የሠላት ማዕዘናት ግዴታዎች

የሠላት ማዕዘናት የሚባሉት የሠላት ዋና ዋና ክፍሎች ሲሆኑ ታውቆም ሆነ በመርሳት ከተተዉ ሠላት የሚበላሽባቸው ነገሮች ናቸው፡፡

እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡

ተክቢረቱል ኢሕራም (የመግቢያ ተክቢራ ወይም ‹‹አላሁ አክበር‹‹) • መቆም ለሚችል ሰው መቆም • ከተከታይ ወይም ማእሙም በስተቀር ፋቲሐን ማንበብ፤ • ሩኩዕ፤ • ከሩኩዕ ቀና ማለት፤ • ሱጁድ፤ • በሁለት ሱጁዶች መሐከል መቀመጥ፤ • የመጨረሻው ተሸሁድ፤ • ለመጨረሻው ተሸሁድ መቀመጥ፤ • መረጋጋት ወይም ጡመእኒና እና ማሰላመት ናቸው

ሰላት ግዴታዎች ማለት በሰላት ውስጥ ግዴታ የሆኑ አካላት ማለት ሲሆን እነዚህ ግዴታዎች ቢሆን ተብሎ ከተተው ሰላቱ ይበላሻል። ነገር ግን አንድ ሰው ረስቶ ወይም ዘንግቶ ከተዋቸው የጐደለውን ለመሙላት የመርሳት ሱጁድ የመውረድ ግዴታ አለበት። ይህም ወደፊት በሚወጣው ርዕስ የምንመለከተው ይሆናል።

የሰላት ግዴታዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡

ከተክቢረተል ኢሕራም ውጭ ያሉት ሁሉም ተክቢራዎች፤ • ሩኩዕ ላይ እያሉ አንድ ጊዜ ‹‹ሱብሐነረቢየል ዐዚም›› ማለት፤ • ብቻውን ለሚሰግድና ኢማም ሆኖ ለሚያሰግድ ‹‹ሰሚዐላሁ ሊመን ሐሚደሁ›› ማለት፤ • ለሁሉም ሰጋጅ ‹‹ረበና ወለከልሐምዱ›› ማለት፤ • ሱጁድ ውስጥ አንድ ጊዜ ‹‹ሱብሐነ ረቢየል አዕላ›› ማለት፤ • በሁለቱ ሱጁዶች መሐከል ሲቀመጡ አንድ ጊዜ ‹‹ረቢግፊርሊ›› ማለት፤ እና • የመጀመሪያው ተሸሁድ፤ ናቸው፡፡ እነኚህ ግዴታዎች በመርሳት ምክንያት ከተተዉ ግዴታነታቸው ይቀራል፡፡ እነርሱም የእርሳና ሱጁድ ወይም ሱጁደ ሰህው በማድረግ ይጠገናሉ፡፡

የሠላት ውስጥ ሱናዎች፡ ማንኛውም የሠላት ማዕዘን ወይም ግዴታ ውስጥ የማይመደብ ንግግርም ሆነ ተግባር የሠላት ውስጥ ሱና ይባላል፡፡ ሠላትን የሚያስውብና የሚያሟላ ነው፡፡ በመሆኑም እርሱን በዘውታሪነት መፈፀም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እርሱን በመተዉ ሠላት አይበላሽም፡፡

ሱጁደ ሰህው

ሱጁደ ሰህው፣ ሁለት ሱጁዶችን ማድረግ ሲሆን በሠላት ውስጥ ለሚከሰቱ ጉድለቶችና ክፍተቶች ማካካሻና መጠገኛነት የተደነገገ ነው፡፡

ሱጁደ ሰህው ማድረግ የሚፈቀደው መቼ ነው?

በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ሱጁደ ሰህው ይደረጋል፡

  1. አንድ ሰጋጅ በመርሳትና በስህተት ምክንያት በሠላቱ ውስጥ ተጨማሪ ሩኩዕን ወይም ሱጁዱን ወይም መቆም ወይም መቀመጥን ከጨመረ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  2. ከሠላት ማዕዘናት መካከል አንዱን ማዕዘን ካጎደላ፣ ያንን ያጎደለውን ማዕዘን ያሟላና በሠላቱ ማብቂያ ላይ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  3. እንደ ተሸሁደል አወል(የመጀመሪያው መቀመጥ) ዓይነት ከሠላት ግዴታዎች መካከል አንዱን ረስቶ ከተወ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  4. የሰገዳቸውን የረከዓት ቁጥር ከተጠራጠረ፣ መጀመሪያ እርግጠኛ የሆነውን፣አነስተኛውን ቁጥር ይይዝና ካሟላ በኋላ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡

የአሰጋገዱ ዓይነት፡ በመደበኛ ሠላቱ ውስጥ እንዳለው ሱጁድና መቀመጥ ዓይነት፣ በሱጁዶቹ መሐከል የሚቀመጥ ሆኖ ሁለት ሱጁዶችን ይሰግዳል፡፡

ሱጁድ የማድረጊያው ጊዜ፡ ሱጁደ ሰህው ሁለት ጊዜዎች አሉት፤ ሰጋጁ ከሁለቱ በአንዱ በፈለግው ጊዜ ሊሰግደው ይችላል፡፡

  • ከመጨረሻው ተሸሁድ በኋላ ይሰግዳትና ከዚያም ያሰላምታል፡፡
  • ሠላቱን በሰላምታ ካሰናበተ በኋላ ሁለት ሱጁዶችን ስግዶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ በሰላምታ ያሰናብታል፡፡

ሠላትን የሚያበላሹ ነገሮች

  1. ሠላት፣ አንድ ሰጋጅ መተግበር የሚችለው ሆኖ፣ ሲታወቀውም ይሁን በስህተት ማዕዘንን ወይም የሠላት መስፈርትን ከተወ ሠላቱ ትበላሻለች፡፡
  2. ሲታወቀው ከሠላት ግዴታዎች መካከል አንዱን ግዴታ ከተወ ትበላሻለች፡፡
  3. ሲታወቀው ከተናገረ ትበላሻለች፡፡
  4. ሠላት ድምጽ ባለው ሳቅ፣ በማሽካከት ትበላሻለች፡፡
  5. በማያስገድዱ ሁኔታዎች ውስጥ በሚደረጉ ተከታታይና በርካት በሆኑ እንቅስቃሴዎች ትበላሻለች፡፡

በሠላት ውስጥ የተጠሉ ነገሮች፡፡

እነኚህ ነገሮች፣ የሠላትን ምንዳ የሚቀንሱ፣ ለሠላት መተናነስን የሚያጠፉ፣ እና የሠላትን ግርማ ሞገስ የሚሰልቡ ናቸው፡፡ እነርስሩም እንደሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. በሰላት ውስጥ መዞር የተጠላ ተግባር ነው ምክንያቱም ነቢዩ(ሰ∙ዐ∙ወ) በሰላት ውስጥ መዞርን (እየዞረ መመልከትን) አስመልክቶ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ‹‹እርሱ ሰርቆት ነው(ሸይጧ የአላህ ባሪያ ከሰላቱ ይሰርቀዋል›› ብለዋል።(ቡኻሪ፡ 718)
  2. በሠላት ውስጥ በእጆች፣ በፊት፣ ጣቶችን በማጣመርና በማንጫጫት መጫወት ይጠላል፡፡
  3. አንድ ሰው፣ ልቡ በሽንት ሐሳብና በምግብ ክጃሎት ሐሳብ ልቡ ተጠምዶ ወደ ሠላት መግባቱ ይጠላል፡፡ ነገሩ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዳሉት ነው፡፡ ‹‹ምግብ ቀርቦ፣ ሁለቱ ቀሻሾች እየገፈተሩትም ሠላት የለም›› (ሙስሊም 560)

 

 የተወደዱ ሠላቶች የሚባሉት ምንድን ናቸው?

በሙስሊም ላይ፣በቀንና በሌሊት ግዴታ የሚሆኑት ሠላቶች አምስት ናቸው፡

እንዲህ ከመሆኑ ጋር፣ ኢስላማዊው ድንጋጌ ለአንድ ሙስሊም ከነኚህ አምስት ሠላቶች በተጨማሪ የውዴታ ሠላትን እንዲሰግድ ደንግጎለታል፡፡

እነኚህ ሠላቶች የአላህን ውዴታ የማግኚያ ሰበቦች ናቸው፡፡ ከግዴታ ሠላቶችም የጎደለውን የሚያሟሉ ናቸው፡፡ የውዴታ ሠላቶች ብዙ ናቸው፤ ከነርሱ መካከል ዋንኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. የተዘወተሩ ሱናዎች( አር ረዋቲብ)፤ይሄንን ስያሜ ያገኙት ከግዴታ ሠላቶች ጋር ተቆራኝተው ስለሚመጡ፣ እንዲሁም አንድ ሙስሊም የማይዘነጋቸው በመሆኑ ነው፡፡

ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ማንም ሙስሊም ግዴታ ሳይሆን በውዴታ የሆኑ አስራ ሁለት ረከዓዎችን አይሰግድም አላህ በጀነት ቤትን ቢገነባለት እንጂ›› (ሙስሊም 728)

እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1 ከፈጅር ( ከጎሕ መቅደድ) ሠላት በፈት ሁለት ረከዓ፡
2 ከዙሁር ሠላት በፈት አራት ረከዓ፤ በየሁለት ረከዓው ያሰናብታል፡፡ ከዚያን ደግሞ ከዙሁር በኋላ ሁለት ረከዓዎችን ይሰግዳል፡፡
3 ከመግሪብ ሠላት በኋላ ሁለት ረከዓ
4 ከዒሻእ በኋላ ሁለት ረከዓ
  1. የዊትር ሠላት፡ በዚህ ስያሜ የተጠራችው የረከዓዎቿ ቁጥር ኢ-ተጋማሽ ስለሆነ ነው፡፡ ከውዴታ ሠላቶች ሁሉ በላጯ ነች፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹እናንተ የቁርኣን ባለቤቶች ሆይ ዊትርን ስገዱ›› ብለዋል፡፡ (አቲርሚዚ 453/ ኢብኑ ማጃህ 1170)

የዊትር ሠላት ተመራጩ ጊዜ በሌሊቱ ማብቂያ አካባቢ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ከዒሻእ ሠላት በኋላ ጎሕ እስኪቀድ ድረስ በየትኛውም የሌሊት ክፍል ሊሰግዳት ይችላል፡፡

የዊትር ሠላት የረከዓዎች ቁጥር ገደብ የለውም፡፡ ትንሹ ቁጥር አንድ ረከዓ ነው፡፡ ተመራጩ ቁጥር ሦስት ረከዓ ነው፡፡ በዚህ ላይ የፈለገውን መጨመር ይችላል፡፡ የኣላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አስራ አንድ ረከዓ አድርገው ይሰግዷት ነበር፡፡

የውዴታ ሠላቶች መሰረታዊ ፈለግ ባለ ሁለት ረከዓ ሠላት መሆኗ ነው፡፡ ሁለት ረከዓዎችን ይሰግድና ያሰላምታል፤ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡ የዊትር ሠላትም እንደዚሁ ነች፡፡ ግን ሠላቱን ማገባደድ ሲፈልግ አንድ ረከዓ ይሰግድና በርሷ ያጠናቅቃል፡፡ በዊትር ሠላት ውስጥ፣ ከሩኩዕ ቀና ካለ በኋላ፣ ሱጁድ ከማድረጉ በፊት በሐዲስ የተወረዱትን ውዳሴዎች ማነብነብ ይወደድለታል፡፡ ከዚህም በኋላ፣ ሁለት መዳፎቹን ወደ ላይ በመዘርጋት አላህን ይለምናል፡፡ ይህ ዱዓ፣ ዱዓኡል ቁኑት በመባል ይታወቃል፡፡

በፈቃደኝነት የሚሰገዱ ሠላቶች የሚከለከሉበት ወቅት፡

ኢስላም ሠላት በውስጣቸው እንዳይሰገድ ነጥሎ ከጠቀሳቸው ወቅቶች በስተቀር የተቀሩት ወቅቶች በሙሉ አንድ ሰው የውዴታ ሠላቶችን ያለ ገደብ ሊሰግድ ይችላል፡፡ እነኚህ የተከለከሉት ወቅቶች የከሃዲያን ማምለኪያ ሰዓታት ስለሆኑ ያለፈን የግዴታ ሠላት አለያም እንደ ተሒየተል መስጂድ ያሉ ሰበብ ያላቸውን ሠላቶች ካልሆነ በስተቀር የውዴታ ሠላቶችን መስገድ አይቻልም፡፡ ይህ ሠላትን በተመለከተ ያለው ፍርድ ሲሆን አላህን ማወደስና(ዚክር) እና አላህን መለመን(ዱዓእ) ግን በየትኛውም ሰዓት ሊተገበር ይችላል፡፡

የተከለከሉት ወቅቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1 ጎሕ ከቀደደበት ጊዜ ጀምሮ ፀሐይ ወጥታ የጦር ዘንግን ያህል ትንሽ ከፍ እስከምትል ድረስ ያለው ወቅት፤ የምድር ወገብ አካባቢ ላሉ አገሮች ከ20 ደቂቃ በኋላ ይህ ወቅት ይደርሳል፡፡
2 ፀሐይ በሰማይ መሐከል ሆና ወደ መጥለቂያዋ እስክትዘነበል ድረስ መስገድ አይቻልም፡፡ ይህ የዙሁር ሰላት ወቅት ከመግባቱ በፊት ያለ ትንሽ ጊዜ ነው፡፡
3 ከዐሥር ሠላት በኋላ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ያለው ጊዜ፡

 ሠላተል ጀማዓ (በሕብረት መስገድ)

አላህ(ሱ.ወ) ወንዶችን በሕብረት እንዲሰግዱ አዟቸዋል፡፡ ሠላተል ጀማዓ ትልቅ ምንዳ እንዳለውና ልቅናውን የሚናገሩ ሐዲሶች ወርደዋል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የሕብረት ሠላት ከነጠላ ሠላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል፡፡›› ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 619 / ሙስሊም 650)

የሠላተል ጀማዓ ትንሹ ቁጥር ኢማምና አንድ ተከታይ ነው፡፡ የጀመዓው ቁጥር በበዛው ልክ አላህ ዘንድ ያለውም ተወዳጅነት ይጨምራል፡፡

የመከተል ትርጉም፡

መከተል ማለት፣ አንድ ተከትሎ የሚሰግድ ሰው ሠላቱን በኢማሙ ማሰሩ ነው፡፡ ተከትሎ የሚሰግደው ሰው ኢማሙን በሩኩዑ፣ በሱጁዱ ይከተለዋል፡፡ የቁርኣን ንባቡን ደግሞ ያዳምጠዋል፡፡ ኢማሙን ሊቀድመው ወይም ከርሱ ወደ ኋላ መቅረት አይገባውም፤ ይልቁንም ኢማሙ የሚሰራውን ነገር በቶሎ እየተከተለ ይተገብራል፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ እነሆ ኢማም የተደረገው ሊከተሉት ነው፡፡ አላሁ አክበር ሲል አላሁ አክበር በሉ፤ አላሁ አክበር እስኪልም ቀድማችሁ አላሁ አክበር አትበሉ፤ ሲያጎነብስ አጎንብሱ፣ እስኪያጎነብስ ድረስም አታጎንብሱ፤ ሰሚዐላሁ ሊመን ሐሚደሁ ሲል፣ ረበና ወለከል ሐምዱ በሉ፤ ሲሰግድም ስገዱ፤ እስኪሰግድ ድረስም አትስገዱ…..›› (አል ቡኻሪ 701/ ሙስሊም 414 / አቡዳውድ 603)

ለኢማምነት የሚቀደመው ማን ነው?

የአላህን መጽሐፍ በቃሉ የሸመደደ ሰው ለኢማምነት ይቀደማል፡፡ ከርሱ በመለስ ያለው ይከተለዋል እንዲህም እያለ ይቀጥላል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የአላህን መጽሐፍ ይበልጥ አሳምሮ የሚያነብ ሰው ለኢማምነት ይቀደማል፡፡ በንባብም የሚስተካከሉ ከሆነ ደግሞ ይበልጥ ፈለጌን(ሱናን) የሚያውቀው ይቀደማል፡፡….›› (ሙስሊም 673)

ኢማሙና ተከታዮቹ የሙቆሙት የት ነው?

ኢማሙ ከፊታቸው መሆን አለበት፡፡ ተከታዮቹ ደግሞ፣ የመጀመሪያውን ሠፍ ብሎ የሚቀጥለውን እያሟሉ ተስተካክለው መቆም አለባቸው፡፡ ተከታዩ አንድ ከሆነ ደግሞ ከኢማሙ በስተቀኝ በኩል ይቆማል፡፡

ኢማም ተከትሎ ሲሰግድ ያመለጠውን ሠላት እንዴት ይሞላዋል?

ከሠላት የተወሰነ ክፍል አምልጦት ኢማሙን የተከተለ ሰው፣ ኢማሙ ኢስኪያሰናብት ተከትሎ ይሰግድና ከዚያም ቀሪዉን ይሞላል፡፡

ከኢማሙ ጋር ያገኘውን የሠላት ክፍል እንደ ሠላቱ መጀመሪያ፣ቀጥሎ የሚሰራውን ደግሞ እንደ ሠላቱ መጨረሻ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

ረከዓ በምን ትገኛለች?

ሠላትን የምንቆጥረው በረከዓዎች ቁጥር ነው፡፡ ከኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ የደረሰ ሰው ሙሉ ረከዓን አግኝቷል፡፡ ሩኩዕ ያመለጠው ሰው ደግሞ ኢማሙን ተከትሎ ወደ ሠላት ይገባል ነግር ግን ከዚያች ረከዓ ያመለጠው ስራና ንግግር ከረከዓዎቹ አይቆጠሩም፡፡

ከኢማሙ የመጀመሪያው የሠላት ክፍል ያመለጠው ሰው ምሳሌ፡

ከፈጅር ሠላት፣ ከኢማሙ ጋር ሁለተኛዋን ረከዓ ያገኘ ሰው፣ ኢማሙ ካሰላመተ በኋላ ቆሞ ያለፈችውን አንድ ረከዓ ማሟላት አለበት፡፡ አጠናቆ እስኪሰግድ ድረስ ማሰላመት የለበትም፤ ምክንያቱም የፈጅር ሠላት ረከዓ ቁጥር ሁለት ነው፤ እርሱ ደግሞ ያገኘው አንዷን በመሆኑ የተቀረውን ማሟላት አለበት፡፡

የዙሁር ሠላት ላይ፣ በሦስተኛዋ ረከዓ፣ ኢማሙን ሩኩዕ ላይ ያገኘው ሰው፣ ከኢማሙ ጋር ሁለት ረከዓዎችን አግኝቷል፡፡ ይህ ማለት ለተከትሎ ሰጋጁ ከዙሁር ሠላት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ረከዓዎች ሰገደ ማለት ነው፡፡ ኢማሙ ካሰናበተ በኋላ ቆሞ የተቀረውን ማሟላት አለበት፡፡ ዙሁር ባለ አራት ረከዓ ስለሆነ፣ ቆሞ የሚሞላቸው ረከዓዎች ሦስተኛዋንና አራተኛዋን ይሆናል ማለት ነው፡፡

ኢማሙ ከመግሪብ ሠላት በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ሆኖ ያገኘው ሰው፣ ኢማሙ ካሰላመተ በኋላ ሦስት ሙሉ ረከዓዎችን መስገድ አለበት፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ እርሱ ኢማሙን ያገኘው በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ነው፤ ረከዓን ማግኘት የሚቻለው ግን ከኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ በመድረስ ስለሆነ ነው፡፡

 አዛን

አላህ ለሙስሊሞች አዛን ያደረገው ሰዎችን ወደ ሰላት ለመጥራትና የሰላት ወቅት መግባቱን እንዲሁም የሰላቱን መጀመር ማሳወቂያ ይሆን ዘንድ ነው። ሙስሊሞች ለሰላት እየተጠራሩ ይሰባሰቡ ነበር። ግን አንድ ለሁሉ የሚጠራ አልነበረም አንዳንዶች የክርስቲያኖችን መሰል ደውል አድርጉ ሲሉ ተወሰኑት ደግሞ

እንደ አይሁዳዊያን ቀንድ ይሁን አለ ዑመር ወይም ለሰላት የሚጣራ ሰው አድርጉ አሉ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንደህ አሉ፦‹‹ ቢላል ሆይ! ተነስና ለሰላት ጥሪ አድርግ።››(ቡኻሪ 579 ሙስሊም377)

የአዛንና የኢቃም መገለጫ

  • በአዛንና በኢቃም ስነ- ስርዓት በግለሰብ ሳይሆን በቡድን ላይ ግዴታ ነው። አውቀው የተውት ከሆነ ሃጢአት ኖሮባቸውም ቢሆን ሰላታቸው ትክክል ነው።
  • አዛን ለማድረግ በመልካምና በሚሰማ ድምጽ ሆኖ ሰዎች ሰላት እንዲመጡ የሚጣራ መሆን አለበት
  • ለአዛንና ለኢቃም የተለያዩና የተረጋገጡ አኳኋኖች ከነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) ተዘግበዋል።

ኢቃም (የሠላት መጀመሪያ ጥሪ)

  1. አላ…ሁ አክበር፣ አላ…ሁ አክበር፤ አላ…ሁ አክበር አ…ላሁ አክበር!
  2. አሽሐዱ አን ላ..ኢላ..ሃ ኢለላ…ህ፤አሽሐዱ አን ላ..ኢላ..ሃ ኢለላ...ህ!
  3. አሽሐዱ አነ ሙሐመደን ረሱ…ሉላ…ህ! .
  4. ሐይየ ዐለ ሠላ…ህ!
  5. ሐይየ ዐለልፈላ…ሕ!
  6. ቀድ ቃመቲ ሠላ…ህ ቀድ ቃመቲ ሠላ…ህ!
  7. አላ…ሁ አክበር፣ አላ…ሁ አክበር!
  8. ላ..ኢላ…ሃ ኢለላ….ህ!

አዛን

  1. አላ…ሁ አክበር፣ አላ…ሁ አክበር፤ አላ…ሁ አክበር አ…ላሁ አክበር!
  2. አሽሐዱ አን ላ..ኢላ..ሃ ኢለላ…ህ፤አሽሐዱ አን ላ..ኢላ..ሃ ኢለላ...ህ!
  3. አሽሐዱ አነ ሙሐመደን ረሱ…ሉላ…ህ፤ አሽሐዱ አነ ሙሐመደን ረሱ…ሉላ…ህ!
  4. ሐይየ ዐለ ሠላ…ህ፤ ሐይየ ዐለ ሠላ…ህ!
  5. ሐይየ ዐለልፈላ…ሕ፤ ሐይየ ዐለልፈላ…ሕ!
  6. አላ…ሁ አክበር አላ…ሁ አክበር
  7. ላ..ኢላ…ሃ ኢለላ….ህ!

ሙኣዚኑን ተከትሎ መድገም

አዛን ለሰማ ሰው፣ ሙኣዚኑን ተከትሎ እርሱ የሚለውን በሙሉ መልሶ ማለት ይወደዳል፡፡ ሙኣዚኑ ‹‹ሐይየ ዐለሠላ..ህ›› እና ‹‹ሐይየ ዐለልፈላ…ሕ›› በሚል ጊዜ ግን፣ ‹‹ላሐውለ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላሂል ዐሊዪል ዐዚም›› ማለት አለበት፡፡

በመቀጠልም፣ ‹‹አላሁም ረበ ሃዚሂ ዳዕወቲታማ ወሠላቲል ቃኢማ ኣቲ ሙሐመደኒል ወሲ..ለተ ወል ፈዲ..ለተ ወብዐስሁል መቃመል መሕሙደኒ ለዚ ወዐድተሁ›› ይላል፡፡