የተባረከው የእርድ በዓል

ዒድ አልአድሓ፣ በወርሃ ዙልሒጃ አስረኛ ቀን ላይ የሚከበር ሁለተኛው የሙስሊሞች በዓል ነው፡፡ ይህ ወር በኢስላማዊው ቀመር አስራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡ በዚህ ዕለት በርካታ ትሩፋቶች ይገኛሉ፡፡ ከነኚህም ትሩፋቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ሪያዎቹ አስር ቀናቶች ናቸው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-‹‹ከነዚህ አስርት ቀናት ይበልጥ አላህ ዘንድ በውስጣቸው የሚሠሩ መልካም ሥራዎች ተወዳጅ የሚሆኑበት ቀን የለም፡፡›› ብለው ሲናገሩ ባልደረቦቻቸው፣ «በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን?» በማለት ጠየቁ፤ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አዎን! ነፍሱንና ንብረቱን ይዞ የወጣ፣ ከዚያም አንዱንም ይዞ ያልተመለሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን (አይበልጥም) አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 926 / አት ቲርሚዚ 757)
  2. የታላቁ ሐጅ ዕለት ነው፡ በውስጡ ከሐጅ ሥራዎች እጅግ የላቀው፣ አንገብጋቢውና የተከበረው ሥራ ይገኛል፡፡ ያም፣ በካዕባ ዙሪያ መዞር፤ እርድን መፈፀም፤ ጀምረተል ዐቀባ ላይ ጠጠር መወርወርና ሌሎች ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡

በእርዱ ቀን(የውመ ነሕር) የሚሠሩ ሥራዎች

ሐጅ ላይ ላልሆነ ሰው፣ በዒድ አልአድሓ ዕለት ከዘካተል ፊጥር ውጭ በጾም ፍች በዓል ላይ የሚተገበሩ ነገሮችን በሙሉ መተግበር ይፈቀድለታል፡፡ ዘካተል ፊጥር(የጾም ፍች ምጽዋት)፣ በጾም ፍቺ በዓል ላይ ብቻ የሚተገበር ነው፡፡ እነኚህን ተግባራት ከዚህ በፊት ጠቅሰናቸዋል፡፡

የእርድ በዓል (ዒድ አልአድሓ)፣ ወደ አላህ መቃረቢያ እርድ (ቁርባን) የሚቀርብበት ዕለት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡

እርድ(ኡዱሒያ)፡ እርድ(ኡዱሒያ)፣ በእርድ ቀን ከዒድ ሠላት መልስ ወደ አላህ ለመቃረብ የሚሰዋ ወይም የሚታረድ ግመል፣ ከብት፣ ወይም ፍየልና በግ ሲሆን የወርሃ ዙል ሒጃ አስራ ሦስተኛ ቀን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሊተገበር ይችላል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ስለዚህ ለጌታህ ስገድ (በስሙ) ሰዋም፡፡›› (አል ከውሰር 2) አንቀጹ በዒድ ሠላትና በዒድ ዕለት በሚፈፀሙ እርዶች ተተርጉሟል፡፡

ኢስላማዊ ፍርዱ፡ እርድ፣ በሚችል ሰው ላይ ጠበቅ ያለ ሱና ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ለራሱና ለቤተሰቦቹ ማረድ አለበት፡፡

ለእርድ የሚቀርበው እንሰሳ ማሟላት ያለበት መስፈርት

  1. ከቤት እንሰሳት መሆን አለበት፡፡ እነሱም፡- ፍየል፣ በግ፣ ከብትና ግመል ናቸው፡፡ ከነዚህ ሌላ ያሉ እንሰሳት ወይም በራሪ አዕዋፋት ለእርድ አይቀርቡም፡፡ አንድ ፍየል ወይም በግ ለአንድ አባወራ ከነቤተሰቡ ይበቃዋል፡፡ በአንድ በሬ (ላም) ወይም ግመል ላይ ሰባት አባወራ ሊሳተፍ ይችላል፡፡
  2. የሚፈለግበት የዕድሜ ገደብ ላይ የደረሰ መሆን አለበት፡፡ የሚፈለገው የዕድሜ ገደብ፡- ለበግ ስድስት ወር፤ ለፍየል አንድ ዓመት፤ ለበሬ(ላም) ሁለት ዓመት፤ እና ለግመል አምስት ዓመት ነው፡፡
  3. እንሰሳው ግልጽ ከወጣ ነውርና ጉድለት የጸዳ መሆን አለበት፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አራት ዓየነት እንሰሳት ለእርድ ብቁ አይደሉም፡- ጠንጋራነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ፤ ህመሟ ይፋ የሆነ እንሰሳ፤ አንካሳነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ እና መረቅ የማይወጣት በጣም የከሳች እንሰሳ ›› (አል ነሳኢ 4371 አት ቲርሚዚ 1497)

የበዓል እርዱ ምን ይደርጋል?

  • ከእርድ ስጋ ላይ መሸጥ አይፈቀድም፡፡
  • እርድ የሚፈጽም ሰው፣ ስጋውን ሦስት ቦታ ከፍሎ፣ አንድ ሦስተኛውን ራሱንና ቤተሰቡን ይመግብበታል፤ ሌላኛውን አንድ ሦስተኛ (ለጓደኛና ቤተ ዘመድ) ስጦታ ያደርገዋል፤ የተቀረውን አንድ ሦስተኛ ደግሞ ለድሆች ይመጸውታል፡፡
  • አንድ ሰው፣ ለእርድ ሌላ ግለሰብን ቢወክል፣አለያም እርድ በመፈፀምና ስጋውን ለችግረኞች በማከፋፈል ሥራ ላይ ለተሰማሩ ታማኝ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የእርድ ገንዘቡን ሊሰጥ ይችላል፡፡

የነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) ከተማ (መዲናን) መጎብኘት

መዲና፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የመካ ጣዖታዊያን ሲያንገላቷቸው ከመካ ወጥተው የተሰደዱበት ከተማ ነች፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መዲና እንደደረሱ መጀመሪያ ያከናወኑት ሥራ የተከበረውን መስጂዳቸውን መገንባት ነበር፡፡ ይህ መስጂድ የዕውቀትና የኢስላማዊ ጥሪ ማዕከልና በሰዎች መሐከል መልካም ነገርን ማሰራጪያ ጣቢያ ሆኗል፡፡

በሐጅ ስነሥርዓትም ሆነ በሌላ አጋጣሚ የነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ መጎብኘት እጅግ የተወደደ ነው፡፡

ይህ ጉብኝት ከሐጅ ሥርዓት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ ለሱ ብቻ የተለየ ወቅትም የለውም፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ወደ ሦስቱ መስጂዶች ካልሆነ በስተቀር ጓዝ ተጭኖ ጉዞ አይደረግም፤ መስጂደል ሐራም፤ይህ መስጂዴና መስጂደል አቅሷ፡፡›› (አል ቡኻሪ 1139 /ሙስሊም 1397 /አቡዳውድ 2033)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከመስጂደል ሐራም በስተቀር በዚህ መስጂዴ ውስጥ የሚሰገድ ሠላት ከሱ ባሻገር ባሉ መስጂዶች ውስጥ ከሚሰገዱ ሠላቶች በአንድ ሺህ ይበልጣል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1133/ ሙስሊም 1394)

በመዲና ውስጥ ሊጎበኙ የሚገቡ ነገሮች ማናቸው?

አንድ ሙስሊም መዲናን ሲጎበኝ፣ዓላማው አድርጎ መነሳት ያለበት፣ የነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ መጎብኘትና በውስጡም ሠላት መስገድን ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ መዲና መምጣቱ ካልቀረ የሚከተሉትን ጉዳዮች መፈፀም ይፈቀድለታል፡፡

  1. በተከበረው ረውዳ ውስጥ ሠላት መስገድ፡ ይህ ስፍራ በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ ውስጥ የሚገኝ ውስን ቦታ ሲሆን፣ በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ቤትና በሚንበራቸው መሐከል የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ በሱ ውስጥ መስገድ ታላቅ ትሩፋት አለው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በቤቴና በሚንበሬ መሐከል ያለው ስፍራ ከጀነት ጨፌዎች አንዱ ጨፌ ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 1137 /ሙስሊም 1390)
  2. ለነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ሰላምታ ማቅረብ፡ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መካነ መቃብር በመሄድ፣ ከቀብሩ ፊት ፊት በመቆም፣ ፊትን ወደ ቀብሩ በማዞር፣ ለቂብላ ጀርባን በመስጠት፣ በስርዓትና ድምጽን ዝቅ በማድገረግ፣ «አሰላሙ ዐለይከ ያ ረሱ..ለላህ ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ አሽሃዱ አነከ በለግተ ርሪሳላ ወአደይተል አማና ወነሠሕተል ኡማ ወጃሃድተ ፊላሂ ሐቀ ጂሃዲሂ ፈጀዛከላሁ ዐን ኡመቲከ አፍደለ ማጀዛ ነቢየን አን ኡመቲሂ» - (አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ሰላምና የአላህ እዝነት እንዲሁም በረከቱ በርስዎ ላይ፡፡ እርሶ መልክትዎን እንዳስተላለፉ፣ አደራዎን እንደተወጡ፣ ለሕዝብዎ መልካሙን ሁሉ እንደመከሩ፣ በአላህ መንገድ ላይ እውነተኛውን ትግል እንደታገሉ እመሰክራለሁ፡፡ አላህ አንድ ነብይ ለሕዝቦቹ በዋለው ውለታ ከሚከፍለው ምንዳ በላጭ የሆነውን ምንዳ ለሕዝብዎ በዋሉት ውለታ ይክፈልዎት፡፡) ይላል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ) እስትንፋሴን መልሶልኝ እኔ ለሰላምታው አጸፋውን ብመለስለት እንጂ አንድም ሰው በኔ ላይ ሰላምታን አያቀርብም፡፡›› ( አቡ ዳውድ 2041) ከዚያም በቀኝ አቅጣጫ ትንሽ ፈቀቅ ይልና የረሱል ሰ.ዐ.ወ ተቀዳሚ ምትክ በሆኑት ከሰሃቦች ሁሉ በላጭ በሆኑት አቡበክር ላይ ሰላምታ ያቀርባል፡፡ ከዚያም ጥቂት ወደ ቀኙ ፈቀቅ ይልና በሁለተኛው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኸሊፋ(ምትክ)፣ በአቡበክር አሲዲቅ(ረ.ዐ) ላይ፣ በመቀጠልም ከአቡ በክር ቀጥሎ ከሠሓቦች ሁሉ በላጭ በሆኑት በዑመር አልፋሩቅ(ረ.ዐ) ላይ ሰላምታን ያቀርባል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰው ልጅ ሁሉ በላጩ ሰው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ጥቅምም ሆነ ጉዳትን ማስከሰት አይችሉም፡፡ ስለሆነም እርሳቸውን መለመን ወይም ድረሱልኝ ብሎ መጣራት ፈፅሞ አይፈቀድም፡፡ ሁሉም የአምልኮ ዘርፎች መፈፀም ያለባቸው፣ ለርሱ ምንም አጋር ለሌለው ለአላህ(ሱ.ወ) ብቻ ነው፡፡
  3. የቁባእ መስጂድ ጉብኝት፡ በኢስላም ታሪክ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂዳቸውን ከመስራታቸው በፊት የተሰራ የመጀመሪያው መስጂድ ነው፡፡ መዲና የመጣ ሰው የቁባን መስጂድ መጎብኘት ይወደድለታል፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ይጎበኙት ነበር፡፡ እንዲህም ብለዋል፡- ‹‹ከቤቱ ተጸዳድቶ በመውጣት፣ ከዚያም ወደ ቁባእ መስጂድ በመምጣት ሠላትን የሰገደ ሰው የዑምራን ምንዳ ያገኛል፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 1412)