ስነ-ምግባር በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ

  1. ስነ-ምግባር፣ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ሰው ዘር ከተላኩበት ዓላማዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡

አላህ (ሱ.ወ) ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርአንን) በነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም… የኾነን መልክተኛ የላከ ነው፡፡›› (ጁምዓ 2 ) በአአንቀጹ ላይ፣ አላህ (ሱ.ወ) ለምእመናን ቁርኣንን እንዲያስተምራቸውና ከእኩይ ስነ-ምግባር እንዲያጠራቸው መልክተኛውን በመላኩ የዋለውን ውለታ አውስቷል፡፡ እራስን ማጥራት ወይም ተዝኪያ፡- ቀልብን በአላህ ከማጋራት እንዲሁም እንደ ቂምና ምቀኝነት ካሉ እኩይ ስነ-ምግባሮች፣ ንግግርና ተግባርን ደግሞ ከተወገዙ ልማዶች ማጥራትን ያካትታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አሻሚ ባልሆነ ግልጽ ቃላቸው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እነሆ እኔ የተላኩት መልካም ስነ-ምግባሮችን ላሟላ ዘንድ ነው፡፡›› (አል በይሃቂ 21301) ለነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) መላክ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ግላዊና ማህበራዊ ስነ-ምግባሮችን ማሳደግና ማረቅ ነው፡፡

  1. ስነ-ምግባር ዋነኛ የእምነት ክፍል ነው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በኢማኑ በላጩ አማኝ የትኛው ነው? ተብሎ በተጠየቁ ጊዜ፡ ‹‹በስነምግባሩ በላጫችሁ ነው ብለዋል፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1162 /አቡ ዳውድ 4682)

አላህ (ሱ.ወ) ኢማንን በጎ ነገር በሚል አውስቶታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹መልካም ስራ፣ ፊቶቻችሁን ወደ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም፤ ግን መልካም ስራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነብያትም ያመነ ሰው….(ስራ) ነው፡፡›› (አል በቀራ 177) መልካም ነገር (ቢር)፡ በጎ ነገሮችን ከስነ-ምግባር፣ ከንግግርና ከተግባር ጋር የሚያቆራኝ ጥቅላዊ ስያሜ ወይም መጠሪያ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹መልካም ነገር ጥሩ ስነ ምግባር ነው፡፡›› ያሉት ለዚህ ነው፡፡ (ሙስሊም 2553) ይህ ጉዳይ በይበልጥ ግልጽ የሚሆነው በሚከተለው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር ውስጥ ነው፡- ‹‹ኢማን ከስልሳ ሦስት እስከ ስልሳ ዘጠኝ ደረጃዎች አሉት፤ ከፍተኛው ላኢላሃኢለላህ የሚለው ቃል ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ ከመንገድ ላይ ቆሻሻን ማስወገድ ነው፤ ህፍረትም ከኢማን ክፍል ነው፡፡›› (ሙስሊም 35)

  1. ስነ-ምግባር ከእያንዳንዱ የአምልኮ ዘርፍ ጋር የተሳሰረና የተቆራኘ ነው አላህ (ሱ.ወ) አንድንም የአምልኮ ዓይነት ሲያዝ ስነምግባራዊ ዓላማውን ወይም በግለሰብና በማህበረሰብ ላይ የሚያስገኘውን ለውጥ ወይንም የሚጥለውን ፋና አብሮ ያሳስባል ወይም ይገልጻል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፤ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሠላት፡ ‹‹ሠላትንም (ደንቡን ጠብቀህ) ስገድ፤ ሠላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡›› (አል አንከቡት 45) ዘካ፡ ‹‹ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፡፡›› (አል ተውባ 103) በመሰረቱ፣ ዘካ ለሰዎች በጎ መዋል፣ እነርሱን መደገፍና መርዳት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ፣ የሰጪውን ክፍል ነፍስ ከመጥፎ ስነ-ምግባሮች ያጠራለታል፡፡ ጾም፡ ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡›› (አል በቀራ183) የጾም ዓላማው፣ ትዕዛዙን በመፈፀምና የተከለከለውን በመራቅ አላህን መፍራት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የውሸት ንግግርና በርሱ መስራትን ያልተወ ሰው፣ ምግብና መጠጡን ከመተው አላህ ጉዳይ የለውም፡፡›› ብለው የተናገሩት ለዚህ ነው፡፡ (አል ቡኻሪ 1804) መጾሙ ከሰዎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ስነ-ምግባራዊ ለውጥ ያላመጣለት ሰው በርሱ ላይ የጾም ዓላማ አልተረጋገጠበትም፡፡

  1. አላህ (ሱ.ወ) ለጥሩ ስነ-ምግባር ያዘጋጀው የላቀ ደረጃና ከባድ ምንዳ በዚህ ዙሪያ በርካታ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች ተላልፈዋል፡፡ ከነሱም መካከል፡
  • በትንሳኤ ቀን በሚዛን ላይ እጅግ በጣም ክብደት ከሚያነሱ ወይም ከሚደፉ መልካም ስራዎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በሚዛን ላይ ተደርጎ ከጥሩ ስነ- ምግባር የበለጠ የሚከብድ ነገር የለም፤ የጥሩ ስነ-ምግባር ባለቤት የጾመኛና የሰጋጅ ደረጃን በርሱ ይደርሳል፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2003)
  • ጀነት ለመግባት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የሰው ልጅን በብዛት ጀነት የሚያስገባው፣ አላህን መፍራትና ሰናይ ስነ-ምግባር ነው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2004 /ኢብኒ ማጃህ 4246)
  • የጥሩ ስነ ምግባር ባለቤት የትንሳኤ ቀን ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እጅግ የቀረበ ይሆናል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በትንሳኤው ቀን እኔ ዘንድ እጅግ ተወዳጃችሁና በስፍራም ለኔ የበለጠ ቅርባችሁ፣ ከናንተ መካከል በስነ ምግባሩ በላጫችሁ ነው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2018)
  • በጀነት ከፍተኛውን ማዕረግ እንደሚያገኝ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዋስትና ሰጥተውታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እውነቱ እርሱ ዘንድ ቢሆንም ሙግትን ለተወ ሰው፣ በጀነት ዳርቻ የሆነ ቤትን፣ ለቀልድ ቢሆንም ውሸትን ለተወ ሰው ደግሞ በጀነት መሐል የሆነ ቤትን፤ ስነ-ምግባሩ ላማረ ሰው ደግሞ በጀነት የላይኛው ክፍል የሚገኝ ቤትን ዋስትና እሰጠዋለሁ፡፡›› (አቡ ዳውድ 4800)

 

በኢስላም ውስጥ የስነ ምግባር ልዩ መገለጫዎች

በኢስላም፣ ስነ ምግባር በርካታ የሆኑ ልዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ ያ ደግሞ ይህን ታላቅ ሃይማኖት ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ነው፡

  1. የላቀ ስነ-ምግባርን ማሳየት በሰው ልጅ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅን ሲፈጥር በተለያየ ቅርጽ፣ ቀለምና ቋንቋ ላይ አድርጎ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአላህ ሚዛን ሁሉም እኩል ናቸው፡፡ በኢማናቸው፣ አላህን በመፍራታቸውና በጥሩነታቸው ልክ እንጂ፣ አንዳቸው በሌላኛው ላይ ምንም ዓይነት ብልጫ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! እኛ ከወንድና ከሴት ፈጠርናችሁ፤ እንድትተዋወቁም ጎሳዎችና ነገዶች አደረግናችሁ፤ አላህ ዘንድ በላጫችሁ በጣም አላህን ፈሪያችሁ ነው፡፡›› (አል ሑጁራት 13) መልካም ስነ ምግባር፣ አንድ ሙስሊም ከማንኛውም ሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ልዩ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም፣ በሃብታምና በድሃ፤ ደረጃው በተለቀና ባነሰ፣ በጥቁርና በነጭ፣ በዐረቡና ዐጀሙ መካከል ልዩነት ስለማይፈጥር ነው፡፡

ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የሚኖር ስነምግባር አላህ (ሱ.ወ) ስነ ምግባራችን ከሁሉም ጋር ያማረ እንዲሆን አዞናል፡፡ ፍትሃዊነት፣ በጎነት፣ እዝነት፣ ትክክለኛ ሙስሊም ከሙስሊሞችም ሆነ ከካሃዲያን ጋር በሚኖረው ግንኙነት የሚታወቅበት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሙስሊም ይህ መልካም ስነ ምግባሩ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ወደዚህ ታላቅ ሃይማኖት የሚጠራበት ዋነኛ መንገዱ እንዲሆን ይጥራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ከነዚያ በሃይማኖት ካለተጋደሏችሁ ከአገሮቻችሁም ካለወጡዋችሁ (ከሃዲዎች) መልካም ብትውሉላቸውና ወደነርሱ ብታስተካክሉ አላህ አይከለክላችሁም፤ አላህ ትክክለኞቹን ይወዳልና፡፡›› (አል ሙምተሒና 8) አላህ የከለከለው ከካሃዲያን ጋር መጎዳኘትንና እነርሱ ያሉበትን ክህደትና ማጋራትን መውደድ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ የሚከለክላችሁ ከነዚያ በሃይማኖት ከተጋደሉዋችሁ ከቤቶቻችሁም ካወጡዋችሁ እናንተንም በማውጣት ላይ ከረዱት (ከሃዲዎች) እንዳትወዳጁዋቸው ብቻ ነው፤ ወዳጅ የሚያደርጓቸውም ሰዎች እነዚያ እነርሱ በዳዮቹ ናቸው፡፡›› (አል ሙምተሒና 9)

 

  1. የላቁ ስነ ምግባሮች በሰዎች ብቻ የተገደቡ አይደሉም፡፡

ስነ ምግባር ከእንሰሳት ጋር

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ አንዲት ሴት ድመትን አስራ በረሃብ በመግደሏ ምክንያት ጀሃነም እንደገባች, ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አንድ ሰው የተጠማ ውሻን በማጠጣቱ ምክንያት አላህ ወንጀሎቹን እንደማረው ነግረውናል:: ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዲት ሴት ባሰረቻት ድመት ምክንያት እሳት ገባች፤ ወይ አላበላቻት ወይ ከመሬት ነፍሳቶች እንድትበላ አልተወቻት፡፡›› (አል ቡኻሪ 3140/ ሙስሊም 2619) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አንድ ሰውዬ በመንገድ እየተጓዘ ሳለ ውሃ ጥም ጠናበት፤ የጉድጓድ ውሃ አገኘ፤ ወደ ጉድጓዱ ወርዶ ጠጣ፤ ከዚያም ሲወጣ ከመጠማቱ የተነሳ አፈር የሚልስ፣ ምላሱን ጎልጉሎ የሚያለከልክ ውሻ አገኘ፤ እንዲህም አለ፡- «ይህ ውሻ ልክ እኔ ተጠምቼ እንደነበርኩት ዓይነት ተጠምቷል» አለና በድጋሚ ወደ ጉርጓዱ ወርዶ፣ በጫማው ውሃ ሞልቶ፣ በአፉ ነክሶ ይዞ በመውጣት ውሻውን አጠጣው፤ በዚህም አላህ ስራውን ወዶለት ወንጀሉን ማረው፡፡›› ብለው ተናገሩ፡፡ ሠሓቦቹም፣ «የአላህ መልክተኛ ሆይ! እኮ እኛ በነዚህ እንሰሳትም ምንዳ እናገኛለን?» በማለት ጠየቁ፤ እሳቸውም፡ ‹‹ነፍስ ባለው ነገር ሁሉ ውስጥ ምንዳ አለ፡፡›› አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 5663 / ሙስሊም 2244)

 

ስነ ምግባርና የአካባቢ ጥበቃ

ኢስላም፣ በመመራመርና ስልጣኔን በማሳደግ፣ በመስራት፣ በማልማት፣ ምድርን እንድናስውባት አዞናል፡፡ ይህም፣ ምድር ላይ ያለውን ጸጋ በመጠበቅ እንዲሁም ከሚያበላሹትና ከሚያባክኑት ነገሮች በመካለከልና በሚገባው ስፍራ ላይ ግልጋሎት እንዲሰጥ በማድረግ ይረጋገጣል፡፡ የአካባቢ ብልሽትና ብክለት ሰዎችን፣ እንሰሳትንም ሆነ እጽዋትን መጉዳቱ ሁሉም በአንድ ዓይን የሚታይ ነው፡፡ ጉዳቱ በየትኛውም አካል ላይ ቢሆን፣

ኢስላም አጥብቆ የሚያወግዘውና የሚጠላው ተግባር ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ ማበላሸትን አይወድም፡፡ እንዲህም ይላል፡- ‹‹አላህም ማበላሸትን አይወድም፡፡›› (አል በቀራ 205) ይህ ኢስላማዊ እሴት፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሙስሊሞች በአስቸጋሪና አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ቢሆኑ፣ መልካምን እንዲሰሩና ምድርን ያለሙ ዘንድ ትእዛዝን እንዲያስተላልፉ አድርጓል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዳችሁ በእጅ ችግኝ ይዞ ሰዓቲቷ ብትከሰት፤ ሳትከሰት ሊተክላት የቻለ ሁሉ ይትከላት፡፡›› (አህመድ 12981)

  1. መልካም ስነ ምግባር በሕይወት ዘርፎች ሁሉ

በቤተሰብ ውስጥ፡

ኢስላም፣ በአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል ስነ ምግባር ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ ‹‹በላጫችሁ ለቤተሰቡ መልካም የሆነው ነው፤ እኔ ለቤተሰቦቼ መልካማችሁ ነኝ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 3895)

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰው ዘር በጠቅላላ ምርጡ ሰው ናቸው፡፡ እንዲህ ከመሆናቸውም ጋር በትንሽ በትልቁ፣ በቤት ውስጥ ጉዳይ ባለቤታቸውን ይረዱና ያግዙ ነበር፡፡ ባለቤታቸው፣ እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ) የሚከተለውን ብለዋል፡- ‹‹እሳቸው በቤተሰባቸው ጉዳይ የተጠመዱ ነበሩ፡፡›› (አል ቡኻሪ 5048) ይህ በቤት ውስጥ በሚሰሩት ስራ ፤ በቤት ውስጥ በሚሰሩት ስራ ከቤተሰባቸው ጋር ይሳተፉ ነበር ማለት ነው፡፡
  • ከሚስቶቻቸው ጋር ይቃለዱና ይጫወቱም ነበር፤ ባለቤታቸው እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡- «በአንድ ወቅት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር በሆነ ጉዟቸው ላይ አብሪያቸው ተጉዤ ነበር፤ በወቅቱ እኔ ልጅ ነበርኩ፡፡ አልወፈርኩም አልከበድም ነበር፤ ነብዩ ለሰዎች እንዲህ አሉ፡ ‹‹ቅደሙን ከፊት ከፊት ሂዱ፡፡›› ሰዎቹም ከፊት ከፊት ሄዱ፡፡ ከዚያም ‹‹ነይ እስኪ እንሽቀዳደም›› አሉኝ ተሽቀዳደምንና እኔ ቀደምኳቸው፤ ዝም አሉኝ፤ ከወፈርኩ፣ ክብደት ከጨመርኩ እና ተሸቀዳድመን እንደነበረ ከረሳሁት በኋላ አሁንም በሆነ አጋጣሚ በአንድ ጉዟቸው ላይ አብሬያቸው ተጓዝኩ፡፡ አብረውን የነበሩ ሰዎችን ‹‹ወደፊት ቅደሙ›› አሏቸውና ሰዎቹም ከፊት ከፊታችን ተጓዙ፤ እሳቸውም ‹‹እስኪ ነይ እንሽቀዳደም›› አሉኝ፤ ተሸቀዳደምንና ቀደሙኝ፤ ከዚያም እየሳቁ፣ ‹‹ይህች የዚያች መካሻ ናት፡፡›› አሉኝ « (አሕመድ 26277)

በንግድ ውስጥ፡

ምናልባት የሰው ልጅ ለገንዘብ ካለው ፍቅር የተነሳ ድንበር በማለፍ እርም የተደረጉ ነገሮች ውስጥ ሊዘፈቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ኢስላም ይህን የገንዘብ ውዴታውን በላቀ ስነ ምግባር ሥርዓት ማስያዝ እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል፡፡ ለምሳሌ፡

  • ኢስላም በሚዛን ድንበር ማለፍንና መበደልን ይከለክላል፡፡ ይህን የሚሠራ ሰውንም ብርቱ የሆነ ቅጣት እንደሚጠብቀው ይነግራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለሰላቢዎች ወዮላቸው፤ ለነዚያ ከሰዎች ባስሰፈሩ ጊዜ የሚያስሞሉ፤ ለነሱም (ለሰዎቹ) በሰፈሩ ወይም በመዘኑላቸው ጊዜ የሚያጎድሉ (ለኾኑት)›› (አል ሙጠፊፊን 1-3)
  • በግብይት ላይ ገራገር መሆንን ያበረታታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሲሸጥ፤ ሲገዛና፤ ሲፋረድ ገር የሆነን ሰው አላህ ይዘንለት፡፡›› (አል ቡኻሪ 1970)

በሥራ ውስጥ፡

ኢስላም፣ የፈጠራ ባለቤቶችን በርካታ ስነ ምግባሮችና ስርዓቶችን ሊላበሱ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡

  • ሥራን በብቃትና በጥራት መስራትን፤ ምርትን በሚያምር ሁኔታ ማምረትን ያዛል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ)፣ አንዳችሁ በሚሠራ ጊዜ ሥራውን በብቃትና በጥራት እንዲሰራው ይፈልጋል፡፡›› (አቡ ያዕላ 4386/ አል በይሃቂ ፊ ሺዓቢል ኢማን 5313)
  • ከሰዎች ጋር የተደረገን ስምምነትና ውል መጠበቅ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ‹‹የመናፍቅነት መገለጫ ምልክቶች ሦስት ናቸው፤›› ካሉ በኋላ ከነሱ መካከል ‹‹ቃል ከገባ በኀዋላ ቃሉን ማፍረስ›› በማለት ጠቅሰዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 33)
  1. የላቀ ስነ ምግባር በማንኛውም ሁኔታ አስፈላጊ ስለመሆኑ

በኢስላም፣ ስነ ምግባር እዚህ ውስጥ አይገባም የሚባልለት ነገር የለም፡፡ ሙስሊም፣ ጦርነትን ጨምሮ እጅግ አዳጋች በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ የአላህን ሕግ በመፈፀም ረገድ የመልካም ስነ ምግባርን መርሆዎች ይከተላል፡፡ የአንድ ነገር ዓላማና መድረሻ መልካምነት የመዳረሻ መንገዶቹን መጥፎ ገጽታ አያጸዳውም፤ ስህተትነቱንና ጥመቱንም አይሸፍነውም፡፡ ስለሆነም ኢስላም ሙስሊሙን፣ ከጠላት ጋር በሚኖረው ግንኙነት እና በጦርነት ወቅት በሚኖረው ሁኔታ ላይ ሳይቀር፣ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የሚገዛውና በስርዓት የሚመራው የሆነ ጠቅላይ መመሪያ አስቀምጧል፡፡ ይህ መመሪያ፣ የአንድ ሙስሊም የሕይወት ገጠመኝ፣ የንዴትና የጭፍንነት ግላዊ ስሜቶች ተገዢና እንዲሁም ለቂም ለችክተኝነትና ለማን አለበኝነት መፈንጪያ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡

 

በጦርነት ላይ ያለው የኢስላም ስነ ምግባራዊ መመሪያ

  1. ኢስላም ከጠላት ጋር ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት እንዲኖር አዟል፤ በደልንና በነርሱ ላይ ድንበር ማለፍን ከልክሏል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፤ አስተካክሉ፤ እርሱ (ማስተካከል)ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡›› (አል ማኢዳ 8) ለጠላቶቻችሁ ያላችሁ ጥላቻ ድንበር እንድታልፉና በደል እንድትፈጽሙ ሊያደርጋችሁ አይገባም ማለት ነው፡፡ ይልቁንም በንግግራችሁም ሆነ በተግባራችሁ ፍትሃዊ ሁኑ እያለ ነው፡፡
  2. ኢስላም፣ ከጠላት ጋር በሚደረግ ውልና ስምምነት መክዳትንና ማታለልን ይከለክላል፡፡ ጠላትንም ቢሆን መክዳትና ማታለል ክልክል ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ ከዳተኞችን አይወድምና፡፡›› (አል አንፋል 58)
  3. ኢስላም የጠላትን ሬሳ ማንገላታትና መቆራረጥን ይከለክላል፡፡ የሙታንን ገላ መቆራረጥ ሐራም ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-‹‹ሬሳን አትቆራርጡ›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 1731)
  4. በጦርነት ላይ የማይሳተፉ አካባቢን በማበላሸት የማይታወቁ የሆኑ ሰላማዊ ነዋሪዎችን መግደል ይከለክላል ታላቁ ሠሐቢይ፣ የሙስሊሞች ኸሊፋ፣ አቡበከር(ረ.ዐ)፣ ኡሳማ ቢን ዘይድን(ረ.ዐ) ወደ ሻም ሀገር የጦር መሪ አድርገው በላኩ ጊዜ፡- ‹‹ታዳጊ ሕፃንን፣ ያረጀ ሽማግሌንም፣ ሴትንም አትግደሉ፡፡ የተምር ዛፍን አትቁረጡ አታቃጥሉም፡፡ የሚያፈራ ዛፍንም አትቁረጡ፡፡ ልትመገቡ ካልሆነ በስተቀር በበቀል የሕዝቦችን ፍየሎች፣ ላምና ግመሎች አትረዱ፡፡ እራሳቸውን ለአምልኮ ያገለሉ፣ በገዳማት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ያጋጥሟችኋል፤ እራሳቸውን አሳልፈው በሰጡለት ነገር ላይ ተዋቸው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ኢብኑ ዓሳኪር 2/ 50)