ሐጅ

የመካ እና የመስጂዱል ሐራም ትሩፋት

መስጂደል ሐራም የሚገኘው በዐረብያ ደሴት፣ በስተምዕራብ በኩል፣ በቅድሲቷ የመካ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በኢስላም፣ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ ትሩፋት ያሉት ሲሆን ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. በውስጡ የተከበረው ካዕባ የሚገኝ መሆኑ

ካዕባ፡ ማለት ወደ ሬክታንግልነት ያደላ ግንባታ ሲሆን በቅድሲቷ መካ ከተማ ውስጥ በመስጂደል ሐራም መሐል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ መካ፣ ሙስሊሞች አላህ ያዘዛቸውን ሠላት ሲሰግዱና ሌሎችንም አምልኮዎች ሲፈፅሙ የሚቅጣጩባት ወይም ፊታቸውን የሚያዞሩባት የአምልኮ አቅጣጫ ነች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአላህ ትዕዛዝ የገነቧት ነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸው ነብዩ ኢስማኢል ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ እድሳት ተደርጎላታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ኢብራሂምና ኢስማዒልም ጌታችን ሆይ ከኛ ተቀበል አንተ ሰሚውና ዐዋቂው አንተ ነህና የሚሉ ሲኾኑ ከቤቱ መሰረቶቹን ከፍ ባደረጉ ጊዜ (አሰታውስ)፡፡›› (አል በቀራ 127) ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.ዐ.ወ) የቅድሲቷ መካ ነዋሪዎች የነበሩ ጎሳዎች አፍርሰው በድጋሚ በሰሯት ጊዜ ጥቁሩን ድንጋይ ወደ ቦታው በመመለሱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ .

  1. በምድር ላይ የመጀመሪያው መስጂድ መሆኑ

ታላቁ ሠሓብይ አቡ ዘር አልጊፋሪ(ረ.ዐ)፣ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ)፣ «የአላህ መልክተኛ ሆይ በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው መስጂድ የቱ ነው?» ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ፡ ‹‹መስጂደል ሐራም ነው፡፡›› በማለት መልሰውለታል፡፡ ከዚየስ? ሲላቸው፣ ‹‹መስጂደል አቅሷ ነው፡፡›› ብለውታል፡፡ «በመካከላቸው ስንት ዓመት አለ?» ሲላቸው ደግሞ፡ ‹‹አርባ ዓመት›› ካሉት በኋላ፣ ‹‹የትም ቢሆን ሠላት ከደረሰብህ ስገድ በሱ ውስጥ ትሩፋቱ አለና›› አሉት፡፡ (አል ቡኻሪ 3186/ ሙስሊም 520)

  1. በሱ ውስጥ የሚሰገድ ሠላት ምንዳው እጥፍ ድርብ መሆኑ

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በዚህ መስጂዴ (በመዲና መስጂድ ውስጥ) የሚሰገድ ሠላት፣ ከመስጂደል ሐራም ውጭ ባሉ መስጂዶች ከሚሰገዱ አንድ ሺህ ሠላቶች ይበልጣል፡፡ በመስጂደል ሐራም ውስጥ የሚሰገድ ሠላት ደግሞ ከርሱ ውጭ ባሉ መስጂዶች ከሚሰገድ አንድ መቶ ሺህ ሠላቶች ይበልጣል፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 1406/ አህመድ 14694)

  1. አላህና መልክተኛው የከለሏት መሆኗ

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የታዘዝኩት የዚህችን አገር ጌታ ያንን ክልል ያደረጋትን እንድገዛ ብቻ ነው፡፡ ነገሩም ሁሉ የርሱ ነው፡፡ ከሙስሊሞችም እንድኾን ታዝዣለሁ (በል)፡፡›› (አል ነምል 91) አላህ (ሱ.ወ)፣ መካን ሰዎች በውስጧ ደም እንዳይፋሰሱባት፣ ማንንም እንዳይበድሉባት፣ አደን እንዳያድኑባት፣ ዛፎቿንና ተክሎቿን እንዳይቆርጡ እርም አድርጓታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ) መካን እርም አድርጓታል፤ እርም ያደረጓት ሰዎች አይደሉም ፤ እናም በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ሰው በውስጧ ደም ሊያፈስም ሆነ ዛፎቿን ሊቆርጥ አይፈቀድለትም፡፡›› (አል ቡኻሪ 104/ ሙስሊም 1354) ).

  1. አላህና መልክተኛው ዘንድ ከሀገራት ሁሉ በጣም ተወዳጅ መሆኗ

ከሠሐቦች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፡- «ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) በመጓጓዣቸው ላይ ሆነው በሃዝዋ መንደር (በመካ ውስጥ ያለች መንደር ናት) እንዲህ እያሉ ተመልክቻቸዋለሁ፡ ‹‹ወላሂ አንቺ በላጭ የአላህ መሬት ነሽ፤ አላህ ዘንድም ተወዳጇ የአላህ መሬት ነሽ፡፡ ካንቺ እንድወጣ ባልደረግ ኖሮ አልወጣም ነበር፡፡››» (አል ቲርሚዚ 3925 / አል ነሳኢ ፊል ኩብራ 4252)

  1. አላህ (ሱ.ወ)፣ በይተል ሐራምን መጎብኘት በቻለ ሰው ላይ መጎብኘትን ግዴታ ያደረገ መሆኑ

ነብዩ ኢብራሂም(ዐ.ሰ)፣ ሰዎች ሐጅ እንዲያደርጉ ተጣርቷል፡፡ ሰዎችም ከየስፍራው ወደተከበረው የአላህ ቤት መጡ፡፡ ነብያት ወደረሱ በመምጣት ጅሐ እንዳደረጉ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ነግረውናል፡፡ አላህም ኢብራሂምን በዚህ አዟቸው እንደነበረ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- ‹‹(አልነውም) በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትዕዛዝ ጥራ፤ እግረኞች፣ ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ኾነው ይመጡሃልና፡፡›› (አል ሐጅ 27)

 የሐጅ ትርጉም

ሐጅ ማለት የተወሰኑ አምልኮት ተግባራትን ለመፈፀም ወደተከበረው አላህን ማምለኪያ ቤት-በይቱላሂል ሐራም(ካዕባ) በማሰብ መጓዝ ነው፡፡ ከዚያም፣ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተላለፉ ተግባሮችና ንግግሮችን ማከናወን ነው፡፡ ኢሕራም መታጠቅ፤ በካዕባ ዙሪያ ሰባት ጊዜ መዞር፤ በሠፋና በመርዋ ኮረብታዎች መሐል ሰባት ጊዜ መመላለስ፤ በዐረፋ መቆም፤ በሚና ጠጠሮችን መወርወርና ሌሎችንም ተግባራት መፈፀምን ያጠቃልላል፡፡

ሐጅ በውስጡ ለአላህ ባሮች ከበባድ ጥቅሞችን ይዟል፡፡ ከነኚህም ጥቀሞች መካከል፤ የአላህን አሃዳዊነት በይፋ ማሳየት፣ ሐጃጆች የሚጎናጸፉት ላቅ ያለ ምህረት፣ የሙስሊሞች መተዋወቅ፣ የሃይማኖት ድንጋጌዎችን በተግባር መማርና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የሐጅ ወቅት፡ የሐጅ ተግባራት የሚፈፀሙት ከዙልሒጃ ወር ስምንተኛው ቀን አንስቶ እስከ አስራ ሶስተኛው ቀን ድረስ ነው፡፡ ዙልሒጃ፣ በጨረቃ ቀመር (ኢስላማዊ አቆጣጠር) መሰረት አስራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡

ሐጅ ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?

ሐጅ ግዴታ የሚሆነው፣ በአንድ ለኃላፊነት በደረሰ ሙስሊም ላይ ሲሆን እርሱም የሚችል ከሆነ ነው፡፡

የመቻል ትርጉም

መቻል ስንል፡ ሕጋዊና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ወደ በይተል ሐራም መድረስ መቻልና የሐጅን ሥርዓት ከተለመደው በጉዞ ላይ ከሚያጋጥም መንገላታት ውጭ ምንም ዓይነት መንገላታትም ሆነ ችግር ሳይገጥመው መፈፀም መቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ለነፍሱና ለንብረቱ ዋስትና የሚኖረው መሆን፤ ለሐጅ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟት ወጪ የሚያደርገው ገንዘብ፣ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ከሚሸፍንበትና በርሱ ስር ከሚተዳደሩ ሰዎች ወጪ የተረፈ ሲሆን ነው፡፡

አንድ ሙስሊም ሐጅ ማድረግ የመቻል መገለጫዎች፡

  1. በራሱ ሐጅ ማድረግ መቻሉ፡ አንድ ሙስሊም፣ በቂ ገንዘብ ያለው ከሆነና ከተለመደው የጉዞ እንግልት በተጨማሪ ምንም ዓይነት እንግልት ሳይደርስበት በራሱ ወደ በይተል ሐራም መድረስ ከቻለ የግዴታን ሐጅ በራሱ የማድረግ ግዳጅ አለበት፡፡
  2. በራሱ ሳይሆን በሌላ ሰው ሐጅን ማስፈፀም የሚችል መሆኑ፡ ዕድሜው የገፋ አዛውንት በመሆኑ ወይም ህመምተኛ በመሆኑ ምክንያት ሐጅ ማድረግ የማይችል፣ ነገር ግን እርሱን ወክሎ ሐጅ ሊያደርግለት የሚችልን ሰው የሚያገኝ ከሆነና እርሱን ወክሎ ሐጅ እንዲያደርግለት ወጪውን መሸፈን ከቻለ፣ የወኪሉን ወጭ ሸፍኖ ሐጅ የማስደረግ ግዴታ አለበት፡፡
  3. በራሱም ሆነ በሌላ ሰው አማካይነት ሐጅ ማድረግ የማይችል፡ ይህ ዓይነቱ ሰው የማይችል እስከሆነ ድረስ ሐጅ የማድረግ ግዴታ የለበትም፡፡

ፍላጎቱን ከሚያሟላበትና የቤተሰቡን ወጪ ከሚሸፍንበት የሚተርፈው ሐጅ ሊያደርግበት የሚችል ምንም ዓይነት ገንዘብ የሌለው ሰው በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡

ሐጅ ማድረግ የሚያስችለው ገንዘብ ለማግኘት ገንዘብ የማሰባሰብ ግዴታ የለበትም፡፡ በቻለ ጊዜ ግን ሐጅ ግዳጅ ይሆንበታል፡፡

 አንዲት ሴት ሐጅ ለማድረግ መሕረም (የቅርብ ተጠሪዋ) አብሯት መኖሩ መስፈርት ነው፡፡

በሴት ላይ ሐጅ ግዴታ ሊሆን የሚችለው መሕረሟ (የቅርብ ተጠሪዋ) ካለ ብቻ ነው፡፡ መሕረሟ አብሯት ከሌለ በሴት ልጅ ላይ ሐጅ ግዴታ አይሆንም፡፡ ለአንዲት ሴት መሕረም የሚሆኗት ባለቤቷ ወይም እርሷን ፈፅሞ ማግባት የማይፈቀድላቸው፣ እንደ አባት፣አያት፣ልጅ፣የልጅ ልጅ፣ ወንድሞችና የወንድም ልጆች፣ አጎቶች፣ ….. (ገጽ 200 ተመልከቱ) ናቸው፡፡

በራሱዋ የምትተማመን ሁና ያለሙህሪም ሐጅ ካደረገች ሐጁዋ ትክክል ነው፤ ምንዳም ያስገኛታል፡፡

ሐጅ ለማድረግ የሚያበቃህ የሆነ በቂ ገንዘብና አካላዊ ብቃት
አዎን
በራስህ ሐጅ ልታከናውን ግዴታ ይሆንብሃል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ሐጅ ለማድረግ በቂ ገንዘብ አለህ ነገር ግን ይድናል ተብሎ በማይከጀል ሕመም ምክንያት ሐጅ ለማድረግ የሚያስችል የአካል ብቃት የለህም፣አለያም በጣም ሸምግለሃል፡፡
አዎን
በዚህን ጊዜ አንተን ወክሎ ሐጅ ለሚያደርግ ሰው ወጪውን የመሸፈን ግዴታ አለብህ፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ከመሰረታዊ ፍላጎቶችህና በአንተ ስር ከሚተዳደሩ ሰዎች መሰረታዊ ወጪ የሚተርፍ የሆነና ሐጅ ለማድረግ የሚያስችልህ በቂ ገንዘብ ከሌለህ ሐጅ የማድረግ ግዳጅ የለብህም፡፡ ሐጅ ለማድረግ ገንዘብ ማስባሰብም አይጠበቅብህም፡፡

የሐጅ ትሩፋቶች

ሐጅ የሚያስገኘውን ትሩፋቶችና መልካም ነገሮች በማስመልከት ብዙ ተነግሯል፡፡ ከዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ሐጅ ከሥራዎች ሁሉ በላጭ ሥራ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሥራዎች በላጩ ሥራ የትኛው ነው? ተብለው በተጠየቁ ጊዜ፡ ‹‹በአላህና በመልክተኛው ማመን ነው›› አሉ፡፡ ከዚያስ? ተባሉ ‹‹በአላህ መንገድ ላይ መታገል›› አሉ፡፡ በድጋሚ ከዚያስ? ተባሉ ‹‹ተቀባይነት ያገኘ ሐጅ›› ብለው መለሱ (አል ቡኻሪ 1447 / ሙስሊም 83)
  2. ሐጅ ሰፊ ምህረት የሚገኝበት አጋጣሚ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሐጅ ያደረገ፣ በሐጁም ውስጥ ከማላገጥና ከማፈንገጥ የራቀ ሰው፣ ልክ እናቱ እንደወለደችው ዕለት ከወንጀል የጸዳ ሆኖ ይመለሳል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1449 / ሙስሊም 1350)
  3. ከእሳት ነፃ ለመውጣት ታላቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ከዐረፋ ዕለት የበለጠ አላህ (ሱ.ወ) ሰዎችን ከእሳት ነፃ የሚያወጣበት ዕለት የለም፡፡›› (ሙስሊም 1348)
  4. የሐጅ ምንዳ ጀነት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ተቀባይነትን ያገኘ ሐጅ ከጀነት ሌላ ለርሱ ምንዳ የለውም፡፡›› (አል ቡኻሪ 1683 / ሙስሊም 1349)

እነኚህና ሌሎች ትሩፋቶች የሚሰጡት ሃሳቡ(ኒያው) ላማረ፣ ከልቡ ለሚሰራ፣ ውስጡ ጽዱዕ ለሆነና የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ ላልሳተ ሰው ብቻ ነው፡፡

የሐጅ ዓላማዎች

ሐጅ በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚረጋገጡ ላቅ ያሉ ዓላማዎችና ግቦች አሉት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በእርድ ቀን ሐጅ አድራጊ ሊሰዋው ስለሚገባው እርድ ካወሳ በኋላ፡- ‹‹አላህን ስጋዎቿም ደሞቿም ፈጽሞ አይደርሰውም፡፡ግን ከናንተ የኾነው ፍራቻ ይደርሰዋል፡፡›› ይላል፡፡ (አል ሃጅ 37) ነብዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በካዕባ ዙሪያ መዞር፣በሠፋና በመርዋ መካከል መመላለስ፤ ጠጠር መወርወርም የተደረገው አላህን ለማውሳት ብቻ ነው፡፡›› (አቡ ዳውድ 1888)

ከነኚህ ዓላማዎችና ግቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ለአላህ መዋረድና እራስን ዝቅ ማድረግን መግለጽ

ሐጅ ላይ ያለ ሰው የድሎትና የመንፈላሰስ ገጽታዎች አይንጸባረቁበትም፡፡ የኢሕራም ትጥቁን በመልበስ የፈጣሪውን ደጅ የሚጠና መሆኑን ይገልጻል፡፡ ጥርት ባለ ልብ ወደ ፈጣሪው መጠቃለልን ከሚከለክሉትና ከሚያጠምዱት ዓለማዊ ስንክሳሮች እራሱን ያጸዳል፡፡ በዚህም የፈጣሪውን ምህረትና እዝነት ያገኛል፡፡ ከዚያም፣ በዐረፋ የፈጣሪውን ጸጋና ውለታ አመስጋኝ፣ ጌታውን አሞጋሽ፣ ለወንጀሉና ለስህተቱ ምህረትን ለማኝ ኾኖ ፈጣሪውን እየተማጸነ ይቆማል፡፡

  1. የጸጋ ምስጋና

አላህ (ሱ.ወ) ባሮቹን ካጎናጸፋቸው ጸጋዎች መካከል፣ በሐጅ የሁለት ጸጋዎች ምስጋና ይረጋገጣል፡፡ እነሱም የሀብት እና ለጤናማነት ጸጋ ምስጋና ናቸው፡፡ ሁለቱም የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ውስጥ ከሚጣቀምባቸው ጸጋዎች ሁሉ በላጮቹ ናቸው፡፡ በሐጅ ላይ ለነዚህ ሁለት ታላላቅ ጸጋዎች ምስጋና ይቀርባል፡፡ ሰዎች ነፍሳቸውን ታግለው አላህን ለመታዘዝና ወደርሱ ለመቃረብ ገንዘባቸውን ያወጣሉ፡፡ ለተጣቀሙበት ጸጋ ምስጋና ማቅረብ ደግሞ አዕምሮ የሚያጸድቀው፣ እንዲሁም የሃይማኖት ሕግና መመሪያ የሚያዘው ግዳጅ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

  1. የሙስሊሞች መሰባሰብና መገናኘት

ከተለያየ የዓለም ክፍል የመጡ ሙስሊሞች በሐጅ ላይ ይገናኛሉ፣ ይተዋወቃሉ፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ በሰዎች መካከል ያሉ ልዩነቶች ይወገዳሉ፡፡ የሀብት፣ የፆታና የቀለም፣ እንዲሁም የቋንቋ ልዩነቶች ይወገዳሉ፡፡ የሙስሊሞች ቃል አንድ ይሆናል፡፡ በዚህ የሰው ዘር በተሰበሰበበት ታላቅ ስብሰባ ፡ በመልካም ማዘዝ፣ አላህን በመፍራትና በሐቅ ላይ በመመካከር እና በትዕግስት ላይ በመተዋወስ ላይ ያለው የታዳሚዎች አጀንዳ አንድ ይዋሃዳል፡፡ ትልቁ ዓላማውና ግቡ የሕይወት ግቦችን ከመለኮታዊ ግቦች ጋር ማቆራኘትና ማስተሳሰር ነው፡፡

  1. የመጨረሻውን ቀን ማስታወስ

ሐጅ፣ አንድን ሙስሊም የመገናኛውን ዕለት ያስታውሰዋል፡፡ ሐጅ የሚያደርግ ሰው፣ ልብሶቹን አውልቆ፣ ለሐጅ በመታጠቅ አቤት(ለበይክ) እያለ በዐረፋ ሜዳ ላይ ቆሞ የሰዎችን ብዛትና የልብሳቸው አንድ መሆንን ሲያይ ከከፈን ጋር እንደሚመሳሰል ያስተውላል፡፡ በዚህን ጊዜ አዕምሮው፣ አንድ ሙስሊም ከሞተ በኋላ ስለሚያጋጥመው የቀብር ሕይወት ያስባል፡፡ ይህም ከአላህ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ዝግጅት እንዲያደርግና ስንቅ እንዲቋጥር ይጋብዘዋል፡፡

  1. በንግግርም በስራም አላህን በብቸኝነት በመገዛት የአላህን አሃዳዊነት ይፋ ማድረግ

የሐጃጆች መለያቸው ተልቢያ ነው፡፡ (ለበይከላሁመ ለበይክ፤ ለበይከ ላ ሸሪ..ከ ለከ ለበይክ ኢነል ሐምደ ወኒዕመተ ለከ ወልሙልክ ላሸሪ..ከለክ) ‹‹አላህ ሆይ! ጥሪህን አክብረን መጥተናል፤ አንተ አጋር የለህም፣ አቤት ብለናል፤ ምስጋናም፣ ጸጋም፣ ንግሥናም ያንተ ነው፤ አንተ አጋር የለህም፡፡›› ይላሉ፡፡ ታላቁ ሠሓቢይ፣ የነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) ተልቢያ በማስመልከት፣ «አሐዳዊነት ገላጭ ነው፡፡» ያለው ለዚህ ነው፡፡ (ሙስሊም 1218) ግልጽ በሆነ መልኩ በተግባር፣ በንግግርና እንዲሁም በየሐጅ ሥራዎች ሁሉ የአላህ አሐዳዊነት ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡

 ዑምራ

ዑምራ፣ የኢሕራም ልብስ በመልበስ በካዕባ ዙሪያ ሰባት ጊዜ በመዞር፣ በሠፋና መርዋ መሐከል ሰባት ጊዜ በመመላለስ እና ከዚያም ጸጉርን በመላጨት ወይም በማሳጠር የሚጠናቀቅ የአምልኮ ተግባር ነው፡፡

ኢስላማዊ ፍርዱ፡ ማድረግ በሚችል ሰው ላይ በዕድሜ አንድ ጊዜ መስራቱ ግዴታ ነው፡፡ ደጋግሞ መስራቱ ይወደዳል፡፡

ጊዜው፡ ዓመቱን ሙሉ ዑምራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በረመዳን ወር ውስጥ የሚደረግ ዑምራ እጥፍ ድርብ የሆነ ምንዳ አለው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በረመዳን ውስጥ የሚደረግ ዑምራ (በምንዳ) ከሐጅ ጋር ይስተካከላል፡፡›› (አል ቡኻሪ 1764/ሙስሊም 1256)