ትልቁ ሐደስ(ምናባዊ ቆሻሻ) እና ትጥበቱ

ትጥበትን ግድ የሚያደርጉ ነገሮች

እነኚህ ነገሮች፣ አንድ ሙስሊም ከተገበራቸው ሠላትን ከመስገድና ጠዋፍ ከማድረግ በፊት ገላውን መታጠብ ግዴታ የሚያድርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ ሰው ከመታጠቡ በፊት ትልቁ ሐደስ አለበት ይባላል፡፡

  1. የፍቶት ፈሳሽ (የዘር ፍሬ - መኒይ)፣ በንቃት ሕሊናውም ሆነ በእንቅልፍ ውስጥ፣ በእርካታ መልክ እየተገፋተረ መውጣት፡፡ የፍቶት ፈሳሽ (መኒይ) የሚባለው በጣም በስሜት ውስጥ ሲገባና እርካታ ሲሰማ ከብልት የሚወጣ ነጭና ትኩስ ፈሳሽ ነው፡፡
  2. የግብረ ስጋ ግንኙነት፡ ይህ የፍቶት ፈሳሽ (መኒይ) ባይፈስም፣ የወንድ ብልት ብቻ የሚጠቁም ድርጊት ነው፡፡ የወንዱ ብልት ጫፍ ሴቷ ብልት ውስጥ መግባቱ ብቻ ትጥበትን ግዴታ ያደርጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፡-«(ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት ጀናባ) ብትኾኑ (ገላችሁን ) ታጠቡ፡፡» ይላል፡፡ (አል ማኢዳ 6)
  3. የወር አበባና የወሊድ ደም መፍሰስ
    • የወር አበባ ደም የሚባለው፣ በየወሩ ሴቶች የሚፈሳቸው ተፈጥሯዊ ደም ነው፡፡ ሰባት ቀን ወይም ከዚያ በላይ ይፈሳል፡፡ እንደሴቶቹ ተፈጥሯዊ ልዩነት ከዚያም ያነሰ ሊሆን ይችላል፡፡
    • የወሊድ ደም ደግሞ በመውለዳቸው ምክንያት ከሴቶች የሚወጣ ደም ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል፡፡

የወር አበባና የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች፣ ደሙ በሚፈስባቸው ቀናት የጾምና የሠላት ግዴታ ይነሳላቸዋል፡፡ ከደሙ ሲጸዱ፣ ጾሙን ይከፍላሉ ሠላቱን ግን አይከፍሉም፡፡ በነኚህ ቀናት ውስጥ ባሎቻቸው ሊገናኟቸው አይፈቀድላቸውም፡፡ ከግንኙነት መለስ ባለ ነገር ግን መጠቃቀምና መደሰት ይችላሉ፡፡ ሴቶቹ ደሙ ከቆመላቸው በኋላ ገላቸውን መታጠባቸው የግድ ይሆናል፡፡

አላህ (ሱ.ወ)፡- «ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹህ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቧቸው፡፡ ንጹህ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኟቸው፡፡» ይላል፡፡ (አል በቀራ 222) «ንጹህ በኾኑም ጊዜ » ማለት ገላቸውን በታጠቡ ጊዜ ማለት ነው፡፡

አንድ ሙስሊም ከጀናባ ወይም ከትልቁ ሐደስ የሚጠራው እንዴት ነው?

አንድ ሙስሊም መጽዳትን በልቡ አስቦ ገላውን በሙሉ በውሃ ከታጠበ፣ ከትልቁ ሐደስ ይጸዳል፡፡

  • ይህ ትጥበት የተሟላ የሚኾነው ግን፣ ከተጸዳዳ በኋላ የሚያደርገውን ዓይነት ኢስቲንጃ አድርጎ፣ውዱእን አስከትሎ፣ከዚያም ሰውነቱን በጠቅላላ በውሃ አዳርሶ ሲታጠብ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ትጥበት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የአስተጣጠብ ፈለግ ጋር ስለሚገጣጠም ከምንዳ አንፃር ከፍተኛው ነው፡፡
  • አንድ ሙስሊም ከጀናባ ሲታጠብ ትጥበቱ ከውዱእ ያብቃቃዋል፡፡ ከትጥበቱ በተጨማሪ ውዱእ ማድረግን አይገደድም፡፡ በላጩ ግን፣ በነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) የአስተጣጠብ ፈለግ መሰረት ወዱእንም ያካተተ ትጥበት መታጠብ ነው፡፡

በካልሲ ላይ ማበስ

ከኢስላም ገርነት መገለጫዎች መካከል አንድ ሙስሊም ወዱእ ሲያደርግ በውሃ በራሰ መዳፉ እግሮቹን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነውን የላይኛውን የካልሲውን ወይም የጫማውን ክፍል እግሮቹን በመታጠብ ምትክ ማበስ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ግን፣ ቀደም ሲል ውዱእ እያለው ያጠለቃቸው ወይም የተጫማቸው መሆን አለበት፡፡ ሳያወልቅ ሊያብስ የሚችለው ደግሞ፣ ነዋሪ ከሆነ ከ24 ሰዓታት ላልበለጠ ጊዜ ሲሆን መንገደኛ ከሆነ ደግሞ ለ72 ሰዓታት ያህል ነው፡፡

ከጀናባ ለመጽዳት በሚያደርገው ትጥበት ግን በፈለገው ሁኔታ ላይ ቢሆንም ሁለቱን እግሮችን ማጠብ ግዴታ ነው፡፡


ውሃን መጠቀም ያቃተው ወይም ያልቻለ ሰው

አንድ ሙስሊም በበሽታ፣ ውሃ በማጣት፣ ወይም ለመጠጥ ብቻ እንጂ ውሃ የማያገኝ በመሆኑ ምክንያት ውዱእ ለማድረግ ወይም ሰውነቱን ለመታጠብ ውሃን መጠቀም ካልቻለ አለያም ካቃተው፣ ውሃ አግኝቶ መጠቀም እስከሚችል ድረስ በአፈር ተየሙም ማድረግ ይፈቀድለታል፡፡

የተየሙም አደራረግ፡ በውስጠኛው መዳፎቹ አፈር ላይ አንድ ምት በመምታት በመዳፎቹ ላይ በቀረው አፈር ፊቱን ማበስ፣ቀጥሎም የቀኝ እጁን የላይኛውን የመዳፍ ክፍል በግራው የውስጠኛ መዳፍ ማበስ፣ እንዲሁም የግራ እጁን የላይኛውን የመዳፍ ክፍል በቀኙ የውስጠኛ መዳፍ በማበስ ይፈፅማል፡፡