የሠላት ገጽታ

  1. ማሰብ (ኒያ) ኒያ ለሠላት ትክክለኛነት መስፈርት ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የመግሪብ ወይም የዒሻእ ሠላት መሆኑን ለይቶ፣ በልቦናው በሠላት አላህን መገዛት ማለም፣የሠላት ኒያን ይገልፃል፡፡ ድምፅን ከፍ በማድረግ ሐሳቡን በንግግር መግለጽ አይፈቀድም፡፡ የሚፈለገው በልቦናውና በሕሊናው ማለም ብቻ ነው፡፡ ይህን ድምፅ በማውጣት መግለጽ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ኒያን በንግግር መግለጽ ከነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) ሆነ ከተከበሩት ባልደረቦቻቸው ስላልተላለፈ ነው፡፡
  2. ለሠላት እንደቆመ አላሁ አክበር (አላህ ትልቅ ነው፡፡) ይላል፡፡ በዚህን ጊዜ፣ የውስጥ መዳፉን ወደ ቂብላ አቅጣጫ በማዞር፣ እጁን በትከሻው ልክ ወይም የበለጠ ከፍ ያደርጋል፡፡ አላሁ አክበር ከሚለው ቃል ውጭ ሌላ ዓይነት ቃልን መጠቀም አይቻልም፡፡ ትርጉሙም፡ ክብር፣ የበላይነትና ኃያልነት ለአላህ የተገባ ነው ማለት ነው፡፡ አላህ ከርሱ ሌላ ካሉ አካሎች ሁሉ ታላቅ ነው፡፡ ከዱንያና በውስጧ ካሉ ፍላጎቶችና መርኪያዎች ሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ስለሆነም ስንሰግድ በልቦናችንና በሕሊናችን ተመስጠን ሁሉን ነገር ወደ ጎን በመተው ወደ ታላቁ አላህ እንዙር፡፡

 

  1. አላሁ አክበር ካለ በኋላ፣ ቀኝ እጁን በግራ እጁ ላይ በማነባበር በደረቱ ላይ ያስቀምጣል፡፡ ምንጊዜም ሲቆም ማድረግ ያለበት ይህንን ነው፡፡
  2. የመክፈቺያ ዱዓ ቢል የተወደደ ነው፡፡ እሱም፡- «ሱብሓነከላሁመ ወቢሐምዲከ፣ ወተባረከስሙከ፣ ወተዓላ ጀዱከ፣ ወላ ኢላሃ ገይሩከ»- የሚለው ሲሆን፣ ትርጉሙ፣ «አምላካችን ሆይ ከምስጋና ጋር ጥራት ይገባህ ፡፡ ስምህ የተባረከ ነው፡፡ ልዕልናህ የላቀ ነው፡፡ ካንተ ሌላ አምላክ የለም፡፡» ማለት ነው፡፡
  3. አዑዙ ቢላሂ ሚነ ሸይጧኒ ረጂም (ከእርጉሙ ሰይጣን በአላህ እጠበቃለሁ) ይላል፡፡ ጥበቃን መፈለግ ይህ ነው ፡፡ ትርጉሙ፣ ‹‹ወደ አላህ በመጠጋት ከሴጣን ተንኮል እጠበቃለሁ›› ማለት ነው፡፡
  4. በስመላህን፣(ቢስሚላሂ ራሕማኒ ረሒም) - (በአላህ ስም እጅግ ርኀሩኀ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡) የሚለውን ሐረግ ያነባል፡፡ የበስመላህ መልዕክቱ፣ በአላህ ስም የምታገዝና የምባረክ ስሆን እጀምራለሁ ማለት ነው፡፡
  5. የፋቲሓን ምዕራፍ ያነባል፡፡ ፋቲሓ በአላህ መፅሐፍ ውስጥ ባለው ክብርና ደረጃ ታላቁ ምዕራፍ ነው፡፡
  • አላህ (ሱ.ወ) ይህን ምዕራፍ ማውረዱን በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ውለታ አድርጎ ቆጥሮታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትንና ታላቁንም ቁርኣን (በሙሉ) በርግጥ ሰጠንህ፡፡» ይላል፡፡ (አል ሂጅር 87) «ከሚደጋገሙ የኾኑን ሰባትን» የተባለው ፋቲሓን ነው፡፡ በዚህ ስያሜ የተሰየመችው የአንቀጾቿ ብዛት ሰባት ስለሆነ ነው፡፡
  • ሙስሊም ሁሉ ይህንን ምዕራፍ መማር አለበት፡፡ ምክንያቱም፣ ብቻውን ወይም ኢማሙ ድምጹን ከፍ አድርጎ በማያነብባቸው ሠላቶች ውስጥ ተከታይ ሆኖ የሚሰግድ ሰው፣ በሠላቱ ውስጥ እሷን ማነብነቡ ከሠላት ማዕዘናት መካከል አንዱ በመሆኑ ነው፡፡
  1. ፋቲሓን ካነበበ ወይም ኢማሙ ሲያነብ እያዳመጠ ከቆየ በኋላ፣ ኣሚን ማለት ይወደድለታል፡፡ ትርጉሙም አምላካችን ሆይ ተቀበለን ማለት ነው፡፡
  2. በመጀመሪያዎቹ ሁለት ረከዓዎች ላይ ከፋቲሓ አስከትሎ ሌላ ምዕራፍን ወይም አንቀጾችን ያነባል፡፡ ሦስተኛና አራተኛ ረከዓ ላይ ግን ፋቲሓን ብቻ በማንበብ ይገደባል፡፡
  • በፈጅር፣ በመግሪብና በዒሻእ ሠላቶች ላይ፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ረከዓዎች፣ ፋቲሓንም ከሱ ቀጥሎ የሚነበበውንም ክፍል፣ ድምጽ ከፍ ተደርጎ ይነበባል፡፡ በዙህርና በዐሥር ሠላት ላይ ግን ድምጽ ከፍ አይደረግም፡፡ የተቀሩት በሠላት ውስጥ የሚባሉ ውዳሴዎችና ሙገሳዎችም ሲነበቡ ድምፅ ከፍ አይደረግም፡፡
  • ሌሎች የሶላት ዚክሮች በልቦና ይባላሉ።
  1. ከዚያም፣ ልክ በመጀመሪያው ተክቢራ ላይ እንዳደረገው እጆቹን በትከሻዎቹ ትክክል ወይም ትንሽ ከፍ አድርጎ በማንሳትና የመዳፎቹን ውስጣዊ ክፍል ወደ ቂብላ በማቅጣጨት ለሩኩዕ ‹‹አላሁ አክበር›› ይላል፡፡
  2. በመዳፎቹ ጉልበቶቹን በመያዝ ወደ ቂብላ እንደተቅጣጨ ከወገቡ ጎንበስ በማለት ሩኩዕ ያደርጋል፤ ጭንቅላቱና ወገቡ ወጣ ገባ መሆን የለበትም፤ እንዲህም ይላል፡- ‹‹ሱብሓነ ረቢየል ዐዚም›› (ታላቁ ጌታዬ ከእንከንና ከጉድለት ጠራ፡፡) ይህን ውዳሴ ሦስት ጊዜ መደጋገም የተወደደ ነው፤ ግዴታው ግን አንድ ጊዜ ብቻ ማለት ነው፡፡ ሩኩዕ አላህን የሚያልቁበትና የሚያወድሱበት ዒባዳ ነው፡፡ ‹‹ሱብሓነ ረቢየል ዐዚም›› - ‹‹ታላቁን አላህ ከእንከንና ከጉድለት አጠረዋለሁ፤ እቀድሰዋለሁ፤›› ማለት ሲሆን፣ አንድ ሰጋጅ ይህንን የሚለው ከወገቡ ጎንበስ በማለት ለአላህ ያጎበደደና የተዋረደ ሆኖ ነው፡፡
  1. ልክ እንደ ከዚህ በፊቱ እጆቹን በትከሻዎቹ ትክክል ከፍ በማድረግና የመዳፎቹን ውስጠኛ ክፍል ወደ ቂብላ በማቅጣጨት ካጎነበሰበት ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡ ኢማም ወይም ብቻውን የሚሰግድ ከሆነ ደግሞ፣ ‹‹ሰሚዐላሁ ሊመን ሐሚደሁ›› - (አላህ ያመሰገነውን ሰው ሰማው) ይላል፡፡ ከዚያም ሁሉም ፡ ‹‹ሐምደን ከሲረን ጠይበን ሙባረከን ፊሂ ሚልኣሰማኢ ወል አርዲ ወሚልአ ማሺእተ ሚን ሸይኢን በዕድ›› - (በርካታ፣ መልካምና በውስጡ በረከት ያለው፣ በሰማያት ሙሉ፣ በምድር ሙሉ፣ ከነዚህም ሌላ አንተ በምትሻው ነገሮች ሙሉ የሆነ ምስጋና ይድረስህ) ይላሉ፡፡
  1. በማስከተል፣ በሰባት የሰውነት ክፍሎቹ መሬት ላይ በመደፋት ሱጁድ ያደርጋል፡፡ እነኚህም የሰውነት ክፍሎች ግንባር ከአፍንጫ ጋር፤ ሁለት መዳፎች፤ ሁለት ጉልበቶች እና ሁለት እግሮች ናቸው፡፡ ሱጁድ ሲያደርግ እጆቹን ከጎኖቹ ማራራቅ፣ ሆዱንና ጭኖቹን አለማጣበቅና እንዲሁም ጭኖቹንና ባቶቹን አለማገናኘት ይወደድለታል፡፡
  2. በሱጁድ ውስጥ፡ ‹‹ሱብሐነ ረቢየል አዕላ›› - (ከፍ ያለው ጌታዬ ከእንከንና ከጉድለት ጠራ) ይላል፡፡ ) ይህንን አንድ ጊዜ ማለት ግዴታ ሲሆን ሦስት ጊዜ መደጋገም ደግሞ ተወዳጅ ተግባር ነው፡፡ ሱጁድ፣ አላህን ከመለመኛ ስፍራዎች ሁሉ በላጩ ነው፡፡ ሰጋጆች በሱጁድ ውስጥ መባል ያለባቸውን ውዳሴዎችን ካሉ በኋላ የሚፈልጉትን የዱንያም ሆነ የኣኺራ ጉዳዮችን መለመን ይችላሉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ባሪያ ለጌታው እጅግ ቅርብ የሚሆንበት ስፍራ ሱጁድ ነው፤ ስለሆነም በርሱ ውስጥ ዱዓን አብዙ፡፡›› (ሙስሊም 482) ‹‹ሱብሐነ ረቢየልአዕላ›› የሚለው ሐረግ ትርጓሜ፡- ‹‹የላቀው አላህ፣ በትልቅነቱና በችሎታው የተቀደሰና ከሰማያት በላይ የላቀ ነው፤ ከማንኛውም ጉድለትና እንከንም የጠራ ነው›› ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ቃል እራሱን ዝቅ በማድረግና በመመሰጥ፣ በመሬት ላይ በመደፋት ሱጁድ ለሚያደርግ ሰው ሁሉ፣ በርሱና በጌታው መሐከል ያለን የማይነፃፀር ልዩነት እንዲያስታውስ የሚያደርግ የሆነ ማሳሰቢያ ነው፡፡ በመሆኑም ለጌታው በተመስጦና በመተናነስ ይሰግዳል፡፡
  1. ከዚያም ‹‹አላሁ አክበር›› በማለት ከመጀመሪያው ሱጁድ ቀና ብሎ ይቀመጣል፡፡ አቀማመጡም ግራ እግሩን በማንጠፍና ቀኝ እግሩን በመቸከል ቢሆን ተወዳጅ ነው፡፡ መዳፎቹን ከጉልበቱ ቀጥሎ ባለው የጭኑ ጠረፍ ወይም ጫፍ ላይ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
  • ሰጋጆች በሠላት ውስጥ በሚቀመጡበት በየትኛውም ጊዜ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ መቀመጣቸው የተወደደ ነው፡፡ ግን ለመጨረሻው ተሸሁድ በሚቀመጡበት ጊዜ በተጠቀሰው መልኩ ቀኝ እግርን በመቸከል፣ ግራ እግርን በማሾለክ፣ በእግር ላይ ሳይሆን በመሬት ላይ ተመቻችተው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡
  • ጉልበቱ ህመም የሚሰማው ወይም ልምድ በማጣት ምክንያት ለመጀመሪያው ተሸሁድ ወይም ለሁለተኛው ተሸሁድ በተነገረው መሰረት መቀመጥ ያልቻለ ሰው ሳይጨናነቅ ለተጠቀሰው አቀማመጥ የቀረበ በሆነ መልኩ መቀመጥ ይችላል፡፡
  1. በሁለቱ ሱጁዶች መካከል ሲቀመጥ፡ ‹‹ረቢ ኢግፊር ሊ፣ ወርሓምኒ፣ ወህዲኒ፣ ወርዙቅኒ፣ ወጅቡርኒ፣ ወዓፊኒ፣›› - (ጌታዬ ሆይ ምሕረትህን ስጠኝ፤ እዘንልኝ፤ ምራኝ፤ ሲሳይህን ለግሰኝ፤ ጠግነኝ፤ ጤናማ አድርገኝ፡፡) ማለት ይኖርበታል፡፡
  2. ከዚያም ልክ በመጀመሪያው ሱጁድ መልኩ ለሁለተኛ ጊዜ ሱጁድ ያደርጋል፡፡
  3. በመቀጠልም ከሁለተኛው ሱጁድ ‹‹አላሁ አክበር›› በማለት ተነስቶ ይቆማል፤
  4. ልክ እንዲሁ የመጀመሪያውን ረከዓ በሰገደው መልኩ ሁለተኛውንም ረከዓ ይሰግዳል ወይም ያስከትላል፡፡
  5. ከዚያም በሁለተኛው ረከዓ፣ ከሁለተኛው ሱጁድ ቀና ካለ በኋላ ለመጀመሪያው ተሸሁድ ይቀመጣል፡፡ ቁጭ ባለበት እንዲህ ይላል፡- ‹‹አትተሒይያቱ ሊልላሂ፣ ወሥሠለዋቱ፣ ወጥጠይባቱ፣ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀ ንነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካቱሁ፣ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲልላሂ አሣሊሒነ አሽሐዱ አን ላ ኢላሃ ኢልለ ላህ ወአሽሃዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፡››
  6. ከዚህ ቡሃላ እንደ ሰላቱ ዓይነት ባለ ሶስት ወይም አራት ረከዓ ሰላት ከሆነ የቀረውን የሰላት ክፍል ለመሙላት ይቆማል፤ ነገር ግን በሶስተኛም ሆነ በአራተኛ ረከዓዎች ላይ የሚነበነበው ፋቲሓ ብቻ መሆን አለበት፡፡
  • የሚሰገደው የሰላት ዓይነት እንደ ፈጅር ሰላት ባለ ሁለት ረከዓ ከሆነ ከዚህ በታች በተጠቀሰው መልኩ የመጨረሻውን ተሸሁድ ይከውናል፡፡
  1. ከዚህ በኋላ በመጨረሻው ረከዓ፣ ከሁለተኛው ሱጁድ በኋላ፣ ለማጠናቀቂያ ተሸሁድ ይቀመጣል፡፡ በመጀመሪያው ተሸሁድ የሚባለውን በሙሉ ካለ በኋላ በሚከተለው መልኩ ለነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ዱዓ ያደርጋል፡ ‹‹አላሁምመ ሠሊ ዐላ ሙሐመድ ወዓላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ሠልለይተ ዓላ ኢብራሂመ ወዓላ ኣሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ፤ ወባሪክ ዐላ ሙሐመዲን ወዓላ ኣሊ ሙሐመድ ከማ ባረክተ ዓላ ኢብራሂም ወዓላ ኣሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡››
  • በማስከተልም፡ ‹‹አዑዙ ቢላሂ ሚን ዐዛቢ ጀሐነመ ወሚን ዐዛቢል ቀብር ወሚን ፊትነቲል ማሕያ ወል መማት ወሚን ፊትነቲል መሲሒ ደጅጃል፡፡›› በማለት ዱዓ ማድረግ ይወደድለታል፡፡ በተጨማሪም የሚሻውን ነገር መለመን ይችላል፡፡
  1. በመጨረሻም ወደ ቀኙ በመዞር ‹‹አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ›› ይላል፤ ወደ ግራውም በመዞር ይህንኑ ይደግማል፡፡ አንድ ሰጋጅ በዚህ መልክ በማሰላመት ስግደቱን ያጠናቅቃል፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ሠላትን አስመልክተው፡ ‹‹በተክቢር ይታሰራል፤ በተስሊም ይፈታል›› ብለዋል፡፡ (አቡ ዳውድ 61/ አቲርሚዚ 3) ከሐዲሱ እንደምንረዳው ወደ ሠላት የሚገባው በመጀመሪው ተክቢራ ሲሆን ከርሱ የሚወጣው ወይም እርሱ የሚጠናቀቀው ደግሞ በተስሊም ወይም በሰላምታ መሆኑን ነው፡፡
  1. አንድ ሙስሊም የግዴታን ሠላቶች ከሰገደ በኋላ የሚከተሉትን ውዳሴና የሙገሳ ቃላትን ማለት ይወደድለታል፡፡
    1. . ሦስት ጊዜ ‹‹አስተግፊሩላህ›› (የአላህን ምሕረት እማፀናለሁ)
    2. ‹‹አላሁምመ አንተ ስሰላም ወሚንከ ስሰላም ተባረክተ ያ ዘል ጀላሊ ወል ኢክራም›› - (አምላካችን ሆይ አንተ ሰላም ነህ፤ ሰላምም ካንተ ነው፤ አንተ የልቅናና የልግስና ባለቤት ሆይ ከሁሉ በላይ ነህ፡፡) ‹‹አላሁምመ ላ ማኒዐ ሊማ አዕጠይተ ወላ ሙዕጢየ ሊማ መነዕተ ወላ የንፈዑ ዘል ጀድዲ ሚንከል ጀድዱ›› - (አምላካችን ሆይ! አንተ ለሰጠኸው ከልካይ፣ ለከለከልከውም ሰጪ የለም፤ የዝምድና ባልተቤትም ዝምድናው ካንተ የሚያብቃቃው አይደለም) ይላል፡፡
    3. ሰላሳ ሦስት ጊዜ ‹‹ሱብሓነላህ››፣ ሰላሳ ሦስት ጊዜ ‹‹አልሐምዱሊላሂ››፣ሰላሳ ሦስት ጊዜ ‹‹አላሁ አክበር›› በማለት ለመቶኛው ማሟያ ‹‹ላ ኢላሃ ኢለላሁ፣ ወሕደሁ ላ ሸሪ…ከ ለሁ ለሁል ሙልኩ ወለሁል ሐምዱ ወሁወ ዓለ ኩልሊ ሸይኢን ቀዲ…ር›› - (ከአላህ ባሻገር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም፤ በአምላክነቱ ብቸኛ ነው፤ አጋር የለውም፤ ንግሠና ሁሉ የርሱ ነው፤ ምስጋናም ሁሉ የርሱ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡) ይላል፡፡

የፋቲሓ ትርጓሜ በሚከተለው መልኩ ይገለፃል፡

‹‹ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለኾነው››፡ አላህን በባሕሪያቱ፤በተግባራቱ፣ በግልጽና ስውር ፀጋዎቹ በሙሉ ከውዴታና ከማላቅ በመነጨ መልኩ አመሰግነዋለሁ ማለት ነው፡፡

ጌታ(ረብ)፡ የሁሉ ፈጣሪ፤ ባለቤት፤ አስተናባሪና ባለ ጸጋ የሆነ አካል ማለት ነው፡፡ ዓለማት፡ የሚባለው ደግሞ ማንኛውም ከአላህ ባሻገር ያለ፣ የሰው፣ የጅን፣ የመላእክት፣ የእንሰሳትና የተቀሩት ፍጡራንን የሚገልጽ ቃል ነው፡፡

‹‹እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ፡›› እነኚህ ከአላህ የተዋቡ ስሞች መካከል ሁለት ስሞቹ ናቸው፡፡ ‹‹ርኅሩኅ›› ማለት ሁሉን ነገር የሚያዳርስ የሆነ ርኅራኄ ባለቤት ማለት ነው፡፡ ‹‹አዛኝ›› የሚለው ቃል ደግሞ ምእመናን ባሮቹን ብቻ የሚደርስ በሆነ የርኅራኄ ባህሪ የሚገለፅ ማለት ነው፡፡

‹‹የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነው››፡ የፍርዱና የግምገማው ቀን ባለቤትና አስተናባሪ ማለት ነው፡፡ ይህ አንቀጽ የመጨረሻውን ቀን ያስታውሳል፤ በመልካም ስራ ላይም ያበረታታል፡፡

‹‹አንተን ብቻ እንገዛለን፤ አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምናለን፤›› ጌታችን ሆይ! እኛ አምልኮን ላንተ ብቻ እንሰጣለን፤ በየትኛውም የአምልኮ ዓይነት ካንተ ጋር ሌላን አካል አናጋራም፤ በማንኛውም ጉዳያችን ላይ ካንተ ብቻ እርዳታና እገዛን እንፈልጋለን፤ እያንዳንዱ ጉዳያችን በአንተ እጅ ነው፤ ከርሱ የቅንጣት ታክልም ሌላ አካል ባለቤትነት የለውም፡፡ ማለት ነው፡፡

‹‹ቀጥተኛውን መንገድ ምራን››፡ ቀጥተኛውን መንገድ አመላክተን፤ አቅጣጨን፤ ግጠመን፤ ካንተ እስከምንገናኝ ድረስ በርሱ ላይም አጽናን ማለት ነው፡፡ ቀጥተኛው መንገድ ኢስላም ነው፡፡ እርሱም ግልጽ፣ ወደ አላህ ውዴታና ወደ ጀነት የሚያደርስ ወይም የሚወስድ መንገድ ነው፡፡ እርሱ ያ የነብያትና የመልዕክተኞች መደምደሚያ የሆኑት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የጠቆሙት መንገድ ነው፡፡ በርሱ ላይ በመጽናት እንጂ ለሰው ልጅ ስኬትና ደስታ ሊገኝ አይችልም፡፡

‹‹የነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን መንገድ››፡ የእነዚያን ቀጥተኛውን መመሪያ ያደልካቸውንና በሱም ላይ ያጸናሃቸውን ሰዎች፣ ማለትም የነብያትንና የፃድቃንን መንገድ ምራን ማለት ነው፡፡ እነሱ በርግጥ እውነትን አውቀው የተከተሉ ናቸው፡፡

‹‹በነሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውንና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ››፡ አንተ ከተቆጣህባቸውና ከተናደድክባቸው ሰዎች መንገድ አርቀን፤ ሰውረን፤ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ሐቅን አውቀው አልተገበሩትም፡፡ እነኚህ የሁዶችና መሰሎቻቸው ናቸው፡፡ ከተሳሳቱት ሰዎችም መንገድ ሰውረን፤ አርቀን፤ ማለት ደግሞ፣ ካለማወቃቸው የተነሳ ወደ እውነት ያልተመሩ ሰዎችን፣ ክርስቲያኖችንና መሰሎቻቸው የሚጠቁም ነው፡፡

ፋቲሐን፣ የሠላት ውስጥ ውዳሴዎችንና ሙገሳዎችን በቃሉ ያልያዘ ወይም ያልሸመደደ ሰው ምን ማድረግ አለበት?

በቅርቡ የሰለመና ፋቲሐን፣ የሠላት ውስጥ ውዳሴዎችንና ሙገሳዎችን በቃሉ ያልያዘ ወይም ያልሸመደደ ሰው የሚከተለውን መፈፀም ይኖርበታል፡

  • ግዴታ የሆኑ የሠላት ውስጥ ውዳሴዎችንና ሙገሳዎችን በቃሉ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚከተሉት ውዳሴዎች በዐረብኛ ቋንቋ መሆን አለባቸው፡፡ ፋቲሐና ተክቢር፤ ሱብሐነ ረቢየል ዐዚም፤ ሰሚዐላሁ ሊመን ሐመዲሁ፤ ረበና ወለከል ሐምድ፤ ሱብሐነ ረቢየል አዕላ፤ ረቢግፊርሊ፤ ተሸሑድ፤ ሠላት ዐለ ነቢይ፤ አሰላሙዐለይኩም ወራሕመቱላህ፡፡
  • አንድ ሙስሊም እነኚህን ውዳሴዎችንና ሙገሳዎችን በቃሉ እስከሚይዝ ወይም እስከሚሸመድድ ድረስ በሠላት ውስጥ የሚችለውን ተስቢሕ (ሱብሓነላህ)፣ ተሕሚድ(አልሐምዱሊላህ) እና ተክቢር(አላሁ አክበር) ደጋግሞ ማለት፣ ወይም በቃሉ የያዘውን የቁርኣን አንቀፅ እየደጋገመ ማንበብ አለበት፡፡ ምክንያቱም አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏልና ነው፡- ‹‹አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፡፡›› (አል ተጋቡን 16)
  • ይህ ሰው በዚህ ቆይታው ሠላቱን በተሟላ መልኩ ለመካናወን ይረዳው ዘንድ በጀመዓ መስገድን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህም ኢማሙ በተከታዩ ሰው በኩል የሚከሰቱ ክፍተቶችን ስለሚያሟላ ነው፡፡