ሰውን ማታለልና አለማወቅ

ይህ ሐረግ ማንኛውንም በውስጡ የተወሰነ የማይታወቅ ክፍተት ያለው ነገርን ያዘለ፣ በሁለቱ ውል ፈፃሚዎች (ሻጭና ገዥ) መሐከል ጭቅጭቅና ሙግት እንዲከሰት፣ አለያም አንዱ ሌላኛውን እንዲበድል ምክንያት የሚሆን ተግባርን የሚገልጽ ነገር ነው፡፡

ኢስላም፣ ሙግትን ወይም በደልና ጉዳትን አስቀድሞ ለመከላከል ሲል ማታለልንና ግልጽ አልባነትን እርም አድርጓል፡፡ ይህ ነገር ሰዎች ቢስማሙበትና ቢወዱትም ክልክል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ማታለል ያለበትን ሸያጭ ከልክለዋል፡፡ (ሙስሊም 1513)

ማታለልና ግልጽ አልባነት ያለበት ሽያጭ ምሳሌ

  1. አንድን ፍሬ ጥሩና መጥፎነቱ ሳይለይ፣ በዛፍ ላይ እያለ ለመቆረጥ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ላይ ሳለ መሸጥ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከመብሰሉ በፊት የመበላሸት አደጋ ሊደርስበት ስለሚችል ይህ ዓይነቱን ሸያጭ ከልክለዋል፡፡
  2. በውስጡ ያለው ነገር ውድ ይሁን ርካሽ፣ የሚጠቅም ይሁን አይሁን ከመረጋገጡ በፊት አንድ ሳጥንን ወይም እሽግ ዕቃን ለመግዛት የሆነ ያክል ገንዘብ አስቀድሞ መክፈል ክልክል ነው፡፡

የአንድ እቃ ምንነት አለመታወቅ በግብይቱ ውስጥ ታሳቢነት የሚያገኘው መች ነው?

ከውሉ ጋር ብዙ ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮችና በውሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በስተቀር ሽንገላና ምንነቱን አለማሳወቅ የአንድን ውል ፍፃሜ የተከለከለ ለማድረግ አይችሉም፡፡

ለምሳሌ፣ ለአንድ ሙስሊም አንድን ቤት ለመገንባትና ለማሳመር የተጠቀመውን የዕቃ ዓይነት ሳይገልጽ ቤቱን መሸጥ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ምንንቱን አለማሳወቅ ዋናው ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም የተከሰተው በውሉ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ሳይሆን ከውሉ ጋር ተያያዥነት ባለው ጉዳይ ዙሪያ በመሆኑ ነው፡፡

በደልና የሰዎችን ገንዘብ አላግባብ መውሰድ

በደል ኢስላም ካስጠነቀቃቸው እኩይ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በደል የትንሳኤ ቀን ጽልመት ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 23215 / ሙሲሊም 2579) ትንሽ ቢሆንም፣ የሰዎችን ገንዘብ ያለ አግባብ መውሰድ ክልክል ነው፡፡ ይህ አላህ(ሱ.ወ) ፈፃሚዎቹን በመጨረሻው ዓለም ላይ ጠንካራ ቅጣት እንደሚገጥማቸው ከወዲሁ በመንገር ከዛተባቸው ከከባባድ ሃጢኦቶችና ወንጀሎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ስንዝር ያክል መሬት የበደለ ሰው በትንሳኤ ቀን ከሰባቱ ምድር (በአንገቱ) ይጠለቅለታል፡፡›› (አልቡኻሪ 2321 /ሙስሊም 1610)

 

በማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ከሚከሰቱ የበደል ምሳሌዎች፡

  1. ማስገደድ፡ በየትኛውም የማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ፣ ማስገደድና በኃይል ማንበርከክ አይፈቀድም፡፡ በነፃ ምርጫና በስምምነት ካልሆነ በስተቀር በማስገደድ የሚፈፀም ማንኛውም ውል ተቀባይነት የለውም፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሽያጭ (የሚፀድቀው) በስምምነት ነው፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 2185)
  2. የሰዎችን ገንዘብ በሐሰት ለመብላት ማታለልና ማጭበርበር፡ ይህም ከከባባድ ወንጀሎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እኛን ያታለለ ከኛ አይደለም፡፡›› (ሙስሊም 101) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሐዲስ የተናገሩበት ምክንያቱ፡ በአንድ ወቅት ወደገበያ ወጣ ባሉበት፣ እህል የያዘ ከረጢት ተመለከቱ፤ ከዚያም እጃቸውን ወደታች ዘለቅ አድርገው በከረጢቱ ውስጥ ሲሰዱት ከታች እርጥበትን አገኙ፤ ወዲያውም ለሻጩ ‹‹አንተ ባለ እህል ይህ ምንድነው?›› አሉት፤ እሱም፡ ‹‹ዝናብ አግኝቶት ነው የአላህ መልክተኛ›› አላቸው፤ እሳቸውም፡- ‹‹ሰዎች እንዲያዩት ከላይ አታደርገውም ነበር? እኛን ያታለለ ከእኛ አይደለም፡፡›› አሉት፡፡ (አል ቲርሚዚ 1315)
  3. የሰዎችን ገንዘብ ያለ አግባብና በግፍ ለመውሰድ በሕግና ደንብ መቀለድ፡ አንድ ሰው የርሱ ያልሆነ ገንዘብን በሕጋዊ መንገድና በፍርድቤት አስወስኖ የመውሰድ ጮሌነትና ፍጥነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የአንድ ዳኛ ፍርድ ስህተትን እውነት ሊያደርገው አይችልም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እኔ የሰው ልጅ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ እኔ ዘንድ በመምጣት ትካሰሳላችሁ፤ ምናልባት አንዳችሁ ማስረጃ ከማቅረብ አኳያ ከሌላኛው የበለጠ ይሆንና በሰማሁት መሰረት ለርሱ ልፈርድለት እችላለሁ፡፡ እናም ከወንድሙ መብት ለርሱ የፈረድኩለት ሰው እንዳይወስድ፤ እኔ ለርሱ የቆረጥኩለት ከእሳት የሆነ ቁራጭን ነውና፡፡››
  4. ጉቦ ማለት፣አንድ ሰው የርሱ ያልሆነን ንብረት ለማግኘት ሲል ገንዘብ ወይም የሆነ አገልግሎት መስጠቱ ሲሆን፣ ይህ ተግባር ከበደል ዓይነቶች ሁሉ አደገኛው በደልና ከባዱ ወንጀል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጉቦ ሰጪውንም ተቀባዩንም ረግመዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 1337) በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ጉቦ ከተስፋፋ፣ ስርዓት የለሽነት ይሰፍናል፤ ስርዓት ይንኮታኮታል፡፡ እድገቱና ስልጣኔውም ይቆማል፡፡

በካሃዲነቱ ዘመን ያለ አግባብ ገንዘብ ይወስድ የነበር ሰው ኢስላምን ሲቀበል ፍርዱ ምንድነው?

አንድ ሰው አግባብ ባልሆኑ መንገዶች በግፍ ድንበር በማለፍ በስርቆት ወይም በመሸወድና ወዘተ ከሰዎች የወሰደው ገንዘብ እሱ ዘንድ እያለ ከሰለመ የሚያውቃቸው ከሆነና ምንም ዓይነት አደጋ ሳይከሰት ለነርሱ ማስረከብ የሚችል ከሆነ ለባለቤቶቹ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡

ይህን ገንዘብ፣ ምንም እንኳን ኢስላምን ከመቀበሉ በፊት ያገኘው ቢሆንም ይህ በግፍ ድንበር በመተላለፍ የተወሰደ ገንዘብ በእጁ ያለ ገንዘብ ነው፡፡ እናም ከቻለ ይህን ገንዘብ መመለስ ይገባዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡›› (አል ኒሳእ 58)

ባለቤቱን ለማወቅና ለማግኘት የሚችለውን ያክል ከጣረ በኋላ ማወቅ ካልቻለ ገንዘቡን በመልካም ስራዎች ላይ በማዋል መጽዳት አለበት፡፡

 ቁማር

ቁማር ማለት ምንድን ነው?

ቁማር ሁለት ተጫዎቾች ወይም ተወዳዳሪዎች ወይም ተወራራጆች አንዳቸው ካተረፈ (ካሸነፈ) ከከሰረው (ከተሸነፈው) ላይ ገንዘብ እንዲወስድ ቅድመ መስፈርት በሚቀመጥለት ውድድርና ጫወታ ላይ ይከሰታል፡፡በዚህ ላይ የሚሳተፉት ሁለቱም ወገኖች ገንዘቡን ከሌላው ወገን በሚያገኙበት ወይም ለሌላው በማስረከብ በሚከስርበት መሀል የሚሽከርከሩ ናቸው፡፡

የቁማር ሸሪዓዊ ፍርድ፡

ቁማር እርም ነው፡፡ በቁርኣንና በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሱና ውስጥ እርምነቱ በግልፅ ተነግሯል፡፡

  1. አላህ (ሱ.ወ) በቁማር ምክንያት የሚከሰት ወንጀልና ጉዳት በርሱ ከሚገኝ ጥቅም እጅግ የገዘፈ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አዕምሮን ከሚቃወም (አስካሪ) መጠጥና ከቁማር ይጠይቁሃል፤ በሁለቱም ውስጥ ጥቅሞች አሉባቸው ግን ሃጢአታቸው ከጥቅማቸው በጣም ትልቅ ነው በላቸው፡፡›› (አል በቀራ 219)
  2. አላህ (ሱ.ወ) በግለሰቦችና በማህበረሰብ ላይ ከሚያስከትሉት መጥፎ ጉዳቶች አንጻር ቁማርን ስውር ወይም ረቂቅ እርኩስ በሚል ፍርድ ሰጥቶበታል፡፡ ከርሱ በመራቅም አዟል፡፡ የልዩነትና የጥላቻ መንስኤ፣ ከሠላትና አላህ ከማውሳት የመዘናጊያ ምክንያት መሆኑንም ተናግሯል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጦኦታትም አዝላምም(የመጠንቆያ እንጨቶች) ከሰይጣን ስራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፡፡(እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና፡፡ ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ብቻ ነው ታዲያ እናንተ (ከነዚህ) ተከልካዮች ናችሁን? (ተከልከሉ)›› (አል ማኢዳ 90-91)

ቁማር በማህበረሰብና በግለሰቦች ላይ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች፡

ቁማር በማህበረሰቡና በግለሰቦች ላይ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች እጅግ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹም፡

  1. በሰዎች መካከል ጠብንና ጥላቻን ይፈጥራል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቁማር ተጫዎቹች ጓደኛሞችና ወዳጆች የነበሩ ይሆናሉ፡፡ ከዚያ በኋላ፣አንደኛቸው አሸናፊ ሆኖ ገንዘቡን በሚወስድ ጊዜ፣ ሌሎቹ እንደሚጠሉትና ቂም እንደሚይዙበት፣ በነፍሳቸው ውስጥም ለርሱ ጥላቻንና ምቀኝነትን እንደሚያበቅሉ ጥርጥር የለውም፡፡ እርሱ በነሱ ላይ ኪሳራን እንዳደረሰባቸው ሁሉ እነሱም እርሱን ለመጉዳትና ለመተናኮል የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ ይህ፣ ሁሉም የሚያውቀውና የሚያስተውለው ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ):- ‹‹ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል ነው፡፡›› ይላል፡፡ በተጨማሪም ኃላፊነትን ከመወጣት፣ ሠላትን ከመስገድ፣ እንዲሁም አላህን ከማውሳት የሚያዘናጋ ነገር ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ሰይጣን ሰዎች ቁማርን እንዲጫወቱ የሚያሰማምርበትና የሚገፋፋበትን ሁኔታ ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ብቻ ነው››
  2. ቁማር ገንዘብ የሚሟጥጥ፣ ሃብትንም የሚያከስም ነው፡፡ በቁማርተኞች ላይ በርካታና ከፍተኛ ክስረቶችን ያደርስባቸዋል፡፡
  3. ቁማርን የሚያዘወትር ሰው በሱሱ ይጠመዳል፡፡ ቁማርተኛ ሲያሸንፍ በቁማር ላይ ያለው ጉጉትና ምኞት ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ይህን የሐራም ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ ይቀጥላል፡፡ ሲሸነፍም፣ ምናልባት ያጣሁትን ገንዘቤን አስመልሳለሁ በሚል ጉጉትና ምኞት መጫወቱን ይቀጥላል፡፡ ሁለቱም የስራና የልማት ጸሮች፣ የማህበረሰብ ውድቀት ምንጮች ናቸው፡፡

የቁማር ዓይነቶች

በቀደምት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የቁማር ዓይነቶች በርካታና የተለያዩ ናቸው፡፡ በዘመናችን ከሚገኙ የቁማር ዓይነቶች መካከል የሚከተሉት አሉበት፡

  1. ማንኛውም አሸናፊው በማሸነፉ ከተሸናፊው ገንዘብ ሊወስድ ቅድመ መስፈርት የሚቀመጥበት ጫወታ፡፡ ለምሳሌ፡ የሆኑ ሰዎች ተሰባስበው ካርታ ሲጫወቱ በቅድሚያ ሁላቸውም የሆነ ያክል ገንዘብ ያስይዛሉ ወይም ያስቀምጣሉ፡፡ ከነሱ መካከል አሸናፊው የሁሉንም ገንዘብ ይወስዳል፡፡
  2. የሆነ ክለብ፣ ወይም ቡድን፣ ወይም ተጫዋች ያሸንፋል አያሸንፍም በሚል መወራረድ፡፡ የሚወራረዱት ሁላቸውም ቅድሚያ ገንዘብ በማስያዝ ሲሆን እያንዳንዳቸው ያሸንፋል ብለው በሚገምቱትና በሚያምኑበት ቡድን ወይም ተጫዋች ስም ገንዘብ ያስይዛሉ፡፡ ከዚያም የተወራረደበት ቡድን ካሸነፈ የተወራራጆቹን ገንዘብ ይወስዳል፡፡ የተወራረደበት ቡድን ከተሸነፈ ገንዘቡን ይከስራል፡፡
  3. ዕድልና ዕጣ፡ ለምሳሌ ዕጣው ሲወጣ የአንድ ሺህ ዶላር አሸናፊ ልሆን እችላለሁ በሚል እሳቤ በእጣው ላይ ለመሳተፍ የሆነ ካርድ በሆነ ያክል ዶላር ይገዛል፡፡
  4. ተንቀሳቃሽ የሆኑ በኤክትሮኒክስ መሳሪያ የሚሰሩ ወይም በኢንተርኔት ድህረ ገጾች ላይ የሚለቀቁ የቁማር ጨዋታዎች፡፡ በነዚህ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቹ ሁለት ግምቶች ይኖሩታል፡፡ እሱም ገንዘብ ማግኘት ወይም መክሰር ነው፡፡