የወላጆች መብት
ለወላጆች በጎ መዋል ከመልካም ስራዎች መካከል ከባዱና አላህ ዘንድ ብዙ ምንዳን ከሚያስገኙ ተግባሮች ሲሆን፣ አላህ (ሱ.ወ) እርሱን ከመገዛትና በአሃዳዊነቱ ከማመን ጋር አቆራኝቶታል፡፡
ለነርሱ በጎ መዋልና ጥሩ መሆን ጀነት ለመግባት የሚያስችል ወሳኝ ምክንያት አድርጎታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ወላጅ የጀነት የመሐለኛው በር ነው፤ ይህን በር ብትፈልግ ቸል በለው ወይንም ጠብቀው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1900)
- በወላጆች ላይ የማመፅና ለነርሱ ክፉ የመሆን አደገኝነት
መለኮታዊ መመሪያዎች በሙሉ በአደገኝነቱና በከባድ ወንጀልነቱ የተስማሙበትና ከርሱም ያስጠነቀቁት ነገር ቢኖር ለወላጆች ክፉ መሆን ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለሠሓቦቻቸው፡ ‹‹አይከብዱ የከበዱ ወንጀሎችን አልነግራችሁምን?›› አሉ፡፡ ሠሐቦችም፡ «እንዴታ ይንገሩን እንጂ አንቱ የአላህ መልክተኛ» አሉ፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡ ‹‹በአላህ ማጋራትና በወላጆች ላይ ማመፅ ናቸው፡፡›› አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 5918)
- በአላህ ላይ ከማመፅ ውጭ ባለ ጉዳይ እነርሱን መታዘዝ
አላህ(ሰ.ወ) ላይ በማመፅ ወይም የአላህን ሕግ በመጣስ እስካላዘዙ ድረስ ወላጆች በሚያዙት ነገር ሁሉ ለነርሱ ፍጹም ታዛዥ መሆን ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም በፈጣሪ ላይ እያመፁ ለፍጡራን መታዘዝ አይፈቀድም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሰውንም በወላጆቹ መልካም አድራጎትን አዘዝነው፤ ላንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን (ጣዖት) በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው፡፡›› (አል አንከቡት 8)
- ለነርሱ በጎ መዋል በተለይም ሲሸመግሉ
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ፤ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡›› (አል ኢስራእ 23) አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ ለወላጆቹ በተለይም ከሸመገሉና ከደከሙ በኋላ ታዛዥ እንዲሆንና እንዳይገላምጣቸው ወይም እንዳይቆጣቸው አዟል፡፡ ኡፍ በማለት ቢሆንም ቃል ባይተነፍስም እንኳ በእነርሱ ላይ መበሳጨትና መቆጣት የለበትም፡፡
- ከሃዲያን ወላጆች
አንድ ሙስሊም ወላጆቹ ከሃዲያን ቢሆኑም እንኳን ለነርሱ ፍፁም ታዛዥና በጎ የሚውልላቸው ሊሆን ይገባል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ለአንተ በርሱ እውቀት የሌለህን ነገር በኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፤ በቅርቢቱም ዓለም በመልካም ስራ ተወዳጃቸው›› (አል ሉቅማን 15) ለነርሱ በጎ ከመዋል ሁሉ እጅግ ታላቁና ጠቃሚው እነርሱን በጥሩ ስነምግባርና በጥበብ በተሞላ መልኩ ወደ ኢስላም መጥራት ነው፡፡
የልጆች መብት
- ጥሩ እናት ልትሆን የምትችል መልካም ሚስት ለጋብቻ መምረጡ አባት ለልጆቹ ከሚያቀርብላቸው ስጦታዎች ሁሉ በላጩ ነው፡፡
- ስም ከነርሱ የማይለይ የሆነ መገለጫቸው በመሆኑ፣ ልጆችን በሚያማምሩ ስሞች መሰየም ልጆች በወላጆች ላይ ካላቸው መብት መካከል ነው፡፡
- በመልካም ስነ ምግባር አንጾ ማሳደግ፣ መሰረታዊ የሃማኖት ጉዳዮችን ማስተማርና ሃይማኖታቸውን እንዲወዱ ማድረግ፡፡
ብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እያንዳንዳችሁ እረኞች ናችሁ፤ ከጠበቃችሁት ነገርም ተጠያቂዎች ናችሁ፤ በሰዎች ላይ የተሾመ ሹም እረኛ ነው፤ ስለነርሱ ተጠያቂ ነው፤ አባወራ በቤተሰቡ ላይ እረኛ ነው፤ ስለነርሱ ተጠያቂ ነው፤ ሴት በባሏ ቤትና በልጆቹ ላይ እረኛ ነች፤ ስለነርሱ ተጠያቂ ነች፤ ባሪያም በአሳዳሪው ንብረት ላይ እረኛ ነው፤ ስለርሱ ተጠያቂ ነው፤ አዋጅ! ሁላችሁም እረኞቸች ናችሁ፤ ሁላችሁም ስለጠበቃችሁት ነገር ተጠያቂዎች ናችሁ፡፡›› (አል ቡኻሪ 2416 / ሙስሊም 1829) ወላጆች እንደየአስፈላጊነቱና አንገብጋቢነቱ ቅደም ተከተል በማስያዝ ልጆቻቸውን ማነጽ ይኖርባቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ከማጋራትና ከፈጠራ አመለካከት የጸዱ ማድረግ፣ ትክክለኛውን የእምነት መሰረት እንዲይዙና ከዚያም አምልኮዎችን፣ በተለይም ሠላትን እንዲሰግዱ ማድረግና ብሎም ጥሩ ስነምግባርንና ስርዓቶችን ሊያስተምሯቸው ይገባል፡፡ ክብርና በጎ የሆነን ሁሉ ሊያሳዩዋቸው ይገባል፡፡ ይህ አላህ ዘንድ ትልቅ ከሚባሉ ስራዎች ነው፡፡
- ወጪ፡ ወላጅ አባት የወንድም ሆነ የሴት ልጆቹን ወጪ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ችላ ማለትም ሆነ መሳነፍ አይገባውም፡፡ እንደውም እንደችሎታውና አቅሙ በተሟላ መልኩ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት መጣር ይኖርበታል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ሰው የሚያስተዳድረውን መጣሉ ብቻ ከወንጀል በኩል ይበቃዋል፡፡›› (አቡ ዳውድ 1692) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ሴት ልጆችን በመጠበቅና ለነርሱ ወጪ ማድረግን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የነዚህን ሴት ልጆች ጉዳይ የተሸከመና ለነርሱም በጎ የዋለላቸው፣ እነርሱ ለርሱ ከእሳት ግርዶ ይሆኑለታል፡፡›› (አል ቡኻሪ 5649/ ሙስሊም 2629)
- ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሁሉም ልጆች መካከል ፍትሃዊ መሆን፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህን ፍሩ በልጆቻችሁ መካከል ፍትሃዊ ሁኑ፡፡›› (አል ቡኻሪ 2447 / ሙስሊም 1623) ሴቶችን ከወንዶቹ ማስበለጥ እንደማይፈቀድ ሁሉ ወንዶችንም ከሴቶች ማስበለጥም አይፈቀድም፡፡ ይህን ማድረግ አደገኛ ችግርን ይፈጥራል፡፡