የንጽህና ትርጉም

የንጽህና መሰረታዊ ትርጉም፡- መጥራት፣ መጽዳት ወይም መወልወል ነው፡፡

አላህ(ሱ.ወ) አንድ ሙስሊም ላዩንም ውስጡንም እንዲያጠራ አዞታል፡፡ ላዩን ግልጽ ከሆኑ እርም ነገሮች፣እንዲሁም ከቆሻሻና ፀያፍ ነገሮች፣ ውስጡን ደግሞ ከማጋራት(ሺርክ) እና፣ እንደ ምቀኝኘት፣ ኩራትና ቂም ከመሳሰሉ የቀልብ በሽታዎች እንዲያጸዳ አዞታል፡፡ ይህን ከፈፀመ፣ የአላህን ውዴታ ይጎናጸፋል፡፡ አላህ(ሱ.ወ)፡-«አላህ (ከኀጢአት) ተመላሾችን ይወዳል፡፡ ተጥራሪዎችንም ይወዳል፡፡» ይላል፡፡ (አል በቀራ 222)

አላህ(ሱ.ወ) ሠላት ከመስገድ በፊት ከቆሻሻዎች መጥራትን አዟል፡፡ ይህ፣ ሠላት ከአላህ ጋር የመገነኛና የመነጋገሪያ መንገድ በመሆኗ ነው፡፡ በተለምዶ እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከአንድ ንጉሥ ወይም መሪ ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ጸዱዕ ሆኖና የሚያምር ልብሱን ለብሶ ነው፡፡ ታዲያ የንጉሦች ንጉሥ የሆነው ኃያሉ አምላክ ጋር የሚገናኝስ እንዴት ሊሆን ይገባል?

ለሠላት አስፈላጊ የሆነው መፀዳዳት እንዴት ዓይነት ነው?

አላህ(ሱ.ወ) አንድ ሙስሊም ሠላት ለመስገድ፣ ቁርኣን ለመንካት ወይም በተከበረው ካዕባ ዙሪያ ለመዞር በሚፈልግበት ጊዜ በኢስላማዊው ሕግ የተደነገገን ልዩና እራሱን የቻለ የመፀዳዳት ዓይነትን በቅድሚያ እንዲያከናውን ግዴታ አዘል ትእዛዝን አዞታል፡፡ በበርካታ ስፍራዎች ላይ ደግሞ ይህንኑ እንዲፈፅም በውዴታ ግዴታ (ሙስተሐብ) መልኩ አበረታቷል፡፡ ከነኚህ ስፍራዎች መካከል፣ በእጅ ሳይነካ በቃል ቁርኣንን በሚያነብ ጊዜ፣ ዱዓ ሲያደርግ፣ ሲተኛ፣ እና ወዘተ…

አንድ ሙስሊም ለመስገድ ሲፈልግ ከሁለት ነገሮች መጥራት ይገባዋል፡፡

ከነጃሳ(ከግልፅ ቆሻሻ)

ከሐደስ(ምናባዊ ቆሻሻ)

 ከነጃሳ(ግልፅ ቆሻሻ) መጥራት

  • ነጃሳ ማለት፣አምልኮ ስንፈፅም ኢስላላማዊው ድንጋጌ በቆሻሻነት የፈረጃቸውንና ከነርሱ እንድንጠራ ትዕዛዝ የሰጠበትን ተጨባጭ ነገሮች የሚገልፅ ነው፡፡
  • ነገሮች መሰረታቸው የተፈቀደና ንጹህ ነው፡፡ ነጃሳ ባዕድና በአጋጣሚ የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ፡ የአንድን ልብስ ንጹህነት ከተጠራጠርንና ነጃሳ እንደተገኘበት እርግጠኞች መሆን ካልቻልን፣ በመሰረቱ ንጹህ ነው እንላለን፡፡
  • ሠላት ለመስገድ ስንፈልግ ሰውነታችንን፣ ልብሳችንና የምንሰግድበትን ስፍራ ከነጃሳ ነገሮች የማጽዳት ግዴታ አለብን፡፡

ነጃሳ ነገሮች

1 የሰው ልጅ ሽንትና ዓይነ ምድሩ
2 ደም፤ ትንሽ ጠብታ ደም ግን ችግር የለውም
3 ስጋቸው የማይበላ የማንኛውም እንሰሳት ሽንትና ፋንድያ (ገጽ 183 ተመልከት)
4 ውሻና አሳማ
5 ሙት እንሰሳት (የሞቱ እንሰሳትን ሁሉ የሚመለከት ሲሆን ስጋቸው የሚበላና በሸሪዓዊ መንገድ የታረዱትን ግን አይመለከትም፡፡ ገጽ 184 ይመልከቱ ) የሞተ ሰው አካል ፤አሳና ነፍሳቶች ቢሞቱም ንጹህ ናቸው፡፡

ከነጃሳ መጽዳት

ነጃሳ(ግልፅ ቆሻሻ) ከሰውነት፣ ከልብስ ወይም ከአንድ ቦታ፣ ወዘተ. ላይ ሲታጠብ፣አወጋገዱ፣ ውሃን ወይም ሌላን ነገር በመጠቀም፣ አለያም በሌላ መንገድ ቢሆንም፣ የነጃሳው ነገር መልኩና አካሉ ከቆሸሸው ቦታ ላይ መወገዱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢስላማዊው ድንጋጌ ነጃሳን ማስወገድን እንጂ ከውሻ ነጃሳ በስተቀር ነጃሳን ለማስወገድ በተወሰነ ቁጥር ማጠብን መስፈርት አላደረገም፡፡ የውሻ ነጃሳም ቢሆን ልጋጉን፣ሽንቱንና ዓይነ-ምድሩን እንጂ አካሉን አያካትትም፡፡ የውሻን ቆሻሻ በተመለከተ፣የመጀመሪያውን በአፈር አድርጎ፣ ሰባት ጊዜ ማጠብን አዟል፡፡ የተቀሩትን ነጃሳዎች ግን መልካቸውና አካላቸው መወገዱ ብቻ በቂ ነው፡፡ የመልኩ ፋና እና ሽታው መቅረቱ ችግር አይኖረውም፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የወር አበባ ደምን በማጠብ ዙሪያ ለአንዲትን ሠሓቢት፡- «ደሙን ማጠብሽ ይበቃሻል ፋናው መቅረቱ ችግር የለውም፡፡» ብለዋታል፡፡ (አቡ ዳውድ 365)

የኢስቲንጃእ(ሀፍረተ ገላንና አካባቢውን ማጠብ) እና የመጸዳዳት ስርዓት

  • አንድ ሰው ሽንት ቤት ሲገባ፣ ግራ እግሩን ማስቀደምና ‹‹ቢስሚላህ፣አላሁመ ኢኒ አዑዙ ቢከ ሚነል ኹቡሲ ወል ኸባኢስ›› - በአላህ ስም፣ አምላኬ ሆይ ከእርኩሱና ከእርኩሲቷ (ሰይጣን) በአንተ እጠበቃለሁ- ማለቱ ይወደዳል፡፡
  • በሚወጣ ጊዜ ደግሞ ቀኝ እግርን በማስቀደም ‹‹ጉፍራነከ›› -ምህረትህን ለግሰን- ማለት ይወደዳል፡፡
  • በሚጸዳዳበት ጊዜ ሀፍረተ ገላውን ከሰዎች እይታ የመከለል ግዴታ አለበት፡፡
  • ሰዎች በቆሻሻው በሚጎዱበት ስፍራ መጸዳዳት ክልክል ነው፡፡
  • የሚጸዳዳው ከቤት ውጭ ባለ መስክ ውስጥ ከሆነ፣ እርሱ ሊጎዳቸው፣ እነሱም ሊጎዱት የሚችሉ እንሰሳት አለያም አውሬዎች የሚኖሩበት በሆነ ጎሬ ውስጥ መጸዳዳቱም ክልክል ነው፡፡
  • የሚጸዳዳው በሜዳ ላይ ከሆነና የሚከልለው ግርዶሽ የሌለ ከሆነ፣ ፊቱን ወደ ቂብላ ማዞር ወይም ለቂብላ ጀርባውን መስጠት አይገባውም፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «በምትጸዳዱበት ጊዜ፣ ስትሸኑም ሆነ ዓይነምድር ስታስወግዱ፣ፊታችሁን ወደ ቂብላ አታዙሩ ጀርባችሁንም ለቂብላ አትስጡ፡፡» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 386/ ሙስሊም 264)
  • የሚፈናጠሩና የሚረጩ ነጃሳዎች ልብሱና ሰውነቱን እንዳይነኩት ጥንቃቄ ማድረግ፣ከነኩት ደግሞ የማጠብ ግዴታ አለበት፡፡
  • ተጸዳድቶ ሲያበቃ ከሁለት አንድ ነገር መፈፀም አለበት
የሽንትና የዓይነምድር መውጫ አካሎቹን በውሃ ማጠብ (ኢስቲንጃእ)

በሶስት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ደንጋዮች፣ለስላሳ የመጸዳጃ ወረቀቶች፣ ወይም ሰውነቱን ከነጃሳ ሊያጸዳለት በሚችል መሰል ነገር ማጽዳት ነው፡፡

 ሐደስ(ምናባዊ ቆሻሻ)

  • ሐደስ፡ ማለት ምናባዊ የሆነ፣ ሰው ከርሱ ከመጥራቱ በፊት ሠላት መስገድን የሚከለክል ነገር ነው፡፡ እንደ ነጃሳ በግልፅ የሚነካ ነገር አይደለም፡፡
  • ሐደስ ከአንድ ሙስሊም ላይ የሚወገደው ሊያጠራ በሚችል ውሃ ወዱእ ሲያደርግ ወይም ገላውን ሲታጠብ ነው፡፡ ሊያጠራ የሚችል ውሃ የሚባለው፣ ነጃሳ ያልተቀላቀለበት ውሃ፣ ወይም ነጃሳ ነክቶት፣ መልኩን ወይም ጣዕሙን ወይም ሽታውን ያልቀየረው ውሃ ነው፡፡

ሐደስ በሁለት ይከፈላል፡፡

አንድ ሰው እርሱን ከላዩ ላይ ለማስወገድ የግድ ውዱእ ሊያደርግ የሚገባው ዓይነት ሲሆን እሱም ትንሹ ሐደስ ይባላል፡፡
አንድ ሰው እርሱን ከላዩ ላይ ለማስወገድ የግድ በውሃ ገላውን ሙሉ በሙሉ በማደረስ መታጠብ ያለበት ዓይነት ሲሆን ትልቁ ሐደስ በመባል ይጠራል፡፡

ትንሹ ሐደስና ውዱ

አንድ ሙስሊም ምናባዊ ጽዱዕነቱን አጥቶ ውዱእ ማድረግ የግድ የሚሆንበት ከሚከተሉት ነገሮች አንዱ በሚከሰበት ጊዜ ነው፡፡

  1. ሽንት፣ ዓይነምድርና ማንኛውም ከሁለቱ መጸዳጃ ብልቶች የሚወጣ ንፋስና መሰል ነገሮች ከወጡ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጽዱዕነትን የሚያፈርሱ ነገሮችን ሲዘክር፡- «ወይንም ከናንተ አንዱ ከዓይነምድር ቢመጣ» ብሏል፡፡ (ኒሳእ 43) ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) በሠላት ውስጥ ሆኖ ሐደስ እንደተከሰተበት የተጠራጠረን ሰው በማስመልከት፡- «ድምጽ እስካልሰማ ወይም ሽታ እስካለገኘ ድረስ አቋርጦ አይሂድ!» ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 175/ ሙስሊም 361)
  2. ያለግርዶ በስሜት ብልትን መንካት፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- «ብልቱን የነካ ሰው ወዱእ ያድርግ» ብለዋል፡፡ (አቡ ዳውድ 181)
  3. የግመል ስጋ መብላት፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፣ «የግመል ስጋን በመብላቴ ውዱእ ላድርግን?» የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ «አዎን» በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ (ሙስሊም 360)
  4. አእምሮ በእቅልፍ ወይም በአእምሮ ህመም ወይም በስካር መሳት