በሠላት ውስጥ መመሰጥ
በሠላት ውስጥ መመሰጥ የሠላት እውነተኛ መገለጫና አንኳሩ ነው፡፡ መመሰጥ ማለት፡ አንድ ሰጋጅ፣ በሠላት ውስጥ የተናነሰና እራሱን ዝቅ ያደረገ ሆኖ፣ የሚያነበውን የቁርኣን አንቀጽ፣ ጸሎቱንና ውዳሴን በሕሊናው እያስተነተነ አላህ(ሱ.ወ) ፊት መቆሙ ነው፡፡
መመሰጥ፣ ከአምልኮዎች ሁሉ በላጩና የላቀ የታዛዥነት መገለጫ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ በመፅሐፉ ውስጥ መመሰጥ የምእመናን ባህሪ መሆኑን ትኩረት ሰጥቶ የተናገረው ለዚህ ነው ፡፡አላህ (ሱ.ወ)፡- #ምእመናን ፍላጎታቸውን ሁሉ በእርግጥ አገኙ (ዳኑ) እነዚያ እነሱ በስግደታቸው ውስጥ አላህን ፈሪዎች (የሆኑት); ይላል፡፡ (አል ሙእሚኑን 1-2)
በሠላት ውስጥ መመሰጥ የቻለ ሰው፣ የኢማንና የአምልኮን ጣዕም ማጣጣም ይችላል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የዓይን መርጊያዬ በሠላት ውስጥ ተደርጋልኛለች›› ያሉት ለዚህ ነው፡፡ (አል ነሳኢ 3940)
የዐይን መርጊያ ማለት፣ ከዳር የደረሰ ደስታ፣ ስኬትና እርካታን ማግኘት ነው፡፡
በሠላት ውስጥ ለመመሰጥ የሚረዱ መንገዶች
በሠላት ውስጥ ለመመሰጥ የሚረዱ መንገዶች አሉ፡፡ ከነሱም፡-
- አስቀድሞ ለሠላት መዘጋጀት
ዝግጅት ማለት፡ ወንዶች፣ የሚያምር ልብስ በመልበስና ወደ ሠላት በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ በመራመድ አስቀድሞ ወደ መስጂድ በመምጣት፣ ከሠላት በፊት የሚከናወኑ ነብያዊ ፈለጎችን በማከናወን የሚረጋገጥ ነው፡፡
- አዕምሮን የሚያጠምዱ፣ አዘናጊና እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን በቅድሚያ ማስወገድ
አንድ ሰው፣ ከፊት ለፊቱ ሐሳቡን የሚሰርቁ ምስሎች፣ ልብ የሚያንጠለጥሉ ጨዋታዎችና ሐሳቡን የሚሰርቁ ድምፆች ባሉበት መስገድ የለበትም፡፡ እንዲሁም፣ ሽንት ቤት መግባት እያስፈለገው፣ ተርቦ ወይም ተጠምቶ፣ ምግብና መጠጥ በቀረበበት ቅጽበት ሠላት መጀመር የለበትም፡፡ ይህ ሁሉ ያስፈለገው ሰጋጁ አዕምሮው ነፃ እንዲሆንና ከባድ ጉዳይን በማስተናገድ እንዲጠመድ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከፊት ለፊቱ የሚያገኘው ሠላቱን ይሆናል፡፡ ሠላት ደግሞ ከጌታው ጋር የሚነጋገርበት ወሳኝ ነገር ነው፡፡
- በሠላት ውስጥ መረጋጋት
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሠላትን ሲሰግዱ፣ በሩኩዓቸውም በሱጁዳቸውም ውስጥ፣ እያንዳንዱ መገጣጠሚያቸው ወደ ቦታው እስኪመለስ ድረስ በመረጋጋት ነበር፡፡ ሠላቱን ማሳማር ያልቻለውን ሰውዬ፣ በሠላቱ ውስጥ በሚፈፅማቸው ተግባሮችን በሙሉ በእርጋታና በዝግታ እንዲፈፅም አዘውታል፡፡ መቻኮልን ከልክለዋል፤ችኮላን ከአሞራ ውሃ አጠጣጥ ጋር አመሳስለውታል፡፡
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- #በስርቆት አደገኛው ሰው ማለት ከሠላቱ ላይ የሚሰርቅ ነው፡፡; ሲሉ፣ ሠሓቦች፡ «ከሰላቱ ላይ የሚሰርቀው እንዴት ነው?» በማለት ጠየቁ፡፡ እሳቸውም፡ #ሩኩዓንም ሱጁዷንም በማጓደል ነው; በማለት መለሱላቸው (አህመድ 22642)
በሠላት ውስጥ የማይረጋጋ ሰው፣ በሠላቱ ሊመሰጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም መፍጠን መመሰጥን ስለሚጻረር ነው፡፡ እንደ አሞራ ጎንበስ ቀና ማለት ምንዳን ያሳጣል፡፡
- ፊት ለፊቱ የሚቆመውን አካል ኃያልነት ማሰብ
በሠላት ውስጥ ሆኖ የፈጣሪን ኃያልነትና ልቅና፣ የነፍሱን ደካማነትና ወራዳነት፣እንዲሁም ጌታው ፊት በመቆም እየተማፀነውና እያናገረው እንደሆነ ያስብ፣ ለርሱ በመዋደቅና በመዋረድ ፈጣሪውን ይለምን፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ አላህ (ሱ.ወ) በወዲያኛው ዓለም ለምእመናን ያዘጋጀውንና የደገሰውን፣ እንዲሁም አጋሪያን የሚጠብቃቸውን ቅጣትና ውርደት ያስተንትን፡፡ በወዲያኛው ዓለም ጌታው ፊት የሚቆምበትን ጊዜ ያስታውስ፡፡
አንድ ሙእሚን በሠላት ውስጥ ሆኖ ይህን በአዕምሮው መሳል ከቻለ፣ አላህ በመፀሐፉ ውስጥ፣ ‹‹ጌታቸውን እንደሚገናኙ እርግጠኞች ናቸው›› ብሎ ከዘከራቸው ሰዎች ይሆናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- #(ሠላት) በፈሪዎች ላይ እንጅ በሌላው ላይ በእርግጥ ከባድ ናት፡፡ እነዚያ እነርሱ ጌታቸውን የሚገናኙ እነሱም ወደርሱ ተመላሾች መኾናቸውን የሚያረጋግጡ በኾኑት ላይ እንጅ ከባድ ናት; ይላል፡፡ (አል በቀራ 45-46)
አንድ ሰጋጅ በሠላቱ ውስጥ መመሰጥን የሚያገኘው፣ አላህ (ሱ.ወ) እንደሚሰማው፣ የጠየቀውን እንደሚሰጠውና ለልመናው ምላሽ እንደማይነፍገው በሕሊናው መሳል በሚችለው ደረጃ ልክ ነው፡፡
- የሚነበቡ አንቀጾችን፣ የሠላት ውዳሴና ሙገሳዎችን ማስተንተንና ከነሱ ጋር በሕሊና መጓዝ
ቁርኣን የተወረደው ሊያስተነትኑት ዘንድ ነው፡፡ #ይህ ወዳንተ ያወረድነው ብሩክ መጽሀፍ ነው አንቀጾቹን እንዲያስተነትኑና የአዕምሮዎች ባለቤቶችም እንዲገሰጹ አወረድነው፡፡; አንድ ሰው የሚያነባቸውን አንቀጾች፣ የሚላቸውን ውዳሴዎችና ዱዓዎች ትርጉም ካላወቀ ሊያስተነትን አይችልም፡፡ ትርጉሙን መረዳት ሲችል፣ በአንድ በኩል እርሱ ያለበትን ሁኔታና ተጨባጭ ነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአንቀጾቹን፣ የውዳሴና ልመናዎቹን ትርጉም ማስተንተን ይችላል፡፡ ከዚህም፡ መመሰጥ፣እንዲሁም ለጌታው መዋረድና መዋደቅ ይገኝለታል፡፡ ጥልቅ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ምናልባትም ዓይኖቹ ሊያነቡ ይችላሉ፡፡ አንድም አንቀጽ ጫና ሳያሳድርበት አያልፍም፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- #እነዚያም በጌታቸው አንቀጾች በተገሰጹ ጊዜ (የተረዱ ተቀባዮች ኾነው እንጅ ) ደንቆሮችና ዕውሮች ኾነው በርሷ ላይ የማይደፉት ናቸው፡፡; ይላል፡፡ (አል ፉርቃን 73)
የጁምዓ ሠላት
አላህ (ሱ.ወ) በጁምዓ ዕለት፣ በዙህር ሠላት ወቅት እጅግ በጣም የላቀ የኢስላም መገለጫና ከግዴታዎቹ ሁሉ የጠበቀ ሠላትን ደንግጓል፡፡ ይህ ሙስሊሞች በሳምንት አንዴ የሚሰባሰቡበት ዕለት ነው፡፡በዚሁ ዕለት የጁምዐው ኢማም የሚያቀርብላቸውን ምክርና ተግሳጽ ያዳምጣሉ ከዚያም የጁምዐን ሠላት ይሰግዳሉ፡፡
የጁምዓ ዕለት ትሩፋት
የጁምዓ ዕለት ከሳምንቱ ቀናቶች ትልቁና የላቀ ክብር ያለው ዕለት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ከቀናቶች መካከል መርጦታል፡፡ ከተቀሩት ወቅቶች በበርካታ ልዩ ነገሮች አብልጦታል፡፡ ከነኚህም መካከል፡-
- አላህ (ሱ.ወ)፡ ይህን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ነጥሎ በዚህ ዕለት አልቆታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ) ከኛ በፊት ያሉትን የጁምዓን ዕለት አስቷቸዋል፡፡ ለአይሁዶች የቅዳሜን ዕለት፣ ለክርስቲያኖችም የእሁድን ዕለት አደረገላቸው፡፡ አላህ እኛን አመጣንና ለጁምዓ ዕለትም መራን፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 856)
- አደም የተፈጠረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ የምፅዓት ዕለትም የምትከሰተው በጁምዓ ዕለት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- #ፀሐይ ከምትወጣባቸው ቀናቶች በላጩ የጁምዐ ቀን ነው፡፡ኣደም የተፈጠረው በሱ ውስጥ ነው፡፡ ጀነት እንዲገባ የተደረገውም በሱ ውስጥ ነው፡፡ ከሷም እንዲወጣ የተደረገው በዚሁ ዕለት ውስጥ ነው፡፡ ሰዓቲቱም በጁምዓ ዕለት እንጂ አትከሰትም፡፡; ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 854)
ጁምዓ ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?
የጁምዓ ሠላት የሚከተለውን መገለጫ ባሟላ ሰው ላይ ግዴታ ነች፡፡
- ወንድ፡ በሴት ላይ ግዴታ አይደለም
- ለአቅመ አዳም የደረሰ፡ በባሪያና ባልደረሰ ሕፃን ላይ ግዴታ አይደለም፡፡
- ነዋሪ፡ በመንገደኛ፣ እንዲሁም ከከተማና ከመንደር ርቆ በዱር በሚኖር ሰው ላይ ግዴታ አይደለችም፡፡
የጁምዓ ሠላት አፈፃፀምና ድንጋጌዎች
- ከጀሙዓ ሠላት በፊት ገላን መታጠብ፤ኹጥባ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በጊዜ ወደ መስጂድ መምጣትና ጥሩ ልብስ መልበስ የተወደደ ነው፡፡
- ሙስሊሞች ጁምዓ በሚሰገድበት ትልቅ መስጂድ ወይም መስጂድ ጃሚዕ ውስጥ ይሰባሰቡና፣ ኢማሙ በመድረክ ላይ በመውጣት ፊቱን ወደ ሰጋጆቹ በማዞር በሁለት ክፍል የተከፈለ ኹጥባ/ዲስኩር ያደርግላቸዋል፡፡ በሁለቱ ኹጥባዎች መሐከል፣ ለመለያ ያክል ትንሽ ጊዜ በመቀመጥ እረፍት ያደርጋል፡፡ በኹጥባው ውስጥ፣ አላህን እንዲፈሩ ያስታውሳል፡፡ የቁርኣን አንቀጾችን እያጣቀሰ የተለያዩ ምክሮችና ተግሳጾችን ያስተላልፋል፡፡
- ሰጋጆቹ ኹጥባውን በጥሞና ማዳመጥ አለባቸው፡፡ መነጋገር ወይም ከኹጥባው ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በሚያደርጉ ነገሮች እራስን ማጥመድ ክልክል ነው፡፡ መስገጃ መነካካት ወይም አሸዋና አፈር እያነሱ መበተን እንኳን ክልክል ነው፡፡
- ከዚህ ቀጥሎ፣ ኢማሙ ኹጥባውን ሲጨርስ ከመድረኩ ይወርዳል፡፡ ኢቃም ይደረግና በቁርኣን ንባቡ ድምፁን ከፍ በማድረግ ሁለት ረክዐዎችን ያሰግዳቸዋል፡፡
- የጁምዓ ሠላት የተደነገገው የተወሰነ ያክል ሰው ለሚገኝበት ሁኔታ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የጁምዓ ሠላት ያመለጠው ወይም በሆነ ምክንያት ከጁምዓ ሠላት የቀረ ሰው፣ በሱ ምትክ መስገድ ያለበት ዙህርን ነው፡፡ ብቻውን የሚሰግደው ጁምዓ ተቀባይነት የለውም፡፡
- ከጁምዓ ሠላት የዘገየና ከኢማሙ ጋር ከረከዓ ያነሰውን ክፍል እንጂ ያልደረሰ ወይም ያላገኘ ሰው የሚሞላው ሠላት በዙህር መልክ ነው፡፡
- ጁምዓ ግዴታ የማይሆንባቸው፣ ሴቶችና መንገደኛ የመሳሰሉት በሙሉ ከሙስሊሞች ጋር በመሆን ቢሰግዱ ሠላታቸው ተቀባይነት ያገኛል፡፡ በዚህም የዙህር ሰላት ግዴታ ይወርድለታል፡፡
ከጁምዓ ለመቅረት የሚፈቀድለት ማን ነው?
ኢስላማዊው ድንጋጌ፣ የጁምዓ ሠላት ላይ መገኘቱ ግዴታ በሆነባቸው ሰዎች ላይ ሁሉ በቦታው መጣድ ግዴታ መሆኑን አጥብቆ አሳስቧል፡፡ በዓለማዊ ጉዳይ ከርሱ መዘናጋትን አጥብቆ አስጥንቅቋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- #እናንተ ያመናችሁ ሆይ በዐርብ ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት ኺዱ መሸጥንም ተዉ፤ ይሃችሁ የምታውቁ ብትኾኑ ለናንተ በጣም የተሻለ ነው፡፡›› ይላል፡፡ (አል ጁምዓ 9)
ያለ ህጋዊ ምክንያት ከርሱ የሚቀርን ሰው በልቦናው ላይ መናፍቅነት መታተምን አስጥንቅቋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹ያለ ምንም ምክንያት በመዘናጋት ሦስት ጁምዓን የተወ ሰው፣ አላህ (ሱ.ወ) በቀልቡ ላይ ያትምበታል፡፡›› ብለዋል፡፡ (አቡ ዳውድ 1052 አህመድ 15498) ‹‹በቀልቡ ላይ ያትምበታል›› ማለት ይጋርደዋል፣ ይሸፍነዋል፣ በውስጡ እንደ መናፍቃንና አመጸኞች ልብ መሃይምነትንና ድርቀትን ያበቅልበታል ማለት ነው፡፡
ከጁምዓ ለመቅረት የሚያስችል ምክንያት፡ ድንገተኛና ያልተለመደ፣ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም በኑሮ አለያም በጤና ላይ አስጊና አደገኛ ሁኔታ መከሰት ነው፡፡
በስራና ሃላፊነት ላይ ለመገኘት ሲባል ከጁምዓ መቅረት እንደ ህጋዊ ምክንያት ይታያልን?
በመሰረቱ፣ በስራና ሃላፊነት ላይ ለመገኘት ሲባል ከጁምዓ ሠላት መቅረት ህጋዊነት ወይም ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በዚህ ወቅት ስራችንን ትተን ለሠላት ዝግጁ እንድንሆን፣ #እናንተ ያመናችሁ ሆይ በዐርብ ቀን ለስግደት ጥሪ በተደረገ ጊዜ ወደ አላህ ማውሳት ኺዱ መሸጥንም ተዉ ይሃችሁ የምታውቁ ብትኾኑ ለናንተ በጣም የተሻለ ነው፡፡›› በማለት አዞናል፡ (አል ጁምዓ 9)
አላህ (ሱ.ወ)፡- ‹‹አላህንም የሚፈራ ሰው ለርሱ መውጫን ያደርግለታል፡፡ ከማያስበውም በኩል ሲሳይን ይሰጠዋል፡፡በአላህ ላይ የሚጠጋ ሰው እርሱ በቂው ነው፡፡›› ይላል፡፡ (አጠላቅ 2-3)
ስራ፣ ከጁምዓ ሠላት ለመቅረት ህጋዊ ምክንያት የሚሆነው ምን ጊዜ ነው?
ቀጥለው ከተጠቀሱት፣ ከሁለቱ በአንዱ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ተደጋጋሚና ዘውታሪ ስራ ከጁምዓ ሠላት ለመቅረት እንደ ምክንያት ሊቆጠር አይችልም፡፡
- እርሱ በቦታው ላይ በመኖሩና ከጁምዓ በመቅረቱ እንጂ ሊከሰት የማይችል ትልቅ ህዝባዊ ጥቅም ካለና ይህን ስራ እርሱ ከተወው ከፍተኛ ጉዳትና አደጋ የሚደርስ ከሆነ እርሱን ሊተካው የሚችል ማንም ከሌለ፡፡
- በድንገተኛ ክፍል የሚሰራ ዶክተር ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ቁስለኞችንና በሽተኞች የሚያክም ከሆነ
- ዘበኛና ፖሊስ የሰዎች ንብረት በሌቦችና በወሮበሎች እንዳይዘረፍ በመጠብቅና በመከላከል ላይ ከተሰማሩ
- በትላልቅ ኢንዳስትሪ ውስጥ የማሽኖችና መሳሪያዎችን ሂደት የሚከታተልና የሚቆጣር ቴክኒሻን ከሆነ ክትትል ለሴኮንዶች መቋረጥ የማይችል ከሆነ
- ስራው ብቸኛ የገቢ ምንጩ ከሆነ አስፈላጊ የዕለት ወጪዎቹን ምግቡን መጠጡንና ወሳኝ ጉዳዮችን ለራሱና ለቤተሰቦቹ የሚያስፈፅምበት ከዚያ ስራ ውጭ ምንም ከሌለው ሌላ ስራ እስከሚያገኝና ያለበት ችግር እስኪወገድለት ድረስ በዚያ ስራ ላይ በመቆየት ጁምዓ ሳይሰግድ ቢቀር ይፈቅድለታል፡፡ወይም ምግቡን መጠጡንና አስፈላጊ ጉዳዮችን ለራሱና ለቤተሰቦቹ የሚያስፈጽምበት እስከሚያገኝ ድረስ ይፈቀድለታል፡፡ ይሁን እንጂ ሌላ ስራና የገቢ ምንጭ ማስገኛ መንገድ የማፈላለግ ግዴታ አለበት፡፡
የመንገደኛ ሰላት
- መንገደኛ ከቦታ ቦታ በሚዘዋወርበት ወይም ከአራት ቀን ላነሰ ወቅት ጊዚያዊ ቆይታ በሚያደርግበት ስፍራ ሆኖ ባለ አራት ረከዓ ሰላቶቹን ሁለት ረከዓ አድርጎ መስገድ ይወደድለታል፡፡ዙህር ዐሱርና ዒሻን የአገሬ ነዋሪ የሆነ ኢማምን ተከትሎ ካልሰገደ በስተቀር በአራት አራት ረከዓ ምትክ ሁለት ሁለት አድርጎ ይሰግዳል፡፡ እንዲያ ከሆነ ግን ኢማሙን ሊከተልና እንደሱ አራት ረከዓ ሊሰግድ ይገባል፡፡
- ከፈጅር ሱና በስተቀር የተቀሩትን ተቀጥላ ሱና ሰላቶችን ቢተው ወይም ባይሰግድ ይችላል፡፡
- ዙህርና ዐስሩን በአንድነት መግሪብና ዒሻን በአንድነት አቆራኝቶ መስገድ ይችላል፡፡ በተለይ በሚዘዋወርበትና በሚሳፈርበት ወቅትና ሁናቴ ላይ ከሆነ የአላህን ህግ ገራገርነት እዝነትና ማጨናነቅ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የታማሚ ሰው ሰላት
አዕምሮውን እስካልሳተና እራሱን እስካወቀ ድረስ በፈለገው ሁናቴ ላይ ቢሆንም ሰላት በሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን እስልምና የሰዎችን ሁኔታና ያለባቸውን ጉዳይ ከግምት አስገብቷል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች አንዱ ህመም ነው፡፡
ይህን ለማብራራት ያክል፡
- መቆም የማይችል ወይም መቆም የሚያስቸግረው ወይም ለመቆም የሚያስችለው ፈውሱ የሚዘገይበት የሆነ ህመምተኛ ቆሞ መስገድ ይሻርለታል፡፡ እርሱ የሚሰግደው ቁጭ ብሎ ነው፡፡ቁጭ ማለትም ካልቻለ በጎኑ እንደተጋደመ ይሰግዳል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ ቁመህ ስገድ፡፡ ካልቻልክ ቁጭ ብለህ ስገድ፡፡ ካልቻልክ በጎንህ ተጋድመህ ስገድ አል ቡኻሪ 1066
- ማጎንበስ (ሩኩዕ) ወይም ሱጁድ ማድረግ ያልቻለ ሰው በሚችለው ልክ ምልክት በማድረግ ይሰግዳል፡፡
- በመሬት ላይ ቁጭ ማለት የሚቸገር ሰው በወንበርና በመሰል ነገሮች ላይ ቁጭ ብሎ መስገድ ይችላል፡፡
- በህመም ምክንያት ለእያንዳንዱ ሰላት መጥራራት ወይም ዉዱእ ማድረግ የሚቸገር ሰው ዙህራና ዐሱርን በአንድነት መግሪብና ዒሻን በአንድነት በማቆራኘት መስገድ ይችላል፡፡
- ሰላት ለመስገድ በህመም ምክንያት ውሃን መጠቀም የማይችል ሰው በአፈር ተየሙም ማድረግ ይችላል፡፡