ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት

በኢስላም የጋብቻ መሰረት የሚጠነሰሰው አንድ ወንድ ከአንድ ሴት ጋር የሚዋደዱ፣ የሚተሳሰቡና የሚደጋገፉ ኾነው በሚመሰርቱት ቤተሰብ ነው፡፡ ከመሆኑም ጋር፣ ኢስላም ለወንዱ ከአንድ በላይ ሚስት እንዲያገባ ፈቅዶለታል፡፡ ይህ ደግሞ በቀደምት መለኮታዊ ድንጋጌዎችም ጭምር ሲሰራበት የነበረ ነው፡፡ ይህንን የፈቀደበት ዓላማ የግለሰቦችንና የማሕበረሰቡን ጥቅም ለመጠበቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ስርዓት የለሽና ደንብ አልባ አድርጎ አልተወውም፡፡ እንደውም ሴቶች እንዳይበደሉና እንዳይገፉ የሚያደርጉ መብታቸውን የሚያስከብሩ የሆኑ ቅድመ መስፈርቶችንና በደልን ከልካይ ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡

  1. ፍትሃዊነት

በቤት ወጪ፤ በመኖሪያ ቤትና በመሳሰሉት ግልጽ በሆኑ ቁሳዊ ጉዳዮች በሚስቶች መካከል ፍትሃዊ መሆን ግዴታ ነው፡፡ በመካከላቸው ፍትሃዊ መሆን የማይችል ከአንድ በላይ ማግባት በርሱ እርም ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ…ያዙ›› (አል ኒሳእ 3)

ፍትሃዊ አለመሆን እጅግ በጣም አደገኛና አስከፊ ወንጀል ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሁለት ሚስቶች ኖረውት ወደ አንደኛዋ ያዘነበለ ሰው የትንሳኤ ቀን በአንድ ጎኑ ተጣሞ ይቀሰቀሳል፡፡›› (አቡ ዳውድ 2133) የማይቻል ጉዳይ ነውና በልባዊ ፍቅር ፍትሃዊ መሆን ግዴታ አይደለም፡፡ በሚከተለው አንቀጽ ላይ የተጠቀሰውም ይኸው ነው፡፡ ‹‹በሴቶችም መካከል ምንም እንኳ ብትጓጉ (በፍቅር) ለማስተካከል አትችሉም፡፡›› (አል ኒሳእ 129)

 

  1. የሚስቶችን ወጪ መሸፈን መቻል

የሚስቶቹን ጠቅላላ ወጪ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ጋብቻ ሲፈፅም ይህ ጉዳይ የጋብቻ መስፈርት እንደሆነው ሁሉ በሁለተኛው ላይ ደግሞ የበለጠ ወሳኝ የሆነ መስፈርት ይሆናል፡፡

  1. ከአራት ሚስቶች በላይ አለመጨመር

በኢስላም ከአንድ በላይ የማግባት ገደቡ ይህ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ለናንተ ከሴቶች የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት፣ ሦስት ሦስትም፣ አራት አራትም አግቡ፡፡›› (አል ኒሳእ 3) ከአራት በላይ ሚስቶች ኖረውት ኢስላምን የተቀበለ ሰው፣ ከነርሱ መካከል አራቱን ብቻ መርጦ በማስቀረት ሌሎቹን ሊፈታ ይገባል፡፡

  1. ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለመጠበቅና ዝምድናን ላለማበላሸት አንዳንድ ሴቶችን በአንድነት በአንድ ጊዜ ማግባትም አይፈቀድም፡፡
  • አንዲትን ሴት፣ ከእህቷ ጋር በአንድ ወቅት ማግባት አይፈቀድም፡፡
  • አንዲትን ሴት፣ ከእናቷ እህት ከየሹሜዋ ጋር በአንድ ወቅት ማግባት አይፈቀድም፡፡
  • አንዲትን ሴት፣ ከአባቷ እህት፣ ከአክስቷ ጋር በአንድ ወቅት ማግባት አይፈቀድም፡፡

 ፍቺ

ኢስላም የጋብቻ ውል ዘላቂና ዘውታሪ መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ ጋብቻው ሁለቱም ወገኖች ሞት እስኪለያያቸው ድረስ የሚቆይ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጋብቻን የጠበቀ ውል ሲል ጠርቶታል፡፡ በኢስላም፣ ጋብቻን ለተወሰነ የጊዜ ገደብ በሚል መፈፀም ጨርሶ አይፈቀድም፡፡

ኢስላም በጋብቻ ላይ ሰዎችን ሲያበረታታ ድንጋጌው የወጣው በምድር ላይ ለሚኖር ሰብዓዊ ፍጡራን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ የራሳቸው የሆነ ልዩ መገለጫ ባህሪያትና ስጋዊ ፍላጎቶች አሏቸው፡፡ በመሆኑም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና መንገዶች ሁሉ ሲዘጋጉ፣ የማስተካከያና የማሻሻያ ዘዴዎች ሁሉ ፍሬ አልባ ሲሆኑ፣ ከዚህ ውል እራሳቸውን እንዴት ነፃ ሊያደርጉ ወይም ሊያላቅቁ እንደሚችሉ ስርዓትን ደንግጎላቸዋል፡፡ በዚህም ለወንዱም ሆነ ለሴቷ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚበጃቸውን መስመር ይዘረጋል፡፡ ብዙ ጊዜ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ፍቺን ብቸኛ የችግራቸው መፍትሄ የሚያደርጉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በቤተሰቡም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም በባልና ሚስት መሐከል የተመሰረተው ትዳር የተፈለገበትን ግብ ሊመታ ባለመቻሉ አብረው ከመቆየታቸው ይልቅ ፍቺ የተሻለ ይሆናል፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለመውጣት ሲባል ፍቺ የተፈቀደው ለዚህ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ሌላ የትዳር አጋር መቀየር አለባቸው፡፡ ምናልባት ሁላቸውም ከመጀመሪያው የትዳር አጋራቸው ያጡትን ከዚህኛው ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ቢለያዩም አላህ ሁሉንም በችሮታው ያብቃቃቸዋል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ጥበበኛ ነው፡፡›› (አል ኒሳእ 130)

ፍቺ እራሱን የቻለ ስርዓት አለው፡

  • ፍቺ በወንዱ እጅ እንጂ በሴቷ እጅ አይደለም፡፡
  • አንዲት ሴት ከባሏ ጋር መኖር ካልቻለች፣ እሱ ደግሞ ሊፈታት ፍቃደኛ ካልሆነ፣ ዳኛ ዘንድ በመሄድ እራሷን ማስፈታት ትችላለች፡፡ ዳኛውም ያቀረበችው ምክንያት አሳማኝ ሆኖ ካገኘው ሊያፋታት ይገባል፡፡
  • አንዲት ሴት ከተፈታች በኋላ፣ ሁለት ጊዜ መመለስ ትችላለች፡፡ ነገር ግን ለሦስተኛ ጊዜ ከፈታት ሌላ ትክክለኛ ጋብቻ ፈፅማ እስካልተፈታች ድረስ ወደ መጀመሪያው ትዳሯ መመለስ አትችልም፡፡