የባሕር ምግቦች
የባሕር ምግቦች ሲባል የሚጠቁመው በውሃ ውስጥ እንጂ የማይኖሩትን እንስሳት ነው፡፡
ባሕር ደግሞ ብዙ ውሃ ያለው ሲሆን እንደ ሐይቅና የመሳሰሉት ብዙ ውሃ ያለባቸው የውሃ ዓይነቶችም በዚሁ ስር ይካተታሉ፡፡
እነኚህ የባሕር ምግቦች፣ እንሰሳት ወይም እጽዋቶች ቢሆኑም የታደኑ ወይም ሞተው የተገኙ ሆነው በጤንነት ላይ ጉዳት የማያስከትሉ ከሆነ እነሱን መመገብ የተፈቀደ ነው፡፡
አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የባሕር ታዳኝና ምግቡ ለናንተም ለመንገደኞችም ተፈቀደ፡፡›› (አልማኢዳ 96)
ታዳኝ ማለት ከነነፍሱ የተያዘ ማለት ነው፡፡ ምግቡ የተባለው ደግሞ ከሞተ በኋላ ባሕር የተፋው ማለት ነው፡፡
የየብስ እንሰሳት
የየብስ እንሰሳትን መብላት የሚፈቀደው ሁለት መስፈርቶች ከተሟሉ ነው፡፡
እነሱን መመገብ የተፈቀደ መሆናቸውና
አደናቸው ወይም እርዳቸው ኢስላማዊውን ሕግ በተከተለ መልኩ የተከናወነ መሆኑ ነው፡፡
የሚፈቀዱ እንሰሳት የትኞቹ ናቸው?
ሐራምነታቸው ከቁርኣንና ከሱና ማስረጃ ከተገኘላቸው ውጭ ያሉ ሁሉም እንሰሳት መሰረታቸው የተፈቀደ ነው፡፡
የተከለከሉት የሚከተሉት ናቸው፡
-
አሳማ፡ በኢስላም ውስጥ አሳማ እርም የተደረገና እርኩስ ነው፡፡ እያንዳንዱ ገላውና አካሉ ከርሱም የሚወጣ ማንኛውም ነገር እርምና ነጃሳ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በክት፣ ፈሳሽ ደምም፣ የእሪያ (አሳማ) ስጋም … በናንተ ላይ እርም ተደረገ፡፡›› (አል ማኢዳ 3) አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአሳም ስጋ አሱ እርኩስ ነውና፡፡›› (አል አንዓም 145) እርኩስ ማለት ነጃሳ ማለት ነው፡፡
- ማንኛውም አዳኝ ጥርሶች ያሉት አውሬ፡ ይህ ማለት ማንኛውም ስጋ በሊታ አውሬ ለማለት ነው፡፡ እንደ አንበሳና ነብር ያሉ ትላልቆችና ግዙፎች ቢሆኑም አለያም እንደ ድመትና የመሳሰሉ ትናንሾችም ቢሆኑ ፍርዱ ልዩነት የለውም፡፡ ውሻም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡
- ማደኛ ያላቸው በራሪ አዕዋፍ፡ ይህ ስጋ በሊታ የሆኑ አዕዋፍን በሙሉ የሚመለከት ነው፡፡ ቁራ፣ ንስር አሞራንና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
- ነፍሳት፡ ማንኛውም በየብስ የሚኖሩ ነፍሳትን መብላት አይፈቀድም ምክንያቱም እነርሱ ለመታረድ አይመቹም፡፡ ከነሱ መካከል አንበጣ ለብቻው ተነጥሎ ይወጣል፡፡ እሱን መብላት ይፈቀዳል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሁለት ሙት ነገሮች ተፈቅደውልናል፤ አሳና አንበጣ፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 3228)
- እባብ፣ ዘንዶና አይጥ፡ እነኚህን መብላት ክልክል ነው፡፡ እንድንገላቸው ታዘናል፡፡ ነብዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አምስት ነገሮች አጥፊዎች ናቸው፡፡ በሐጅ ትጥቅ ላይ ሆኖም፣ ተፈቶም እነሱን መግደል ይፈቀዳል፡፡ እነሱም፡ እባብ፣ ጥቁር አሞራ፣ አይጥ፣ ተናካሽ ውሻና ቀርጮ፡፡›› (አል ቡኻሪ 3136 / ሙስሊም 1198)
- የቤት አህያ፡ ዕቃን ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝና ለመጫን የሚገለገሉበት አህያ ነው፡፡
የተፈቀዱ እንሰሳት ዓይነት
ከነዚህ መካከል አላህ የፈቀዳቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡
- በበረሃ የሚኖሩ፣ ከሰው ልጅ የሚሸሹ፣ ሰዎች ይዘውት ለማረድ የማይችሉትን የዱር እንስሳ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ልናድነው ይፈቀድልናል፡፡
- ሌላው ዓይነት ደግሞ ለማዳና በቀላሉ ሊያዝ የሚችል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ደግሞ በኢስላማዊ አስተራረድ ካልታረደ በስተቀር መመገቡ አይፈቀድም፡፡
ኢስላማዊ አስተራረድ
ኢስላማዊ መስፈርቶችን ያሟላ እርድ ማለት ነው፡፡
የኢስላማዊው አስተራረድ መስፈርቶች
- የሚያርደው ግለሰብ ለማረድ ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡ እሱም ሙስሊም ወይም የመጽሐፍት ባለቤቶችን፣ ክርስቲያንና አይሁዳውያንን የሚያካትት ሲሆን እርዱን መምረጥ የሚችልና ስለ እርድ የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡
- የሚያርድበት መሳሪያ እንደ ቢላዋ ያለ የሚቆርጥ፣ ደም የሚያፈስና ለማረድ ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡ እንሰሳቱን በክብደቱ በሚጫን መሳሪያ፣ ወይም የእንሰሳቱን ጭንቅላት በመግጨት ወይም በኤሌክትሪክ ንዝረት በማቃጠል መግደል እርም ነው፤ አይፈቀድም፡፡
- እጁን ለማረድ በሚያንቀሳቅ ጊዜ ‹‹ቢስሚላህ›› በማለት የአላህን ስም ማውሳት፡፡
- በእርድ ላይ መቆረጥ ያለባቸውን ክፍሎች መቁረጥ፡፡ እነርሱም የአየር ቧንቧ፣ ጉሮሮና ሁለቱ የደም ጋኖች ናቸው፡፡ እነኚህ፣ በአንገት ግራና ቀኝ ያሉ የደም ስሮች ናቸው፡፡ ከነኚህ አራት አካላት መካከል ሦስቱን ቢቆርጥ በቂ ነው፡፡
እነኚህ ጉዳዮች ከተሟሉ እርዱን መብላት ይበቃል፡፡ ነገር ግን ከእነኚህ መስፈርቶች መካከል አንዱ ከተጓደለ እርሱን መብላት አይፈቀድም፡፡
የስጋ ዓይነቶች በምግብ ቤትና በልኳንዳዎች የሚገኝ ስጋ
- ሙስሊም ወይም የመጽሐፍቱ ባለቤቶች ያላረዷቸው፣ ቡዲሂስቶች፣ ሂንዶዎች፣ እንዲሁም ሃይማኖት የለሾች ያረዷቸው፣ ያልተፈቀዱና እርም የተደረጉም ናቸው፡፡ ብዙሃኑ ነዋሪቿ ሙስሊም ወይም የመጽሐፍ ባለቤቶች ባልሆነች ሀገር ውስጥ የሚገኙ ምግብ ቤቶችና ልኳንዳዎችም በዚህ ስር ይካተታሉ፡፡ ተቃራኒ የሆነ ብይን እስካልተረጋገጠለት ድረስ ይህ ዓይነቱ ሐራም ነው፡፡
- ሙስሊም ወይም የመጽሐፍት ባለቤት የሆነ አራጅ ኢስላማዊውን ሕግ በተከተለ መልኩ ያረደውን መብላት በአንድ ድምፅ የሚፈቀድ ወይም ሐላል መሆኑ የጸደቀ ነው፡፡
- አንድ ሙስሊም ወይም የመጽሐፍት ባለቤት የሆነ ሰው ኢስላማዊውን ሕግ ባልተከተለ መንገድ እንስሳው እራሱን ስቶ እንዲሞት፣ ወይም ውሃ ውስጥ ሰጥሞ እንዲሞት የተደረገ እንስሳ ስጋ፡፡ ይህን ዓይነቱን መብላት ክልክል ነው፡፡
- አንድ አስተራረድ በማያውቅ የመጽሐፍት ባለቤት በሆነ ግለሰብ ወይም ምግብ ቤትና ልኳንዳ ውስጥ የታረደ፡፡ በመሰረቱ ይህ ዓይነቱም ከነሱ እርድ ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ እናም ምንም እንኳ ሐላል መሆኑ ግልጽ የሆነን ስጋ ፈልጎ መመገቡ በላጭ ቢሆንም፣ እንዲህ ያለውን እርድ መመገብ የተፈቀደ መሆኑን የሚያጸድቅ አስተያየት ትክክል ነው፡፡ ሲመገቡት ግን የአላህን ስም ማውሳት መዘንጋት የለበትም፡፡