ሸሪዓዊው አደን

ሸሪዓዊው አደን የሚፈቅደው፣ ስጋቸው የሚፈቀድ፣ ነገር ግን እነርሱን በቁጥጥር ስር አውሎ መባረክና ማረድ የማይመች የሆኑ እንስሳትን ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ስጋ በሊታ ከሆኑት በጫካና በዱር የሚገኙ አዕዋፍ፣ እንዲሁም ሚዳቋ፣ ጥንቸልና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ለአደን መስፈርቶች አሉት፡፡ ከነርሱም መካከል፡

  1. አዳኙ፣ ጤናማ አዕምሮ ያለው፣ አደንን አስቦ የወጣ፣ ሙስሊም አለያም ከመጽሐፍት ባለቤት የሆነ መሆን አለበት፡፡ ጣዖት አምላኪ ወይም አዕምሮን የሳተ ሰው ያደነው አይፈቀድም፡፡
  2. እንሰሳው በመበርገግና ከሰው በመራቁ ምክንያት ተባሮ ሊያዝና ሊታረድ የማይችል መሆን አለበት፡፡ እንደ ዶሮ፣ ፍየልና በግ፣ እንዲሁም ከብት አይነት ከሆነ ማደን አይቻልም፡፡
  3. እንሰሳው የሚገደልበት መሳሪያ እንደ ቀስት፣ ጥይትና የመሳሰሉ መሳሪያዎች ዓይነት በስለቱ የሚገድል መሆን አለበት፡፡ እንደ ድንጋይና መሰል በክብደቱየሚገድል ዓይነት፣ ሰውዬው እንሰሳው ከመሞቱ በፊት ደርሶ የሚባርከውና የሚያርደው ካልሆነ በስተቀር መመገቡ አይፈቀድም፡፡
  4. ማደኛ መሳሪያውን ከመተኮሱ ወይም ከመልቀቁ በፊት፣ ‹‹ቢስሚላህ›› በማለት የአላህን ስም ማውሳት አለበት፡፡
  5. እንሰሳውን ወይንም በራሪውን ካደነው በኋላ ሳይሞት በሕይወት ካገኘው በማረድ ሐላል ሊያደርገው ይገባል፡፡
  6. ለመብላት ካልሆነ በስተቀር እንሰሳትን ማደን እርም ነው፡፡ ያደኑትን ላይበሉ፣ ለመዝናናትና ለሌላ ጥቅማ ጥቅም እንሰሳትን ማደን ክልክል ነው፡፡

 የመብላትና የመጠጣት ስርዓት

አላህ ለሰው ልጆች የዋለውን ጸጋ ለማስታወስ፣ ከበሽታዎች ለመጠበቅ፣ ማባከንን እና፣ ድንበር ከማለፍ መጠበቅን ይመስል ዓላማንና አምላካዊ ጥበብን ለማረጋገጥ፣ አላህ (ሱ.ወ) በምግብና መጠጥ ውስጥ ብዙ ስርዓቶችን ደንግጓል፡፡

ከነኚህ ስርዓቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. በወርቅና ብር ዕቃዎች፣ ወይም የሁለቱ ቅብ በሆኑ ዕቃዎች ላይ መመገብ ክልክል ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ በዚህ ውስጥ ብክነት፣ ድንበር ማለፍ፣ አና የድሆችን ቀልብ መስበር ስላለበት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በወርቅና ብር ዋንጫዎች አትጠጡ፤ በነርሱም ትሪዎች ላይ አትመገቡ፤ እርሷ በዚህች ዓለም የነርሱ (የከሃዲያን)፣ በወዲያኛው ዓለም ደግሞ የኛ ነች፡፡›› (አል ቡኻሪ 5110 / ሙስሊም 2067)
  2. ከምግብ በፊትና በኋላ እጅን መታጠብ፡፡ በእጅ ላይ ቆሻሻና የምግብ ቅሪት ካለበት ደግሞ መታጠቡ የጠበቀ ይሆናል፡፡
  3. መብላት መጠጣት ከመጀመሩ በፊት፣ ‹‹ቢስሚላህ›› ማለት፡፡ ትርጉሟ፡ በአላህ ስም በረከትን እፈልጋለሁ፣ በርሱም እታገዛለሁ፤ ማለት ነው፡፡ ከረሳና በምግቡ መሐከል ካስታወሰ፣ ‹‹ቢስሚላሂ ፊ አወሊሂ ወኣኺሪሂ›› (መጀመሪያውንም መጨረሻውንም በአላህ ስም) ይላል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) የመመገብ ስርዓትን የማያውቅና የማያሰምርን አንድ ትንሽ ሕፃን ልጅ አይተው ሊያስተምሩት እንዲህ አሉት፡- ‹‹አንተ ልጅ ሆይ! የአላህን ስም አውሳ፤ በቀኝ እጅህ ብላ፤ ከአጠገብህም ብላ፡፡›› ( አል ቡኻሪ 5061 / ሙስሊም 2022)
  4. በቀኝ እጅ መብላትና መጠጣት፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በግራ እጃችሁ አትብሉ፤ ሸይጣን የሚበላው በግራ እጁ ነው፡፡›› ( ሙስሊም 2019)
  5. ቆሞ ባይበላና ባይጠጣ ይወደድለታል፡፡
  6. አንድ ሰው እርሱ አጠገብ ካለ ምግብ መብላትና ሰዎች ፊት ለፊት ካለው አለመብላት ከአደብ ነው፡፡ ከሰዎች ፊት እያነሱ መብላት፣ ስርዓት ማጣት ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለልጁ፣ ‹‹ከአጠገብህም ብላ፡፡›› ብለውታል፡፡
  7. ጉርሻ ከወደቀ ማንሳትና ያለባትን ቆሻሻ ማስወገድ እስከተቻለ ድረስ ማበስና መብላት ይወደዳል፡፡ በዚህ ውስጥ ጸጋንና ምግብን መጠበቅ አለበት፡፡
  8. የምግብን ነውር አለመናገር፣ አለማዋደቅና አለመናቅ፡፡ ከተቻለ ያድንቅ፤ አለበለዚያ፣ ይተወውና ዝም ይበል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንዴም ምግብን አነውረው አያውቁም፡፡ ከፈለጉት ይበሉታል፤ ከጠሉት ደግሞ ይተውታል፡፡ (አል ቡኻሪ 5093/ሙስሊም 2064)
  9. ምግብን አለማብዛትና በርሱም አለመወጠር፡፡ ይህ የበሽታና የድብርት ምንጭ ነው፡፡ መሐከለኛ መሆን የነገሮች ሁሉ ያማረው ገጽታ ነው፡፡ ጉዳዩ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት ነው፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ከሆድ የከፋን ዕቃ አልሞላም፡፡ ለኣደም ልጅ፣ ወገቡን ቀና የሚያደርግበት ጥቂት ጉርሳዎች ይበቁታል፡፡ መብላት የግድ ከሆነ ግን፣ አንድ ሦስተኛውን ለምግቡ፣ ሌላ አንድ ሦስተኛውን ለመጠጡ፣ ሌላ አንድ ሦስተኛውን ደግሞ ለአየር ያድርገው፡፡›› (አትቲርሚዚ 2380/ ኢብኑ ማጃህ 3349)
  10. ሲያበቃ ‹‹ አልሐምዱሊላህ ›› በማለት ከሰዎች ብዙዎችን ሳያካትት እርሱን በመመገብ ያበለጸገውን አላህን ያመሰግናል፡፡ በዚህም ላይ አክሎ፣ ((አልሐምዱ ሊላሂ አለዚ አጥዐመኒ ሓዛ ወረዘቀኒሂ ሚን ገይሪ ሐውሊን ሚኒ ወላ ቁዋህ)) -‹‹የኔ ብልሃትና ኃይል ሳይኖርበት ይህንን የመገበኝና የሰጠን አላህ ይመስገን›› ማለት ይችላል፡፡