ኢስላማዊ ሕግጋትን ተማር

አንድ ሙስሊም በሁሉም የህይወት ዘርፍ ዙሪያ ያሉ ኢስላማዊ ሕግጋትን ለማወቅ መጓጓት ይኖርበታል፡፡ የአምልኮ፣ የየዕለት ውሎና ግንኙነት ሥርዓቶችን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ካደረገ የዒባዳ ተግባሩን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ የሚያከናውን ይሆናል፡፡

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል «አላህ መልካም ነገር ላሰበለት ሰው የሃይማኖት ግንዛቤን ይሰጠዋል፡፡» (አል- ቡኻሪ፡71 ሙስሊም፡1037)

በተለይ ግዴታ የሆኑ እንደ ሰላትና ንፅህና አጠባበቅ (ጠሃራ) የመሳሰሉ ህግጋትን መማር አለበት፡፡ የተከለከሉ የምግብ ዓይነቶችን ማወቅም ይኖርበታል፡፡ ግዴታ ያልሆኑ ሆነው ሃይማኖቱ የሚያበረታታቸው አንዳንድ ነጥቦችን ማወቁም ተገቢ ነው፡፡

 የሸሪዓ ሕግጋት፡-

በሸሪዓ ሕግጋት መሠረት የአንድ ሰው ንግግርም ሆነ ተግባር ከአምሰት ማዕቀፎች ሊወጣ አይችልም፡፡

አልዋጂብ (ግዴታ) የግዴታ ተግባር ማለት አላህ ያዘዘው፣ ተግባሪው ምንዳ የሚያገኝበትና ከመተግበር የታቀበው ደግሞ የሚቀጣበት ተግባር ማለት ነው፡፡ አምስቱ ሶላቶችና የረመዷን ፆምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሐራም (ክልክል) ክልክል ተግባር ማለት አላህ የከለከለው፣ ከመተግበር የታቀበው ምንዳ የሚያገኝበትና የተገበረው ደግሞ የሚቀጣበት ተግባር ማለት ነው፡፡ ዝሙትና አስካሪ መጠጥን በምሳሌነት ማውሳት ይቻላል፡፡
አስሱና ወአል ሙስተሐብ (ተወዳጅ ተግባር) ይህ ደግሞ ይተገበር ዘንድ ኢስላም ያበረታታው፣ ተግባሪው ምንዳ የሚያገኝበትና ከመተግበር የታቀበው ደግሞ የማይቀጣበት ተግባር ማለት ነው፡፡ ሰዎች ጥሩ የሆነን ፈገግታ ማሳየት፣ ቀድሞ ሰላምታ ማቅረብና ከመንገድ ላይ ቆሻሻን ማስወገድ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
የሚጠላ (ከርሃ) ነገር ማለት የእስልምና ሃይማኖት አንዳይደረግ ያበረታታው ተግባር ማለት ሲሆን ይህን ተግባር ከማድረግ በመቆጠብ ምንዳ የሚገኝ ሲሆን መተግበሩ ግን ለቅጣት አይዳርግም፡፡ በሶላት ውስጥ ጣትን እያነቃነቁ መጫወት ከዚህ የተጠላ «መክሩህ» ተግባር ውሰጥ ሊመደብ ይችላል፡፡
የተፈቀደ (ሙባሕ) ማለት ደግሞ መተግበሩም ሆነ መቆጠቡ፥ ከልካይና አዛዥ ከሆነ የህግ (ሸሪዓ) መርህ ጋር ግንኙነት የሌለው ክንውን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ መሠረታዊ በሆነ መልኩ መብላት፣ መጠጣት፣ መናገር ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡