና በቤተሰብ ምስረታ ላይ ልዩ እይታ አለው፡፡ በመሆኑም ከስራዎች ሁሉ የላቀ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር፣ የመልክተኞች ፈለግ እንዲሆንም አድርጎታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ነገር ግን እኔ እጾማለሁ እፈታለሁም፤ እሰግዳለሁ አሸልባለሁም፤ ሴትም አገባለሁ፡፡ ከኔ ፈለግ የወጣ ከኔ አይደለም፡፡›› (አል ቡኻሪ 4776 /ሙስሊም 1401)
- ቁርኣን ከታላላቅ ተዓምራትና ጸጋዎች ጎራ ከቆጠራቸው ነገሮች አንዱ አላህ (ሱ.ወ) በባልና ሚስት መሐከል ፍቅርን እዝነትንና እርካታን ማድረጉን ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለናንተም ከነፍሶቻችሁ ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፣ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለሚያስተውሉ ሕዝቦች ታምራቶች አልሉ፡፡›› (አል ሩም 21)
- ጋብቻን ገር ማድረግ፣ ለማግባት የሚፈልግም ሰው ነፍሱን ከዝሙት እንዲጠብቅ መረዳትና መታገዝ እንዳለበት ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ ሦስት ዓይነት ሰዎችን ለመርዳትና ለማገዝ በራሱ ላይ ግዴታ አድርጓል፡፡›› አሉና ከነሱ መካከል፣ ‹‹ጥብቅነትን ፈልጎ ጋብቻን የፈፀመን ሰው›› ጠቅሰዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 1655)
- ወጣቶችን ገና በአፍላ ዕድሚያቸውና ባልተነካ ጉልበታቸው ላይ ሳሉ ጋብቻን እንዲፈፅሙ አዟል፡፡ ምክንያቱም ጋብቻ ለነሱ መርጊያቸውና መርኪያቸው ስለሆነ ነው፡፡ ለፍቶት ስሜታቸውና ፍላጎታቸው ትክክለኛ መፍትሄም ነው፡፡
- ኢስላም ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ወንድም ሆነ ሴት ልዩ ክብር ሰጥቷል፡፡
ኢስላም ልጆችን የመንከባከብና በማሳዳግ ጉዳይ በእናትና በአባት ላይ ከባድ ኃላፊነት ጥሏል፡፡ ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ ማለታቸው ተላልፏል፡- ‹‹ሁላችሁም እረኞች ናችሁ፤ ማናችሁም ከሚጠብቀው ይጠየቃል፡፡ አንድ መሪ እረኛ ነው፤ በጥበቃው ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ አባወራ በቤተሰቡ ላይ እረኛ ነው፤ በርሱ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ ሴትም በባሏ ቤት ውስጥ እረኛ ነች፤ በርሷ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነች፡፡ ባሪያ በአሳዳሪው ንብረት ላይ እረኛ ነው፡፡ በርሱ ስር ስላሉት ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 853 /ሙስሊም 1829)
- ኢስላም ለአባቶችና ለእናቶች ክብር በመስጠትና ደረጃቸውን በመጠበቅ፣ እንዲሁም እስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ድረስ እነርሱን መንከባከብና ትዕዛዛቸውን መፈፀምን አስመልክቶ ልዩ ትኩረት ቸሯል፡፡
ወንድ ወይም ሴት ልጅ፣ ምንም ያህል ትልቅ ሰው ቢሆኑም ለወላጆቻቸው ታዛዥ የመሆንና ለነሱ በጎ የመዋል ግዴታ አለባቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ጉዳይ ከርሱ አምልኮ ጋር አቆራኝቶ ጠቅሶታል፡፡ እነርሱ ላይ በንግግርና በተግባር ድንበር ማለፍን ከልክሏል፡፡ በነሱ መናደዱን የሚመለክትን ቃል ወይም ድምፅ ማሰማትንም ሳይቀር ከልክሏል፡፡ ‹‹ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ፤ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡›› (አል ኢስራእ 23)
- ኢስላም የወንድም ሆነ የሴት ልጆችን መብት እንድንጠብቅ አዟል፡፡ በመካከላቸው በወጪም ሆነ በይፋ በሚታዩ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊ መሆንም ግዴታ ነው፡፡
- ኢስላም በአንድ ሙስሊም ላይ ዝምድናን የመቀጠል ግዴታ ጥሎበታል፡፡ ይህ ማለት በእናቱም ሆነ በአባቱ በኩል ያሉትን ዘመዶቹን ዝምድና በመቀጠልና ለነርሱ በጎ በመዋል ይገለፃል፡፡
ወንድሞቹ፣ እህቶቹ፣ አጎቶቹ፣ አክስቶቹና ልጆቻቸው እዚህ ውስጥ የሚገቡ ሲሆን ለነርሱ መልካም መስራት፣ ከታላላቅ ወደ አላህ መቃረቢያዎችና ታዛዥነትን መግለጫ መንገዶች መካከል ቆጥሮታል፡፡ ዝምድናቸውን ከመቁረጥ፣ ወይም ክፉ ነገር በነርሱ ላይ ከመፈፀም እንድንርቅ አስጠንቅቋል፡፡ ይህን ማድረግን ከከባባድ ወንጀሎች ፈርጆታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ዝምድናን ቆራጭ ጀነት አይገባም፡፡›› (አል ቡኻሪ 5638 /ሙስሊም 2556)
ሴት በኢስላም ውስጥ ያላት ስፍራ
ኢስላም ሴት ልጅን እጅግ በጣም አክብሯታል፡፡ ለወንዶች ባሪያ ከመሆንም ነፃ አውጥቷል፡፡ ክብርና ደረጃ የሌላት ውዳቂና ርካሽ ከመሆንም አድኗታል፡፡ ከሴት ልጅ ክብር ጋር ተያያዥነት ካላቸው ኢስላማዊ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
- ኢስላም ለሴት ልጅ ፍትሃዊ በሆነ ክፍፍሎሽ የውርስ ድርሻዋን ሰጥቷል፡፡ በአንዳንድ ስፍራ ከወንድ ጋር እኩል ታገኛለች፡፡ በአንዳንድ ስፍራ ደግሞ ድርሻዋ ከወንዱ ይለያል፡፡ ይኸውም ለሟች ባላት ቅርበት፣ እንዲሁም ካለባት ኃላፊነትና ወጪ አንጻር የሚወሰን ነው፡፡
- በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ወንድና ሴትን እኩል አድርጓቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ማንኛውም ገንዘብ ነክ እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሴቶች የወንዶች ክፋይ ናቸው፡፡›› (አቡ ዳውድ 236)
- ኢስላም ለሴት ልጅ ባሏን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል፡፡ ልጆችን የማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት ደግሞ ጥሎባታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሴት ልጅ በባሏ ቤት ውስጥ ጠባቂ ነች፤ ከምትጠብቀው ነገር ተጠያቂ ነች፡፡›› (አል ቡኻሪ 853 / ሙስሊም 1829)
- ስሟና በአባት የመጠራት ክብሯ እንዲቆይ አድርጎላታል፡፡ ከጋብቻ በኋላም በአባት መጠራቷ ይቀጥላል፡፡ ምን ጊዜም በአባቷና በቤተሰቦቿ መጠራቷም ይዘልቃል፡፡
- ወጪያቸውን መሸፈን ከሚኖርበት ሴቶች መካከል ከሆነች ማለትም ሚስቱ እናቱ ወይም ሴት ልጁ ከሆነች፣ ኢስላም በወንዱ ላይ እሷን የመጠበቅና ወጪዋን የመሸፈን ግዴታ ጥሎበታል፡፡
- የቅርብ ዘመድ ባትሆንም፣ ረዳት የሌላትን ደካማ ሴት መርዳትና ማገዝ ልዩ ክብርና ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ እሷን ለመርዳትና ለማገዝ መሯሯጥ አላህ ዘንድ ትልቅ ክብር ያለው ተግባር መሆኑን በመግለጽ አነሳስቷል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና የችግረኞችን ጉዳይ ለመፈፀም የሚሯሯጥ ሰው፣ ልክ በአላህ መንገድ ላይ ትግል እንደሚያደርግ፣ ሌሊት ተነስቶ ሳይታክት እንደሚሰግድና፤ ጾሞ እንደማያፈጥር ሰው ነው፡፡›› (አልቡኻሪ 5661 / ሙስሊም 2982)
ኢስላም ልዩ ትኩረት እንዲቸራቸው ያደረጋቸው ሴቶች
እናት፡ አቡ ሁረይራ(ረ.ዐ) የሚከተለውን ሐዲስ አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ሰው ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና፣ አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ ከሰዎች ሁሉ በበለጠ ጓደኝነቱን ወይም ግንኙነቱን ልጠብቅለት የሚገባ ማን ነው? አላቸው፡፡ እሳቸውም፡ ‹‹እናትህ›› አሉት፤ ከዚያስ? አላቸው፤ ‹‹ከዚያም እናትህ›› አሉት፤ ከዚያስ? አላቸው፤ ‹‹አሁንም እናትህ›› አሉት፡፡ ለአራተኛ ጊዜ፡ ከዚያስ? አላቸው፣ ‹‹ከዚያማ አባትህ ነው፡፡›› አሉት፡፡ (አል ቡኻሪ 5626 / ሙስሊም 2548)
ሴት ልጅ፡ ዑቅበቱ ኢብኑ ዓሚር(ረ.ዐ) ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡ ‹‹ሦስት ሴት ልጆች ኖረውት፤ ስለነርሱ ትዕግስት አድርጎ፣ ጥሮ ግሮ ከላቡ ውጤት ያበላቸው፣ ያጠጣቸውና፣ ያለበሳቸው ሰው፣ የትንሳኤ ቀን ከእሳት ግርዶሽ ይሆኑለታል፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 3669)
ሚስት፡ እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ)፣ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፡- ‹‹በላጫችሁ ለቤተሰቦቹ መልካም የሆነው ነው፡፡ እኔ ለቤተሰቦቼ መልካማችሁ ነኝ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 3895)
በኢስላም የወንድና የሴት ግንኙነት የመደጋገፊያ ግንኙነት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ሙስሊም ማህበረሰብን በመገንባት ላይ የሚዘጉት ክፍተት ወይም ቀዳዳ አላቸው፡፡
በሁለቱ ፆታዎች መካከል ሽኩቻ የሚፈጥር ነገር የለም፡፡
በአንዳንድ ያልሰለጠኑ ማህበረሰቡች ውስጥ እንደታየው፣ በወንድና በሴት መካከል የተደረጉት ሽኩቻዎች፣ በወንዱ በሴት ላይ ፈላጭ ቆራጭ መሆን፣ አለያም ደግሞ በሴቷ ከተፈጥሯዊ ባህሪ ማፈንገጥና ከአላህ ሕግጋት ውጭ መሆን ይጠናቀቃል፡፡
ይህ ደግሞ ከአላህ ሕግጋት ፍፁም በመራቅ እንጂ ሊከሰት አይችልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህም ከፊላችሁን በከፊላችሁ ላይ በርሱ ያበለጠበትን ጸጋ አትመኙ፤ ለወንዶች ከሰሩት ስራ ዕድል አላቸው፤ ለሴቶችም ከሰሩት ስራ ዕድል አላቸው፤ አላህንም ከችሮታው ለምኑት አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡›› (አል ኒሳእ 32)
በኢስላም ሁለቱም ፆታዎች እራሱን የቻለ ልዩ ተሰጥኦ፣ ኃላፊነትና ክብር አላቸው፡፡ ሁሉም የአላህን ችሮታና ውዴታ ለማግኘት ይጥራል፡፡ ኢስላማዊው ድንጋጌ፣ ለሙስሊም ማህበረሰብ ብሎም ለሰው ዘር በሙሉ እንጂ ለወንዶች ወይም ለሴቶች ሲባል የተደነገገ አይደለም፡፡
በኢስላም እይታ መሰረት፣ በሁለቱ ፆታዎች መሐከል ያ ለሽኩቻ ቦታ የለውም፡፡ በዓለማዊ ጥቅም መፎካከር ትርጉም አልባ ነው፡፡ በሴቶች ላይ ማሴር ወይም በወንዶች ላይ ማመጽ የሚባል ነገር ጣዕም ወይም ስሜት አይኖረውም፡፡ አንዱ ሌላኛውን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ፣ ድክመቱን ችግሩንና ጉድለቱን ለማጋለጥ የሚካሄድ ሙከራ በኢስላም ቦታ የለውም፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ በኩል ስንመለከተው ጫወታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢስላምንና የሁለቱን ፆታዎች ትክክለኛ የስራ ዘርፍ አላግባብ ከመረዳት የመነጨም ነው፡፡ ሁላቸውም አላህን ከችሮታው ሊለምኑት ይገባል፡፡