ኢስላም፣ ልዩ ትኩረት የቸራቸው በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ስነምግባሮች
ኢስላም፣ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ መመሪያና ደንብ እንደዘረጋ ሁሉ፣ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎችም ሊላበሷቸው የሚገቡትን በርካታ ስነምግባሮችና ስርዓቶችን በመዘርዘር ልዩ ትኩረት ችሯቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
ታማኝነት፡
ታማኝነት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን የንግድ ግንኙነት ወሳኝ ስነ ምግባር ነው፡፡ አንድ ሙስሊም፣ ለሙስሊሞችም ሆነ ለካሃዲያን ያለልዩነት ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ታማኝነት፣ የአላህን ድንጋጌ ለሚከተል ሙስሊም ዋነኛ መገለጫ ባሕሪው ወይም ስነምግባሩ ነው፡፡ በዚህ ላይ ኢስላም ልዩ ትኩረት እንዳደረገ የሚከተሉትን መረጃዎች መመልከት እንችላለን፡፡
- አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡›› (አል ኒሳእ 58)
- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአንድ ሰውን አደራ አለመጠበቅንና በታመነበት ነገር ላይ ማጭበርበርን ከመናፍቅነት ባህሪ ቆጥረውታል፡፡ ‹‹የመናፍቅ መገለጫ ወይም ምልክቶች ሦስት ናቸው፤ ሲናገር ይዋሻል፤ ሲቀጥር ያፈርሳል፤ ሲታመን ይከዳል፡፡›› (አል ቡኻሪ 33 /ሙስሊም 59)
- ታማኝነት የሙእሚኖች ዋነኛ መገለጫቸው ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ምእመናን ፍላጎታቸውን ሁሉ በእርግጥ አገኙ(ዳኑ)››……. ‹‹እነዚያ እነርሱ ለአደራዎቻቸውና ለቃል ኪዳናቸው ጠባቂዎች (የኾኑት)›› (አልሙዕሚኑን 1-8) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አደራን የሚከዳን ወይም የሚያጭበረብርን ሰው ኢማኑን ውድቅ ያደረጉት ለዚህ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ ‹‹አማና የሌለው ሰው ኢማን የለውም፡፡›› (አሕመድ 12567)
- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት ከመሾማቸው በፊት በመካ ሳሉ፣ «እውነተኛው፣ ታማኙ» በሚል ቅፅል ስም ይታወቁ ነበር፡፡ ይህም ከሰዎች ጋር በነበራቸው ግንኙነትና ትስስር የታማኝነት ተምሳሌት ስለነበሩ ነው፡፡
እውነተኝነት
እውነተኝነትና ግልጽነት፣ ኢስላም ልዩ ትኩረት ከቸራቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሻጭና ገዢ በማስመልከት እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እውነተኞች ከሆኑና ግልጽ ካደረጉ ግብይታቸው ይባረክላቸዋል፡፡ ከሸሸጉና ከዋሹ ደግሞ የግብይታቸው በረከት ይነሳል፡፡›› (አልቡኻሪ 1973 / ሙስሊም 1532)
- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እውነተኝነትን አደራ! እውነተኝነት ወደ መልካም ነገር ይመራል፤ መልካም ነገር ደግሞ ወደ ጀነት ይወስዳል፤ አላህ ዘንድ እውነተኛው ተብሎ እስኪመዘገብ ድረስ አንድ ሰው እውነት ከመናገርና እውነትን ከመጠበቅ አይወገድም፡፡›› (ሙስሊም 2607)
- ኢስላም፣ ዕቃውን ለማዳነቅና ለማሻሻጥ ሲል በሐሰት የሚምል ሰው ከባድ ወንጀል ውስጥ እንደተዘፈቀ ያስተምራል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹ሦስት ዓይነት ሰዎችን የትንሳኤ ቀን አላህ አያናግራቸውም፡፤ወደነርሱም አይመለከትም፤ አያጠራቸውምም፤ አሳማሚ ቅጣትም አለላቸው፤›› ካሏቸው መካከል ‹‹በሐሰት መሐላ ዕቃውን የሚያሻሽጥ›› ብለው ጠቅሰዋል፡፡ (ሙስሊም 106)
ሥራን፣ኃላፊነትን በጥራትና በብቃት መወጣት
ማንኛውም ፈብራኪ ወይም ሰራተኛ ሙስሊም፣ ስራውን በጥራትና በብቃት፣ እንዲሁም ባማረ መልኩ የመስራት ግዳጅ አለበት፡፡ ይህ የሙስሊም ቋሚና የማይለወጥ መገለጫው ነው፡፡
- አላህ (ሱ.ወ) በማንኛቸውም ጉዳይ ላይ ጥራትና ማሳመርን ደንግጓል፡፡ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ላይም ተግባራዊ እንዲሆን አዟል፡፡ እንደ አደንና እርድ ያለ መጀመሪያ ሲመለከቱት በብቃትና በጥራት ለመስራት አስቸጋሪና የማይቻል በሚመስል ጉዳይ ላይ ሳይቀር ይህንኑ አስቀምጧል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ በሁሉም ነገር ላይ በጥራት መስራትን ወይም ማሳመርን ደንግጓል፡፡ ስትገድሉ አገዳደልን አሳምሩ፡፡ ስታርዱም አስተራረድን አሳምሩ፡፡ አንዳችሁ ማረጃ ካራውን ይሳለው፡፡ እርዱንም በቶሎ ያሳርፈው›› (ሙስሊም 1955)
- ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የአንድ ሰው አስክሬን ላይ ለመስገድ በተገኙበት አጋጣሚ ባልደረቦቻቸውን የአስክሬኑን ማረፊያ ጉድዷድ አስተካክለው እንዲያዘጋጁና አቀባበሩን እንዲያሳምሩ መመሪያ ይሰጧቸው ነበር፡፡ ከዚያም ወደነሱ በመዞር እንዲህ አሉ፡- ‹‹ይህ እናንተ የሰራችሁት የሞተውን ሰው የሚጠቅመው ወይም የሚጎዳው ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን አላህ አንድ ሥራ ሲተገበር በሚያምር መልክ መሰራቱን ይወዳልና ነው፡፡›› (አል በይሃቂ ፊ ሸዕቢል ኢማን 5315) በሌላ ዘገባ ደግሞ፣ ‹‹አላህ (ሱ.ወ)፣ አንዳችሁ አንድን ነገር ሲሰራ በብቃት እንዲሰራው ይወዳል፡፡›› ብለዋል፡፡ (አቡ ያዕላ ሸዕበል ኢማን 4386) (ገጽ፣ 213 ተመልከት)