ሠላት

የሠላት መሰረታዊ ትርጉሙ፡ መማፀን ወይም መለመን ሲሆን፣ ባሪያን ከፈጣሪው ጋር የምታገናኝ መስመር ነች፡፡ በውስጧ ወሳኝ የሆኑ የባርነት መገለጫዎችን አቅፋለች፡፡ ወደ አላህ መሸሽና በርሱ መታገዝን አዝላለች፡፡ በሠላት ውስጥ ባሪያው ጌታውን ይለምናል፣ በሚስጥር ያወራል፣ ያወሳዋል፣ ነፍሱ ትጸዳለች፣ ባሪያው እውነተኛ ማንነቱን ያስታውስበታል፣በውስጧ እየኖረባት ያለችውን የዱንያን ትክክለኛ ገጽታ ይገነዘባል፡፡ የዚህች ዓይነቷ ሠላት፣ ባሪያው በአላህ ህግጋትና ድንጋጌ ላይ ጽናት እንዲኖረው፣ ከግፍ፣ ከዝሙትና ከአመፀኝነት እንዲርቅ ታደርገዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሠላትንም ደንቡን ጠብቀህ ስገድ፤ ሠላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45)

የሠላት ደረጃና ትሩፋት

ሠላት ከአካላዊ አምልኮዎች ታላቋና ደረጇም የላቅ ነው፡፡ ቀልብን፣ አዕምሮንና ምላስን በአንድነት የሚያሳትፍ አምልኮ ነው፡፡ የሠላት አንገብጋቢነትን ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ይቻላል፡፡

ሠላት ከፍ ያሉ ደረጃዎች አሉት

  1. ከኢስላም ማዕዘናት መካከል ሁለተኛው ማዕዘን ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «ኢስላም በአምስት መሰረታዊ ማዕዘናት ላይ ተገነባ፡፡ -ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ የለም፣ ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር፣ ሠላትን ማቋቋም፣….» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 8 /ሙስሊም 16) የአንድ ግንባታ ማዕዘን ወይም ምሰሶ፣ ያለርሱ ግንባታው የማይቆምበት መሰረቱ ማለት ነው፡፡
  2. ሸሪዓዊ መረጃዎች፣ በሙስሊሞችና በካሃዲያን መካከል መለያ ነጥብ ያደረጉት ሠላትን ማቋቋምን ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «በአንድ ሰውና በክህደት መሐከል ያለው ነገር ሠላትን መተው ነው፡፡» ብለዋል፡፡(ሙስሊም 82) «በእኛና በእነርሱ መሐከል ያለው ኪዳን ሠላት ነው፡፡ እርሷን የተወ በርግጥ ክዷል፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 2621/ አል ነሳኢ 463)
  3. አላህ (ሱ.ወ) ሠላትን በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ እንዲተገበር አዟል፡፡ በመንገደኛነት፣ በነዋሪነት፣ በሰላም፣ በጦርነት፣ በጤንነት፣ በህመምም ላይ ሆኖም በሚቻለው መጠን ሁሉ ይተገበራል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «በሰላቶች ተጠባበቁ» ይላል፡፡ (አልበቀራ 238) ምዕመናን ባሮቹን ደግሞ፡- «እነዚያም እነሱ በስግደቶቻቸው ላይ የሚጠባበቁ የኾኑት፡፡»በማለት ይገልጻቸዋል፡ (አል ሙእሚኑን 9)

የሠላት ትሩፋት

አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ፣ በጦርነትና በአደጋ ጊዜ እንኳን ቢሆን፣ ብቻ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆኖ ሠላትን እንዲተገብር አዟል፡፡

የሠላትን ትሩፋት በማስመልከት በርካታ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች ተላልፈዋል፡፡ ከነሱም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ሠላት ወንጀሎችን ታብሳለች፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «አምስት ሠላቶችና ከጁምዓ እስከ ጁምዓ ትላልቅ ወንጀሎች እስካልተጣሱ ድረስ በመካከላቸው የሚፈፀሙትን ወንጀሎች ያብሳሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 233/ አል ቲርሚዚ 214)
  2. ሠላት፣ለአንድ ሙስሊም በመላው ሕይወቱ የምታበራለት ብርሃኑ ናት፡፡ በመልካም ነገር ላይ ታግዘዋለች፡፡ ከመጥፎ ነገሮች ታርቃዋለች፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሶላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡» ይላል፡፡ (አል አንከቡት 45) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «ሠላት ብርሃን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 223)
  3. ሠላት፣ የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምባት ጉዳይ ናት፡፡ እርሷ ካማረችና ተቀባይነት ካገኘች፣ የተቀረው ስራ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ እርሷ ተመላሽ ከሆነች የተቀሩት ስራዎችም ተመላሽ ይሆናሉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «የትንሳኤ ቀን ባሪያው በመጀመሪያ የሚገመገምበት ነገር ሠላት ነው፡፡ እርሷ ካማረች የተቀሩት ስራዎቹ ያምራሉ፡፡ እርሷ ከተበላሸች የተቀሩት ስራዎችም ይበላሻሉ፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ሙዕጀሙል አውሰጥ ሊጠበራኒ 1859)
ሙእሚን በጣም የሚረካበት ቆይታ፣ በሠላት ውስጥ ጌታውን ሲያናግር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ፣ መንፈሳዊ እረፍትን፣ መረጋጋትናና አጫዋችን ያገኛል፡፡ ሠላት ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ታላቋ የዓይን ማረፊያ ነበረች፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) የህንኑ ሲገልጹ፡-«የዓይኔ መርጊያ በሰላት ውስጥ ተደርጎልኛል፡፡»ይላሉ፡፡ (አል ነሳኢ 3940) ወደ ሠላት ለሚጣራው ሙኣዚናቸው ቢላል፡- «ቢላል ሆይ በርሷ አሳርፈን» ይሉ ነበር፡፡ (አቡ ዳውድ 4985) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የሆነ ጉዳይ ካሳሰባቸው ወይም ካጨናነቃቸው ወደ ሰላት ይሸሹ ነበር፡፡ (አቡ ዳውድ 1319)

ሠላት ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?

ሠላት፣ በወር አበባና በወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች ሲቀሩ በማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ባለው፣ ሃላፊነትን ለመሸከም በደረሰ ሙስሊም ሁሉ ላይ ግዴታ ነው፡፡ ሴቶች በወር አበባ ወይም በወሊድ ደም ላይ ሆነው አይሰግዱም፡፡ ከጸዱና ደሙ ከተቋረጠ በኋላም ሠላትን አይከፍሉም፡፡ (ገጽ 96 ተመልከት)

ለአቅመ አዳምና ሄዋን መድረስ የሚወሰነው ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ ሲሟላ ነው፡፡

አስራ አምስት ዓመት መድረስ
በፊት ለፊት ወይም በኋላ ብልቶች ዙሪያ ከርደድ ያለ ጸጉር ማብቀል
በሕልም ወይም በንቃተ ሕሊና የፍቶት ፈሳሸን ማፍሰስ
ለሴት፣ የወር አበባ መታየት ወይም ማርገዝ

 ለሠላት ሊሟሉ የሚገቡ መስፈርቶች ምንድን ናቸው?

  1. ከሐደስና ከነጃሳ መጥራት፡፡ ዝርዝር ገለፃውን አሳልፈናል (ገጽ፣ 91 ተመልከት)
  2. ሀፍረተ ገላን መሸፈን

ሀፍረተ ገላን በአጭርነትና ወይም በስስነት የሰውነት ክፍሎችን የማያጋልጥና የማያሳይ በሆነ ልብስ መሸፈን የግድ ነው፡፡

ሀፍረተ ገላ ሦስት ዓይነት ነው፡፡

ለሴት፡ ሰላት ለመስገድ የደረሰች ሴት ሀፍረተ ገላ ከፊቷና ከመዳፎቿ በስተቀር ሰውነቷ በሙሉ ነው፡፡

ለሕፃን፡ ትንሽ ሕፃን ልጅ ሀፍረተ ገላው ሁለቱ ብልቶቹ ብቻ ናቸው፡፡

ወንድ፡ የደረሰ ወንድ ሀፍረተ ገላ ከእምብርቱ እስከ ጉልበቱ ድረስ ነው፡፡

አላህ (ሱ.ወ)፡- «የአደም ልጆች ሆይ (ሀፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡» ይላል፡፡ (አል

አዕራፍ 31) ሀፍረተ ገላን መሸፈን ከመጌጥ ትንሹ ደረጃ ነው፡፡ ‹‹በመስገጃው ሁሉ›› ማለት በየሠላቱ ማለት ነው፡፡

 ሙስሊም ሴት፣ በሠላት ውስጥ ከፊቷና ከመዳፎቿ በስተቀር ሌላውን ሰውነቷን በሙሉ መሸፈን አለባት፡፡ .

  1. ወደ ቂብላ መቅጣጨት ወይም መዞር :

አላህ (ሱ.ወ)፡- «ከየትም (ለጉዞ) ከወጣህበት ስፍራ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ አቅጣጫ አዙር፡፡» ብሏል፡፡ (አል በቀራ 149)

 አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሶላት በምእመናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡» ይላል፡፡ (አል ኒሳእ 103)

  • የሙስሊሞች የስግደት አቅጣጫ የተከበረው ካዕባ ነው፡፡ እሷን የገነባት የነብያት አባት የሆነው ኢብራሂም(ዐ.ሰ) ነው ፡፡ ነብያት ወደርሷ የአምልኮ ጉዞ (ሐጅ) አድርገዋል፡፡ እርሷ የማትጠቅም የማትጎዳም ድንጋይ እንደሆነች እናውቃለን፡፡ ግን አላህ (ሱ.ወ) ሙስሊሞች በሙሉ ወደ አንድ አቅጣጫ በመዞር አንድ እንዲሆኑ፣ ስንሰግድ ወደርሷ እንድንዞር ወይም እንድንቅጣጭ አዞናል፡፡ ስለሆነም፣ ወደ ካዕባ በመዞራችን የአላህ ባርነታችንን እንገልጻለን፡፡
  • አንድ ሙስሊም ሲሰግድ ካዕባን ፊት ለፊት የሚመለከታት ከሆነ ወደርሷ ፊቱን ማዞር ግድ ነው፡፡ ከርሷ በርቀት የሚገኝ ሰው ደግሞ ወደ መካ አቅጣጫ መዞሩ በቂ ነው፡፡ በሚቅጣጭ ጊዜ ከካዕባ አቅጣጫ ትንሽ ማዘንበሉ ወይም መዞሩ ችግር የለውም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «በምስራቅና በምዕራብ መሐከል ያለ በሙሉ የሠላት አቅጣጫ (ቂብላ) ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 342)
  • ልክ የተቀሩት ግዴታዎች በመቸገር ምክንያት ግዴታነታቸው እንደሚነሳ ሁሉ፣ በበሽታ ወይም በሌላ ምክንያት ወደ ካዕባ መዞር ላልቻለም ግዴታነቱ ይነሳለታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «አላህንም የቻላችሁትን ያክል ፍሩት፡፡» ይላል፡፡ (አል ተጋቡን 16)
  1. የሠላት ወቅት መግባት

ይህ ለሠላት ትክክለኛነት መስፈርት ነው፡፡ ወቅቷ ከመግባቱ በፊት የተሰገደች ሠላት ትክክለኛ አትሆንም፡፡ ከወቅቷ ማዘግየትም የተከለከለ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሶላት በምእመናን ላይ በጊዜያት የተወሰነች ግዴታ ናትና፡፡» ይላል፡፡ (አል ኒሳእ 103)

ወቅት በመግባት ዙሪያ በተወሰኑ ነገሮች ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡

  • ሠላትን በመጀመሪያው ወቅት ላይ መስገዱ በላጭ ነው፡፡
  • ሠላትን በወቅቷ መስገድ ግዴታ ነው፡፡ በማንኛውም ምክንያት ቢሆንም ሠላትን ማዘግየት ክልክል ነው፡፡
  • በእንቅልፍ ወይም በመርሳት ምክንያት ሠላት ያለፈው ሰው ባስታወሰ ጊዜ ፈጥኖ መስገድ አለበት፡፡

 አምስቱ የግዴታ ሠላቶችና ወቅቶቻቸው

አላህ (ሱ.ወ) በሙስሊሞች ላይ በቀንና በሌሊት ውስጥ አምስት ሠላቶችን ግዴታ አደርጓል፡፡ እነኚህ ሠላቶች የሃይማኖት ምሶሶዎች ናቸው፡፡ ግዴታነታቸውም እጅግ አጽንዖት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ለነርሱም የሚከተሉትን ወቅቶች አድርጎላቸዋል፡፡

የፈጅር ሠላት፡ ሁለት ረካዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ጎሕ ከሚወጣበት ጊዜ ሲሆን፣ በአድማስ ላይ ብርሃን ሲፈነጥቅ ወይም ጨለማ መገፈፍ ሲጀምር ይከሰታል፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ፀሐይ ስትወጣ ነው፡፡

የዙህር ሰላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ፀሐይ ከመሐል አናት በምታዘነብልበት ጊዜ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ የእያንዳንዱ ነገር ጥላ ከራሱ ቁመት ጋር ሲስተካከል ነው፡፡

የዐሥር ሠላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው የዙህር ወቅት ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ይኸውም የእያንዳንዱ ነገር ጥላ ከራሱ ቁመት ጋር ሲስተካከል ነው፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ፀሐይ ስትጠልቅ ነው፡፡ አንድ ሙሰሊም ይህችን ሠላት፣ የፀሐይ ብርሃን ጮራ መድከምና መገርጣት ሳይጀምር ፈጠን ብሎ ሊሰግድ ይገባዋል፡፡

የመግሪብ ሠላት፡ ሦስት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ፀሐይ ከጠለቀችበትና ፍንጣቂዋ ከአድማስ ላይ ሲወገድ ወይም ሲደበቅ ነው፡፡ የሚያበቃው ደግሞ ከፀሐይ መጥለቅ በኋላ የሚታየው ቀዩ ወጋገን ሲጠፋ ነው፡፡

የዒሻእ ሠላት፡ አራት ረከዓ ነው፡፡ ወቅቱ የሚጀምረው ቀዩ ብርሃን ከጠፋበት ቅጽበት ነው፡፡ የሚያበቃው እኩለ ሌሊት ላይ ነው፡፡ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገጥምበት ጊዜ ጎህ እስኪ ቀድ ባሉት ሰዓቶችም ውስጥ ሊሰገድ ይችላል፡፡

አንድ ሙስሊም የሰላትን ወቅቶች በተመለከተ በወቅቶች ሰሌዳ መጠቀም ይችላል ነገር ግን ወደ ሰላት ለመግባት እሱን የመመልከት ግዴታ የለበትም

 የሠላት ቦታ (ስፍራ)

ኢስላም ሠላት በህብረት ወይም በጀመዓ እንዲፈፀም አዟል፡፡ ለሙስሊሞች መገናኛና መሰባሰቢያ መንገድ ይሆን ዘንድም በመስጂድ ውስጥ እንዲፈፀም አበረታቷል፡፡ ይህን በማድረግ፣በመካከላቸው ወንድማማችነትና ፍቅር ይጨምራል፡፡ ኢስላም የጀመዓ ሠላትን አንድ ሰው ለብቻው ከሚሰግደው ሰላት በብዙ ደረጃዎች የሚበልጥ አድርጎታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «አንድ ሰው በጀመዓ የሚሰግደው ሠላት በነጠላ ለብቻ ከሚሰገደው ሠላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 619/ ሙስሊም 650/ አህመድ 5921)

ሠላት በማንኛውም ስፍራ ቢሰገድ ትክክለኛ ነው፡፡ ይህም የአላህ እዝነት መገለጫ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- «ምድር መስገጃና ንጹህ ተደርጋልኛለች፤ከህዝቦቼ፣ ማንም ሰው ሠላት ከደረሰበት፣ በደረሰበት ስፍራ ይስገድ» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 328/ ሙስሊም 521)

የሠላት ቦታ ይዘት

ኢስላም፣ ሠላት የሚሰገድበት ቦታ ንጹህ እንዲሆን በመስፈርትነት አስቀምጧል። አላህ (ሱ.ወ)፡- «ወደ ኢብራሂምና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን ለዘዋሪዎቹና ለተቀማጮቹም፣ ለአጎንባሾች ሰጋጆቹም አጥሩ ስንል ቃል ኪዳን ያዝን፡፡» ይላል፡፡ (አል በቀራ 125) የነገሮች መስረት ንጹህ ነው፤ ነጃሳ ደግሞ ባዕድ/መጤ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ነጃሳ ያለበት መሆኑን እርግጠኛ ባልሆንክበት ነገር ላይ ንጹህነትን ትወስናለህ፡፡ በመስገጃ ወይም ሰሌን ላይ እንጂ አለመስገድ የሚወደድ ተግባር አይደለም፡፡

ልንከተላቸው የሚገቡ በርካታ ስርዓተ ደንቡች አሉ፡፡ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. በመስገጃ ስፍራ ላይ ሰዎችን አለማስቸገር፡፡ ለምሳሌ፡የመተላለፊያ መንገድ ላይ መስገድ፣ እንዲሁም ግፊያና መጨናነቅን በሰዎች ላይ የሚፈጥር ስፍራ ላይ መቆም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሰዎችን ማስቸገርና በነሱ ላይ ጉዳት ማድረስን ሲከለክሉ፡- «መጉዳትም መጎዳትም (በኢስላም) ቦታ የለውም፡፡» ብለዋል፡፡ (ኢብኑ ማጃህ 2340/ አህመድ 2865)
  2. በመስገጃ ቦታ ላይ፣እንደ ስዕል፣ ከፍ ያለ ድምጽና ሙዚቃ ያለ፣ ሰጋጅን የሚረብሽና ትኩረቱን የሚበትን ነገር መኖር የለበትም፡፡
  3. የመስገጃው ስፍራ ለሹፈትና ለፊዝ የሚያጋልጥ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ፡ ሰካራሞች በተሰበሰቡበት ወይም ጽንፈኞች በሚያዘወትሩበት ስፍራና በመሳሰሉት ቦታዎች፣መስገጃ መሆን የለባቸውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የካሃዲያንን አማልክት መሳደብን የከለከለው እነሱ ባለማወቅ አላህን እንዳይሰድቡ ለመከላከል ሲል ነው፡፡ እንዲህም ይላል፡- «እነዚያንም ከአላህ ሌላ የሚግገዟቸውን (ጣዖታት)አትስደቡ፤ ድንበርን በማለፍ ያለ ዕውቀት አላህን ይሰድባሉና፡፡» (አል አንዓም 108)
  4. የመስገጃ ቦታ፣ እንደ ዳንስና ጭፈራ ቤት ያለ፣ አላህን ለማመፅ የተዘጋጀ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ መሰሉ ስፍራ ሠላት መስገድ የተጠላ ነው፡፡

 

 የሠላት ቦታ

በመስጂድ ውስጥ ከጀመዓ ጋር መስገድ ትችላለህን?
አዎን
አዎ፡ ሠላትን በጀመዓ መስገድ በወንድ ላይ የጠበቀ ግዴታ ነው፡፡ ከስራዎች ሁሉ ትልቁና አላህ ዘንድ እጅግ የላቀ ነው፡፡ በጀመዓ መስገድ ለሴቶችም ይፈቀዳል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
በመስጂድ ውስጥ መስገድ ካልቻልክ ከሱ ሌላ ያሉ ቦታዎች ነጃሳ ናቸውን?
አዎን
በነጃሳ ቦታ ላይ መስገድ የተከለከለ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለሠላት ጽዱዕ እንድንሆን አዞናል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ቦታው ነጃሳ ባይሆንም ሰዎችን የሚያስቸግር ቦታ ላይ መስገድ ይፈቀዳል? ለምሳሌ መተላለፊያ መንገዳቸው ቢሆን?
አዎን
ሰዎችን ማስቸገርና ለመስገድ እንኳን ቢሆን በነርሱ ላይ መጨናነቅን መፍጠር ክልክል ነው፡፡ ሌላ ቦታ ልትመርጥና ልትቀይር ይገባል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
እንደ ፎቶና ከፍተኛ ድምፅ የመሰሉ ከሠላትህ የሚያስተጓጉሉ ነገሮች ባሉበት ቦታስ?
አዎን
ሰጋጅን ከሚረብሹና ሠላቱን ከሚያስተጓጉሉ ነገሮች ሁሉ መራቅ ያስፈልጋል፡፡
አይቻልም(በፍፁም)
ይህ ህዝብ (የነቢዩ ኡማህ) ከተቸረው ልዩ ነገር መሐከል በምድር ላይ በየትም ስፍራ ቢሰገድ ሠላቱ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ነው፡፡